January 11, 2018

በደርግ ዘመን የ11ኛ ይሁን የ12ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ (በውል አላስታውስም) የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ሲሰራ፣ በትምህርት ቤታችን አማካኝነት ፍብሪካውን መጎብኘታችን ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ በጦርነት የሚባክን እንጂ፣ ለፋብሪካ የሚለማ ገንዘብና ጊዜ ሀገሪቱ አልነበራትም፤ጨቋኙን ንጉስ ያስወገዱት አብዮተኞች አብታዮዊ ባለሀብት ለመሆን እድል ሳያገኙ ነው በ17 አመት የተወገዱት፡፡ እና ፋብሪካ ብርቅ ነበር፡፡ ዋናው ነጥብ ግን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ አንድ ፍብሪካ አገኘች›› እንጂ፣ ኦሮምያ አንድ ፋብሪካ ተገነባላት ያለ ይቅር፣ ያሰበም አልነበረም፡፡ አማሮች፣ ትግሬዎች፣ አፋሮች፣ ሲዳማዎች . . . . ወዘተ. ‹‹ለእኛስ!?›› ብሎ ማጉረምረም ከልቦናቸው አልነበረም – የደስታው ተቋዳሽ ነበሩ፡፡ እነዚህ ህዝቦች፣ በዚያን ጊዜ የሚኖሩበትን ክልል ካርታና ባንዲራ ከሁሉም በላይ በልቦናቸው እንዲደምቅ፣ ኢትየጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲደበዝዝ አልተደረገም ነበር፡፡

ዛሬ ሁሉም ለክልሉ እንጂ ለሀገሩ እንደሚገነባ አያስብም፡፡ በዚህም የተነሳ ሀገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ ገብታ፣ የሌላትን ገንዘብና ሀብት የህዝቦችን አመጽ ለማቆምና በዚህም የገዢዎችን ስልጣንን ለማደላደል እያባከነችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ክልሎች ለምን ለሙ?›› የሚል ብኩን ተጠየቅ ለማንሳት ፈልጌ አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ዩኒቨርሲቲን ለየብሄሩ ለማዳረስ በየምድረበዳው (ለትራንስፖርትና ለአቅርቦት አስቸጋሪ በሆነ ቦታ) መገንባት ከዚህ ተለይቶ የሚታይበት ሁኔታ አልታየኝም፡፡ ቤተመጻህፍት፣ ላብራቶሪ (ቤተሙከራ) እና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች የተሟሉላቸው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሌሏቸው አካባቢዎች፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ይገንባልን›› ብለው ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡት፣ ከሌላው ክልልና ብሄረሰብ እንዳያንሱ እንጂ፣ በጤነኛ አእምሮ ለልጆቻቸው አስበው አይመስለኝም፡፡ ለልጆቻቸው አስበው ቢሆን ኖሮ፣ ከዩኒቨርሲቲው ህንጻ በላይ 12ኛ ክፍል ጨርሰው የስምንተኛ ክፍል ፈተና የሚወድቁ ልጆቻቸው የወደፊት ህይወት ያስጨንቃቸው ነበር፡፡

ከሱማሌ ክልል ወደሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቀሉ – እነዚህ ሰዎች ለሱማሌዎቹ ኦሮሞዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ በኦሮምያ ክልል ስኳር የጫኑ መኪኖች እንዳያልፉ ተደረገ – እነዚህ መኪኖች ስኳሩን የጫኑት ለሌላ ክልል ህዝቦች እንጂ ለኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ የራሱን ክልላዊና ጎሳዊ ማንነት ያደመቀ ህዝብ፤ ሌላውን ህዝብ በኢትዮጵያዊነት መለጽር ሊመለከት አይችልም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በ27 አመት የአስተዳደር ጊዜው ኢትዮጵያን በጎሳዊ – ክልል እንደመከፋፈል ውጤታማ የሆነበትን ተግባር አላከናወነም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በክልሎች መካከል እጅግ ያልተመጣጠነ ልማታዊ እድገትም የታየው በዚሁ በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ነው፡፡ አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ከሀገሪቱ ውስጥ ተቆርጠው የወጡ ይመስል በወረፋ ከሚዳረሰው የኢቢሲ የልማት ዘገባ እንኳን ሲጠፉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ልማታዊ ባለሀብት ሌማት በቀን ሶስት ጊዜ በየቲቪው ሲቀ ርቡ፣ እራሱ ኢህአዴግ በየአካባቢው እንዲዳብር ያደረገው ጎሳዊ ጡንቻ ዝም ብሎ ያየኛል ብሎ መጠበቁ የሚገርም ነው፡፡

. .. . . . አሁን ኢህአዴግ በየአካባቢው ለ27 አመት የተመጣጠነ ምግብ እየመገበ፣ አካል ብቃት እንቅስቃሴ እያሰራ ያዳበረው ጎሳዊ ጡንቻ ምን ሊያመጣበት – ሊያመጣብን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ እና አሁን ኢህአዴግ ማድረግ ያለበት ‹‹የግጭቶች መንስኤ የፌደራል ስርአቱ እንዳልሆነ ምሁራን ገለጹ›› የሚል ፕሮፖጋንዳ መስራት ሳይሆን፣ የፌደራሊም ስርአቱን ማሻሻል ወይም ሙሉ በሙሉ መቀየር ነው፡፡