ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ አደረገ – በጌታቸው ሺፈራው

image_pdf

January 12, 2018

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ አደረገ

(በጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ 28 ቀሪ ምስክሮችን ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎበታል። ዐቃቤ ሕግ ከሚያዚያ 14 እስከ ሚያዚያ 24/2009፣ ከነሃሴ 1 እስከ ነሃሴ 12/2009 ዓም እንዲሁም ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3/2010 ዓም ምስክር እንዲያሰማ ተከታታይ ቀጠሮዎች ተሰጥቶታል።

ዐቃቤ ሕግ ነሃሴ 12/2009 ዓም በነበረው ቀጠሮ ምስክሮችን ለማቅረብ ለ5 ወር ረዥም ቀጠሮ ቢሰጠውም፣ ከ5 ወር በኋላ ከታህሳስ 23 እስከ ጥር 3 በነበረው ቀጠሮ ያቀረበው 5 ምስክሮችን ብቻ ነው። በተለይ በ5 ተከታታይ ቀናት ምስክር ሳያቀርብ ተከሳሾች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብረው ሲመላለሱ ሰንብተዋል። ዐቃቤ ሕግ በመጨረሻው ቀጠሮ 28 ምስክሮች ስለሚቀሩበት እንዲያሰማ ጥያቄ አቅርቧል። አብዛኛዎቹ ምስክሮች ከእስር ስለተፈቱ ፖሊስ በአድራሻቸው እንዳላገኛቸውና በሀገሪቱ አፈላልጎ ለማቅረብ ጊዜ እንዲሰጠው፣ አንድ መቀሌ የሚገኙ ምስክር በህመም ምክንያት መቅረብ አለመቻላቸውን ፖሊስ በስልክ ማረጋገጡን እንዲሁም ሁለት ምስክሮች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደርሷቸው፣ ቀርበው ለመመስከርም መተማመኛ ፈርመው ስለቀሩ ታስረው እንዲቀርቡ ጥያቄ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው ዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለማቅረብ ተከታታይና ረዥም ቀጠሮዎች ተሰጥቶት ማቅረብ እንዳልቻለ በተለይም ለአሁኑ ቀጠሮ ዝግጅት 5ወር ቢሰጠውም ማቅረብ አለመቻሉን፣ ታመሙ ስለተባሉት ምስክር የህክምና ማስረጃ አለማቅረቡን፣ ፈርመው ቀሩ የተባሉት ምስክሮችን ጥያቄም በቀጠሮው መጨረሻ ሳይሆን ምስክር ባልቀረበባቸው የቀጠሮ ቀናት ማሳሰብ ሲችል አለማቅረቡ ተከሳሾች ለማጉላላት እየሰራ እንደሚገኝ ያሳያል ብለዋል። በመሆኑም ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሳይሰጠው ምስክር የማሰማት መብቱ ታልፎ መዝገቡን መርምሮ ለመበየን ቀጠሮ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። የመጨረሻው ቀጠሮ ትናንት ጥር 3/2010 ዓም የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት የዐቃቤ ሕግ ጥያቄ እና የተከሳሾቹን ተቃውሞ መርምሮ ለመበየን በአዳር ለዛሬ ጥር 4/2010ዓም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ጥር 4/2010ዓም በሰጠው ብይንም ዐቃቤ ሕግ ከእስር ተፈትተው ፖሊስ በአድራሻቸው ስላላገኛቸው በተለዋጭ ቀጠሮ ይቅረቡልኝ ብሎ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎበታል። ምስክሮቹ ማረሚያ ቤት የነበሩ በመሆናቸው ዐቃቤ ሕግ የማቅረብ እድል እንደነበረው፣ አፈላልጌ አቀርባለሁ የሚለው የመገኘት እድላቸው ጠባብ በሆነበት እና የተጠየቀው ተለዋጭ ቀጠሮም የተከሳሾችን መሰረታዊ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው ብሏል። መቀሌ የሚገኙት ታመዋል የተባሉ ምስክርም ስለመታመማቸው የህክምና ማስረጃ ስላልቀረበ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም። ሆኖም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደርሷቸው የቀሩት 2 ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 18/2010 ለመጨረሻ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ምስክሮቹ በዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ ችግር እንዳልቀሩ፣ ፍርድ ቤቱም ትዕዛዙን ማስከበር ስላለበት ታስረው እንዲቀርቡ ወስኗል።

በሌላ በኩል 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ ዛሬ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ሲሆን የቂሊንጦ እስር ቤት ተወካይ ተጠይቀው “በተደጋጋሚ ውጣ ብለን ጠይቀነው፣ አሞኛል ብሎ አልወጣም” የሚል መልስ ሰጥተዋል። እስር ቤቱ 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘን ያላቀረበበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዲገልፅ እና በቀጣይ ቀጠሮም እንዲያቀርበው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ ትናንት ጥር 3/2010 ዓም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤት መመላለስ እንደማይፈልግና ፍርድ ቤቱ በሌለበት የሚወስነውን ውሳኔ እንደሚቀበል ለችሎቱ መግለፁ ይታወሳል።

No widget added yet.

← Heathrow terror arrest: Woman, 27, arrested after arriving at airport on flight from Ethiopia የቴሌ ስራ አስኪያጅ አንዱአለም አድማሴ በደህንነት ቢሮ እየተመረመረ ሲሆን ነገሪ ሌንጮ ከስልጣን ሊባረር ነው ። →

Leave A Reply

Comments are closed