January 12, 2018

– ጴጥሮስ አሸናፊ

ሁዳዱ ጣና በወጀቡ እያጨበጨበ፣ የሕይወት እስትንፋሱን እንደ ገነት ማይ የሚረጭላት የዘንባባ ከተማዋ ባሕር ዳር በጥምቀት ማግስት በቃና ዘገሊላ ቴዲ አፍሮን ታስተናግዳለች። ቃና ዘገሊላ ደግሞ የሰርግ፣ የደስታ፣ የፍሰሃና የመጀመሪያ ተአምር በዶኪማስ ቤት የተፈፀመበት ዕለት ነው።

ቴዲ አፍሮ አንተ ለባሕር ዳር :- እንደ ዘንባባዋ፣ እንደጣና፣ እንደ አባይ አንዱ ነህ፡፡ እነኝህ ሶስትም አንድም ሆነው ባህርዳርን ባህርዳር ያደረጉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ልታዜምላቸው ቀጠሮ መያዝህን ሰምተው ላንተ ክብር እያረገዱልህ ነውና ትንሽ ስለ መዳረሻህ እነሆ፡-

ዘንባባ በመፅሐፍ ቅዱስ ከ 30 ጊዜ በላይ፣ በቅዱስ ቁርዓን ከ 22 ጊዜ በላይ ስሙ የተጠራ የእፅዋት ተወካይ ነው፡፡

ዘንባባ በሚሶፖታሚያ የስልጣኔ በርም ነው፡፡
የሮማውያኑ የድል ምልክት ነው፡፡
የአይሁዳውያን የህይወት ዛፍ ነው፡፡
የእነ ሳኡዲ አረቢያ ፣ የነደቡብ ካሮላይና፣ የነሓይቲ፣ የነፍሎሪዳ …..
የሰንደቃቸው አርማ ነው፡፡

በሁዳዴ መጨረሻው ሳምንት ሆሳዕና (መድሃኒት) ሆኖ፣ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሱስ ወደ እየሩሳሌም ሲመጣ ተከታዮቹ በዘንባባ ተቀብለውታል፡፡

እናም ዘንባባ የእፅዋት ሁሉ ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡ አንተ የሙዚቃ ንጉሥ እንደሆንከው ሁሉ፡፡ ዘንባባ ባህርዳር ላይ ለ 50 ዓመታት ያህል ነግሷል፡፡
የክቡር ዘበኛው አባይ ዘንባባን ያጅበዋል፡፡

ሁዳዱ ጣና ደግሞ በወጀቡ እያጨበጨበ፣ የሕይወት እስትንፋሱን እንደገነት ማይ ይረጨዋል፡፡
አባይ፣ ጣና እና ዘንባባ ሚዜ ሆነው ደግሞ ባህርዳርን ይሞሽራሉ፡፡
አባይ ጣናን በፍቅር ስሞ ጭስ አባይ ሲደርስ ለሙሽራዋ የፏፏቴ ዳንኪራ ይመታል፡፡
ዳንኪራው ተራ ረገጣ አይደለም፡፡
በጎጃም ዝናብ ምት አሊያም በጎንደር ዋንጫ ልቅለቃ ይሆንና ግጥሙ በዋሸራ ቅኔ ይከራል፡፡
በፏፏቴው ቀስተ ዳመና ጫጉላው ይዋባል፡፡
ሙሽሪትን ተፈጥሮ ራሱ ወርዶ ያጫውታታል፡፡
ለጥሎሽ ደግሞ ማኛውና ቅቤው እስከ ማሩ በአርሶ አደሩ፣ አሳው በከተሜው ይመጣላታል፡፡
በቃ ባህርዳር ተፈጥሮ በራሱ ወጪ የሞሸራት ከተማ ናት !
አለፍ ስትል ደግሞ ሽንጣሙ ጣና በመርከብ እያስዋኘህ ወደ ጣና ስር ገዳማት ይሸኝሃል፡፡ በእነዚህ ገዳማት ከእስራኤል ገሊላ የግብፅን በረሃ ችላ፣ የኤርትራን ባህር አቋርጣ ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ያረፈችበትን ቦታ እስከ አሻራው ታገኛለህ፡፡

ከኦሪት መስዋዕት እስከ ቅዱስ ያሬድ የተሰጥኦ አሻራ በጣና ገዳማት በባህር ታጅበህ ታያለህ ፡፡
የእነ አለቃ ገብረሃና፣ የእነ ፋሲል የጥበብ ድካም በጣና ገዳማት አለ፡፡ ጣና ያልተፈታ የምስጢር ሳጥን ነው፡፡
ከዓለማዊ ስልጣኔ እስከ መንፈሳዊ ምጥቀት ጣና በስሩ አቅፎ ይዟል፡፡ ጣና የውብ አሞራዎች፣ እንደ ህዳር አክርማ በሚዘናፈሉ በለምለም ሳሮች ብቻ የተሸለመ ሀይቅ አይደለም፡፡ በጣና አምላክ ዥንጉርጉር ተፈጥሮን
አኑሮበታል፡፡

ጣና ልዩ ልዩ ዛፎችን አስጠልሏል፡፡ አዕዋፋትን ከጉያው አዝሎ በወጀቡ ያጫውታል፡፡ ማረፊያ ደሴት አለው፡፡ ጣና ውሃ ሆኖ የብሱን ያውቃል፡፡ አባይ ከሰከላ ተነስቶ በረጅም ሽንጡ እርቃኑን እየተሳበ ጣናን በፍቅር ሳም አድርጎት ያልፋል፡፡ዜመኛ አሳሳም! ተፈጥሮም ፍቅር ይዞት ሲሟዘዝ ጣና ላይ ታያለህ፡፡
በቃ! ጣና ተፈጥሮ የደረሰው ተውኔት ነው፡፡ የተውኔቱ ተዋህናይት ደግሞ ውቢቷ ባህር ዳር ናት፡፡
በርግጥም ቴዲያችን አንተ ለባሕር ዳር እንደጣና፣ እንደ አባይ፣ እንደ ዘንባባዋ አንዱ ነህ፡፡ ቀድመህ በጥልቁ ምናባህ ከተቀኘህላት አዳምና ሄዋን በተንሸራሸሩባት፣ መልከጼዴቅ በአጸደ ህይወት በተነጠቀባት፣ ሄኖክ የአለምን የምስጢር ቋጠሮ ፅፎ ለአለም ያበረከተባት …
.
.
የጀግኖች ሀገር ያዳም እግር አሻራ
ፈለገ ግዮን ያንቺ ስም ሲጠራ …
ያልካት
.
.
ቀደም ብለህም
.
.
” የዮቶር ልጅ ርስቱ
አባይ ሆኖ ጣና ዳር ቤቱ ”
….ስትል በማራኪ ስንኝህ የተቀኘህላት የጎጃሟ ሙሽራ ባህር ዳር እጆቿን ዘርግታ በጉጉት ትጠብቅሀለች።
ጥር 12 ቀን ቅዳሜ!