በቀለ ገርባ እና ሌሎችም ተከሳቾች እስር ተፈረደባቸው
FACEBOOK/BEKELE GERBA

የኦሮሞ ፌዴራሊስት (ኦፌኮ) ኮንግረስ ከፍተኛ አመራር የሆኑትን አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ችሎትን ተዳፍራችኋል በሚል እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የእስር ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የተከሰሱት አራቱ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጉርሜሳ አያኖ እና አቶ አዲስ ቡላላ እንዲሁም ሌሎቹ ተከሳቾች ናቸው ቅጣቱ የተጣለባቸው።

ተከሳሾቹ ለምስክርነት የጠሯቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና ሌሎች ሰዎችን ማስቀረብ ባለመቻሉ ችሎቱን የተቃወሙ ሲሆን አቶ በቀለ ይህንን ቅዋሜያቸውን ለመግለፅ በችሎቱ ሂደት ወቅት ቆመው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ከፍተኛ የመንግሥት ባለልጣናቱ በምስክርነት መቅረብ አያስፈልጋቸውም በማለት ሲወስን ነበር ተከሳሾቹ ተቃውሟቸውን ያሰሙት።

ተከሳሾቹ በንግግር በችሎቱ ላይ ተቃውሞሟቸውን ከማሰማታቸው በተጨማሪ በዝማሬም ሃሳባቸውን መግለፃቸውን ሂደቱን የታደሙ ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ በሌላ ክስ በችሎቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ሦስት ተከሳሾችም በተቃውሞውና በዝማሬው ወቅት በማጨብጭብ ችሎት ተዳፍራችኋል በሚል እንዲሁ የሦስት ወር እስር ተፈርዶባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በምስክርነት የተጠሩት የመንግሥት ባለስልጣናት ችሎት ያለመቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በማረሚያ ቤት ያሉ ምስክሮችም እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት በክስ ላይ ያሉና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞችን ለመፍታት ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።

በተያያዘ ዜና የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በምስክርነት የተጠሩትን እስክንድር ነጋ እና ውብሸት ታየን ማቅረብ ባለመቻሉ የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጉዳይ ለሌላ ጊዜ ተቀጥሯል።

SOURCE    –  BBC/AMHARIC