January 13, 2018 21:24

ሰሞኑን ፊንፊኔ የተባለ ሬዲዮ የታዋቂውን ጀነራል ታደሰ ብሩን ልጆች ቃለመተይቅ ሰምቼ ብዙ ነገሮች ወደ አእምሮዬ መጡ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የቃምልልስ አድራጊውን ጋዜጠኛ የአጠያየቅ ለዛና የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በጣም አድንቄያለሁ፡፡ ቀጥልበት! የጀነራሉ ልጆች ሙሴና ማርታ መልስ አሰጣጥም ፍጹም የራሳቸውን የሆነውን የቤተሰብ ጉዳይ ሁሉ ሳይቀር ለሕዝብ በማጋራታቸው በጣም ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ይህን ቃለ ምልልስ ስሰማ ብዙ ከዚህ በፊት የሰማኋቸው ጉዳዮች ሙሉ በሙሉም ባይሆን የተረዳሁት ብዙ አለ፡፡ ቀሪውንም ቢያንስ እኔም መልሼ ጥያቄ እንዳቀርብና ምን አልባትም መልስ የማገኝ ሆኖ ተሰማኝ፡፡
ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት በተለይ ከአለፉት 4ና 5 ዓመት ወዲህ እኔ በአብዛኛው ኦሮሞን የተመለከቱ ብዙ መጣጥፎችን አስነበብ ነበር፡፡ ለብዙዎች በተለይም ኦሮሞነታቸውን ለሚያስቀድሙ እኔ የምጽፈው ነገር እንደማይመች እረዳለሁ፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛው ለሚባለው ሰው ለብዙ ኦሮሞ ሳይቀር ሀሳቤ እነሱም የሚጋሩት እንደሆነ በብዙ አጋጣሚዎች አይቼዋለሁ፡፡ እኔ ያለ ኦሮሞ ሕዝብ ሙሉ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አገር ሆና መቀጠል አትችልም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ እኔ የማስበው የእኔ ብቻ እይታ ሳይሆን ነባራዊ ነገሮችም የሚናገሩት ፊት ለፊት ያለ ሀቅ ነው፡፡ የእኔንና ኦሮሞነትን እንደተለየ ስብዕና የሚያዩ ሰዎችን የማያግባባን ግን አያሌ ጉዳዮች አሉ፡፡ ኦሮሞነትን እንደተለየ ስብዕና ስል ሁለቱንም ጽንፍ  ማለቴ ነው፡፡ ሌሎች ኦሮሞን የሚያዩበት ባዕድ አተያይና  ኦሮሞ ሆነው ኦሮሞንትን እንደ ልዩ ማሕበረሰብ የሚያዩትን ነው፡፡ ለእኔ ግን እስካሁንም በአብዛኛው ስጽፍ የነበርኩት አሁንም አይሎና ትኩረት የሚሰጠኝ ኦሮሞ ሆነው ኦሮሞነትን እንደተለየ የሚያዩትን ነው፡፡ ዛሬም ላነሳ የፈለኩት ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ጥቂት ግን ምን አልባትም ጥያቄዎቼን ሊመልሱ የሚችሉ የሌሎችን በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ ያለውን አተያይ በመሀል አቀርባለሁ፡፡

ጥያቄ አንድ ፡- የኦሮሞ ሕዝብ ትግል መሠረታዊ ዓላማ ምንድን ነው?

ይህን ጥያቄ  የማነሳው በብዙ ቦታና ጊዜያት የኦሮሞ ሕዝብ የትግል አላማ የተለየ እንደሆነ የሚመስል እንቅስቃሴ ስለሚታይ ነው፡፡ ይሄን ስል ግን አብዛኛው ኦሮሞን የሚወክል ሆኖ ሳይሆን አነሰም በዛም የተወሰኑም ቢሆኑ የሚገልጹት ነው፡፡ በበለጠም ደግሞ በተደራጀ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱተም የዚሁ አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኢትዮጵያዊነትን እስከመካድ የደረሰ በአመዛኙም ኦሮሚያ የተባለውን ምድር መገንጠልን የሚያስቡ ናቸው፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን ኦሮሚያን ከን ኦሮሞቲ (ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት) የሙሉት አባባል የመጨረሻ አላማቸውን የሚናገር ይመሰልላል፡፡ ግን ለአብዛኛው ኦሮሞ ኢትዮጵያዊነቱ ጥያቄ ነው? ነው ወይስ የኦሮሞ ሕዝብ ትግልን ሆን በለው ወደሌላ ሊያንሻፍፉት እየሰሩ ነው? እርግጥ ነው ሁሉም አንድ አይነት ይሁን አይባልም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብስ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ የሚፈልገው ፍትህ አለ?

ጥያቄ ሁለት፡ – የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለምን ይሄን ያህል ረዥም ታሪክ ሊኖረው ቻለ?

እንደምረዳው የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ተጀመረ የሚባለው በሜጫና ቱለማ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ተነስተው አገርና ሕዝብንም ለማፍረስ የቆሙለት አላማ ሳይቀር ይዘው ተሳክቶላቸዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ነው ብለው የጀመሩ ግን ሕዝቡን ከጨቋኞች እናላቅቃለን ብለው ዛሬ 50ዓመት ገደማ ሆኖታል፡፡ ይህ ትግሉን ለማንቋሸሽ አደለም ግን ያልተሳካበት ምክነያት ምንድነው ብሎ ማሰብ አያስፈልግም ወይ? ይህ ችግር ከላይ ከአነሳሁት የአላማ ወጥነት አለመኖር ጋር ይገናኝ ይሆን?

ጥያቄ ሶስት፡- የሜጫና ቱለማ መሠረታዊ አላማ ልማት ወይስ ፖለቲካ?

ሜጫና ቱለማ ከመሠረቱ እንደልማት አጋር ማሕበር ሆኖ የተቋቋመ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በውስጡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እያስፋፋ እንደመጣም ይነገርለታል፡፡ ይህ ማሕበር የተቋቋመው በተማሩ በተለይም ደግሞ ውጭ አገር ድረስ ሄደው መማር በቻሉ ጭምር መሆኑም ይነገርለታል፡፡ በኋላም ብዙ ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች ተቀላቅለውታል፡፡ በእርግጥስ ሜጫና ቱለማ ከተቋቋመበት መሠረታዊ አላማው ውጭ በሕቡዕ የሄደበት ፖለቲካዊ አላማ ትክክል ነበር? ከአስፈለገስ ከዚህስ በተሻለ ፍትህን ለኦሮሞም ሆነ ለሌላው ለማምጣት አማራጭ አልነበረም?

ጥያቄ አራት፡- ለጀነራል ታደሰ ብሩ በፊት ከነበራቸው ኢትዮጵያዊነት እምነት ወደ ኦሮሞነት ለመቀየር እውንም የወቅቱ ጠ/ሚኒሰቴር አክሊሉ ሀብተወልድ ንግግር ምክነያት ነበር?

እንደሚባለው የወቅቱ ጠ/ሚኒስቴር የሆኑት ለንጉሱ ለምን እነዚህ ኦሮሞዎችን ያስተምራሉ በኋላ በመንግስትዎ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ናቸውና የትምህርት እድል አይሰጣቸው የሚል መንፈስ ያለው ንግግር ነው ጀነራሉን ያሳዘናቸውና ይህ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት ይቅርብኝ ወገኔን ብለው ሜጫና ቱለማን የተቀላቀሉት ይባላል፡፡ ከዛ በፊት ሜጫና ቱለማ ጀነራሉን አባል እንዲሆኑ ሲጠይቃቸው እኔ ብሔርን መሠረት ያደረገ ማህበር አልቀላቀልም ማለታቸውም ይነገራል፡፡ የወቅቱ ጠ/ሚኒሰቴር ንግግር እውነትነትና ውሸትነትም አጨቃጫቂ ነው፡፡ በቅርቡም በሕብር ሬዲዮ ፕ/ር ሕዝቅዬልና አቻምየለህ ባደረጉት ውይይት አንዱ ይሄው ጉዳይ ነው፡፡ አቻም የለም ጠ/ሚኒስቴሩ አላሉም ከነጭርሱም ጀነራል ታደሰ የትምርት ጉዳይ በተነሳበት ስብሰባ አልነበሩም ሲል አለኝ የሚለውን ማስረጃ ተናግሮ ነበር፡፡ እኔ ከጀነራሉ ልጆች ንግግር እንደተረዳሁት ግን ጠ/ሚኒስቴሩ በእርግጥም ኦሮሞን ማስተማር እንደማይገባ እንደተናገሩና ለጀነራሉም ሜጫና ቱለማን መቀላቀል ምክነያት እንደሆነ ነው፡፡ ጉዳዩ በተነሳበት ስብሰባ ጀነራሉ አልነበሩም ማለትም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ከልጆቻቸው ንግግር ጀነራሉ የፊደል ሰራዊትን በዋናነት የሚመሩት ከመሆናቸው አንጻር የትምህርት ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸውና እሳቸው የሌሉበት ትምህርትን የተመለከት ስብሰባ ምን ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፡፡ በዚህ መሠረት እኔ በእርግጥም እንደተባለው ጠ/ሚኒስቴሩ የጀነራሉን ማንነት አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ተናገሩት የተባለውን ንግግር እንደተናገሩና ጀነራሉም በዚሁ ሥብሰባ እንደነበሩ ነው የሚገባኝ፡፡ ሌላም ቦታ የጠ/ሚኒስቴሩን ንግግር ሳደምጥ (ፈልጋችሁ ስሙት) ደጋግመው እኔ ማንንም አልወግንም ይላሉ፡፡ ይህ ንግግራቸው ምን ያለበት ምን አይችልም አይነት ነው የመሰለኝ፡፡ ነጻ ከሆኑ የማንምም ወገን ወክዬ አደለም ብሎ ደጋግሞ መናገርን ምን አመጣመው፡፡ እንደውም ንግግራቸው የሚመስለው ጀነራሉንና ብዙዎችን አስቆጡበት የተባለውን ንግግር ለማስተባበል ነው፡፡ ሌላው አቻምየለህ በወቅቱ የትምህርት ጉዳይ የሚመለከቱና በስብሰባውም የተሳተፉ ግለሰብ የጻፉትን ዋቢ ያደርጋል፡፡ ይሄም አሳማኝ አይሆንም ጸሀፊው እውነቱን ሆን ብለው ላለመደበቃቸው ማስረጃ የለም፡፡ ምክነያቱም ነበር ብሎ መናገሩ በሕዝብ ዘንድ ጥላቻን ያቆያል ከሚል ማስተባበሉን መርጠው ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት የሚከተለውን ጥያቄ ማንሳት መርጫለሁ፡፡

ጥያቄ አምስት፡-ጠ/ሚኒስቴሩ የኦሮሞን ሕዝብ ልጆች መማር ለምን እንደ ሥጋት አዩት?

ከላይ ያነሳሁትን ጠ/ሚኒሰቴሩ አሉ አላሉም ከማለት ሊሉ የሚችሉባቸውን ተጨማሪ አመክንዮዎችን ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ ምን አልባት የሜጫና ቱለማ መሥራቾች በውጭ አገር ሳይቀር የመማር እድል ያገኙና በወቅቱም በልማት ሥም ተቋቁመው ፖለቲካዊ አጀንዳ ማራመዳቸውን መነሻ ተደርጎ ኦሮሞን ማስተማር ብዙ ሜጫና ቱለማን ማፍራት ነው ከሚል ሥጋት ይሆን? ነው ኦሮሞን ከመጥላት?

ጥያቄ ስድስት፡- የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች ቢያንስ ከሜጫና ቱለማ በፊት መገለል ነበረባቸው?

የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች በትምህርትም ሆነ በሥልጣን(ፖለቲከ) ወይም በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በንጉሳውያኑ ዘመን ከሌላው የተሻለ እንጂ ያነሰ እንደልነበረ ብዙ ምስክሮች አሉ፡፡ ራሱን የቻለ ጥያቄ ቢኖረኘም የሚኒሊክ ታሪክ በእኔ አምነት ከእነጭርሱ የኦሮሞ አገዛዝ በሚያስብል መልኩ ከሌላው በሚያይል ሁኔታ የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች መሪነቱን የያዙበት ነው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴም ቢሆን ይበልጠው ሥልጣን በኦሮሞ እንደተያዘ ነው የሚታወቀው፡፡ ሊያውም ዋና ዋና የሚባሉ ሥልጣኖች፡፡ እውንስ ከሜጫና ቱለማ በፊት በማንነቱ ምክነያት የመገለል ሥሜት የሚያድርበት ነበር? ከእነሙሴና ማርታ እንደሰማንው አባታቸው ጀነራል ታደሰ ለንጉሱ በጣም ቅርብ የነበሩና እንደውም የእነ መንግስቱ ነዋይን መፈንቅለ መንግስት ለማምከን ዋናው ሰው እንደነበሩም ነው፡፡ ከዛም በኋላ ጠ/ሚኒሰቴሩ ተናገሩት በተባለው ሊሆን ይችላል ሜጫና ቱለማን እስከተቀላቀሉበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት የኦሮሞነት (በኦሮሞነት መገለላቸው) ሥሜት እንዳልነበራቸው ነው ያስረዱን ልጆቻቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከንጉሱ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት የፈለጉትን ቢጠይቁ እንደሚፈጸምላቸው ነው፡፡ ግን የፊደል ሰራዊትን ለማስፋፋት የጠየቁት ድጋፍ በጎ ምላሽ አልነበረውም፡፡ ለመሆኑ ንጉሱስ ቢሆኑ ኦሮሞን ማስተማር ትክክል አደለም የሚል እምነት ነበራቸው ወይስ የማስተምረው በራሴ ላይ የሚነሳ መሆኑ ያሰጋል ከሚል ፍራቻ ነበራቸው? ንጉሱ እንደሚታወቀው ማንንም ሳይመርጡ ያስተምሩ እንደነበር ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጠረፍ ሳይቀር በተለይም ደግሞ ከቦረና ድረስ እያመጡ በአዳሪ ት/ቤት አስተምረዋቸው ትልቅ ቦታ ያደረሷቸው ብዙዎች ናቸው ይባላል፡፡ ምን አልባትም ውጭ አገር ድረስ ሄዶ ተምሮ በኋላ መፈንቅለ መንግስት ከሞከረባቸው ገርማሜ ነዋይ በኋላ እንደገና በተማሩ የኦሮሞ ተወላጆች የተመሰረተው ሜጫና ቱለማ ከተመሰረተበት አላማ ውጭ በሕቡዕ ፖለቲካዊ አጀንዳን ማራመዱ ንጉሱ ትምህርት ማስተማሩን በጥርጣሬ አይተውት ይሆን? ከመጀመሪያው ጀምሮ ንጉሱ ሥልጣናቸውን እንደሚወዱ (ማን ይጠላል ግን የሳቸው ይበዛል)ብዙ ጠቋሚ  ነገሮች አሉ፡፡ በዛም ምክነያት ብዙ በደሎችን አድርሰዋል፡፡

ጥያቄ ሰባት፡- አሁን ያለው የኦሮሞ ትውልድ ደግሞ ከየትኛውም ሥርዓት የሚኒሊክን ታሪክ ለምን ይጠላል?

እውን ሚኒሊክ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ኦሮሞ በመሆኑ ያደረሱት በደል አለ? ይልቁንስ ሚኒሊክ ዙፋናቸውን ሳይቀር ያወረሱት ለኦሮሞ አደለም?  የአርሲ የሚኒሊክ ጦርነትስ በምን አይነት ምልከታ ነው ኦሮሞ ሁሉ ሚኒሊክን ለመጥላት እንደ ዋና ምክነያት የሚጠቀሰው? በእርግጥስ የአርሲው ጦርነት ኦሮሞን ኢላማ ያደረገ ነበር?
እነዚህ በርከት ያሉ ጥያቄዎች በአንድ ለማጨቅ የፈለኩት የሚኒሊክ ነገር ከተነሳ አይቀር ሁሉም አብረው ስለሚያያዙ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ለእኔ የአሮሞ ሕዝብ ሚኒሊክን የሚጠላበት ምክነያት ሊገባኝ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ሚኒሊክን እንዲጠላ እንደ ዋና ምክነያት የሚቀርበው ከሁሉም በላይ የአኖሌ ጦርነት ነው፡፡ በዛን ጦርነት ብዙ ሕዝብ እንደተሰዋ በተደጋጋሚ በጻፍኳው መጣጥፎቼ ገልጬዋለሁ፡፡ ጦርነቱ ግን ከኦሮሞነት ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ጦርነቱ ሚኒሊክን አገር አንድ አደርጋለሁ ብለው የተነሱበትን አላማ ከማሳካትና ይህንንም ከተቃወማቸው ሁሉ ጋር ጦርነት ከመዋጋታቸው ከእነዚህም አንዱ የአርሲ ሕዝብ ከመሆኑ ያለፈ በኦሮሞነት ደረጃ ሊታሰብ የሚችል አንደም አመክንዮዋዊ እውነታ (ሎጂካል) የለም፡፡ ይልቁንም አኖሌን ታሪክ ጠባሳ በማንሳት ተቀባይነትን ለማግኘት በኋላ የመጡ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ የፈጠሩት ፕሮፓጋንዳ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እነዚሁ ቡድኖች ከአኖሌም በተጨማሪ ከእነጭርሱ ኦሮሞ ከአልሆነው ከሀረሩ አሚር ጋር የተደረገውን የጨለንቆንም ጦርነት የኦሮሞ ነው ሲሉ ገበያ ሲያደርጉት እናያለንና፡፡ በዚህ ረገድ የሚኒሊክን ታሪክ ዛሬ ያለው የኦሮሞ ብዙው ትውልድ የሚጠላው በማይመለከተው ጉዳይ መጥፎ ሆኖ ስለተነገረው እንጂ ሚኒሊክ ለኦሮሞ ሕዝብ ጠላት የሆኑበት አንዳች ምክነያት ኖሮ አይመስልም፡፡

ለመሆኑ ግን ኦነግና መሰሎቹ በኋላም ወያኔ ከዘሩት የጥላቻ መንፈስ በፊት የኦሮሞ ሕዝብ ስለሚኒሊክ ምን ይል ነበር? ስለ ጎበናስ?

ጥያቄ ሰባት፡- የኦሮሞ ሕዝብ ከጊዜ ወደጊዜ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ያለው ግንኙነት ምን እየሆነ ነው?

ይሄን አስመልክቶ በርካታ ጉዳዮችን በቀደሙ መጣጥፎቼ አንስቼያለሁ፡፡ በእኔ ግምነት ከጊዜ ወደጊዜ ጥሩ አልነበረም፡፡ ግን ከጥቂት ወራት በኋላ ጀምሮ ተቀባይነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ለዘመናት በጥላቻ ወሬ ከሌላው እንዲርቅ ሲደረግ ኖሮ ሁሉም እሱን እንደጠላት እንዲያየው ተደርጎ ነበር፡፡ እስካሁንም ይሄንኑ ለሌላው ጥላቻ እንዲኖረው ብዙ የሚሠሩ አሉ፡፡ ሆኖም በቅርብ የመጣው የኦፒዲዮ አመራር መሪውን በማዞር እየሄደበት ከአለው ገደል መልሶ ይሄው ዛሬ ላይ ለሌላውም ተስፋ እንዲሆን እያደረገው እንደሆነ እናያለን፡፡ 50 ምንአልባትም ከዚያም በላይ ያልሰራው የአሮሞ ትግል ጉዳይ በጥቂት ወረቶች (ከመስከረም ወዲህ) ዛሬ ይሄን ያህል ስኬት የስመዘገበበትን ሚስጢር አስተውለናል? ኢትዮጵያዊነት(ከእኔ በላይ ለዚህች አገር የሞተ ማን ነው!)፣ አብሮነት የቀደመ የማንነት ባህሪን ማስታወስና ከሌሎች ጋር አብሮ ለመኖር የተነሳሳበት የፍቅር መንገድ…ና የመሳሰሉት፡፡ ሀምሳና ከዛም በላይ አመት ያልሆነውን ስኬት በእነዚህ ወራቶች ሊያውም ተወዳጅነትንና ክብርን እየጨመረ፡፡  ይህ የእኔ ምልከታ ነው፡፡ ሌላ ነው ምክነያቱ የምትሉ ከአላችሁ ጠቁሙኝ፡፡ ሰሞኑን በቄሮ ላይ የታወጀው ዘመቻ እንዴት አያችሁት?

ጥያቄ ስምንት፡- ለመሆኑ ለኦሮሞም ይሁን ለሌላው ከኢትዮጵያዊነት ቀድሞ የሚመጣ ማንነት ያዋጣዋል?

ሁላችንስ እርስ በእርስ በዘረኝነት መጠላላት መንፈስ የለብንም? እኛስ ዘረኛ ሆነን ሌሎችን ዘረኛ የምንልበት ሞራሉ አለን? ሰሞኑን ትራመፕ የአፍሪካንና የሄይቲን ሰዎች በጥቅሉ የቆሻሻ አገር ሰው ሲል ተደምጦ ብዙዎች የእኛም ሰዎች ወግ አይቀርም ነገር ይሄ ዘረኛ እያሉ ከምራቸው ሲናደዱ አይቼ ተገርሜያለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ የከፋ ዘረኞች ነን፡፡ ሰውን በማንነቱ የምናርድ ዘረኞች፡፡ ለዘመናት ምንም የማያውቁ አማሮች በየቦታው ሲታረዱ አልሰማንም፣ ጋምቤላዎች ሲታረዱ ትንሽ ከውጭ የሰው የሚመስል ድምጽ ተሰማንና ጥቁር ምናምን ብለን ቀልድ አይነት ሀዘን አዘንን፡፡ኦሮሞዎች በመቶዎች ታርደው በመቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ ኦሮሞ ነኝ ብሎ ከሚያስበው ውጭ ለሌላው ብዙም አልተሰማውም፡፡ አንዳንዱ ጭራሽ እነኳን ይለን ነበር፡፡ ትረምፕ አፍሪካኒና ሄይቲን የቆሻሻ አገር ሕዝብ አለ ብለን የትረምፕ ዋና ከሳሾች ሆንን፡፡ ሞራል ማጣት ይልሀል ይሄ ነው፡፡ ትረምፕ በእኔ እምነት እውነቱን ስለሚናገር እንጂ ከሌሎች የተለየ የዘረኝነት አመለካከት አለው ብዬ አላምንም፡፡ እኔ ከክሊንተን ወይም ከኦባማና ተረመፕ ብትሉኝ እውነቱን ለመናገር ትረመፕን እመርጣለሁ፡፡ ሁሉም በአፉ አንጂ ውስጡ ዘረኛ ነው፡፡ እኛ ግን የገዛ ወገናችንን ባዕድ በማድረግ የምንጠላ አልፈንም የምንገድል ዘረኞች ነን፡፡ ዛሬ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ በዘር ተመስርተውባታ ባለች፣ በዘር በተከፋፈለችና በዘራቸው ምክነያት በሺዎች የሚገደሉባት አገር ተወላጆች ሆነን ትረምፕንም ሆነ ሌላውን ዘረኛ የመንቀፍ ሞራላዊ ብቃት የለንም፡፡ አንድ ነገር ግን ይቆጫል! እኛ እርስ በእርስ መናከሳችን ሳያንስ ትረምፕም እንዳለው የቆሻሻ አገር መሆናችን ነው፡፡ ድህነታችን፡፡ ጥቁርነታችን አደለም፡፡ጥቁር ነው የምንለው ኦባማ እኮ በገዛ አገራችን መጥቶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳልቆበት ነው የሄደው፡፡ ሀብታሞችና የበለጸጉ ብንሆን ዘራችንን ፍለጋ ብዙዎች ወደእኛ በመጡ ነበር፡፡ ችግሩ አንድም የጥቁር አገር ለምልክት ሀብታምና የበለጸገ በሌለባት ዓለም ሌሎች በሰሯቸው አገሮችና በሰሩት ስርዓት ስለኖርን እኩል ነን ብሎ ማሰብ ጤነኝነትም አደለም፡፡ ሊፈጥርብን የሚችለው ተጽኖ እጅግ የሚያንገበግብ ቁጭት በሆነ!

በመጨረሻም ሰሞኑንም ኢሳት የተባለው ሚዲያ የደብረጺዮንን የግል ሚስጢር አወጣሁ እያለ ወሬውን ሁሉ  የሞላውን ዜና እንዴ አያችሁት?  ይሄ ምን የሚረባ ሚስጢር ሆኖ ይሆን ለኢሳትና ተከታዮቹ እንደታያቸው? ይሄ እኮ የግለሰብ ጉዳይ ነው፡፡ በይፋም ብዙዎች የወያኔ ባለስልጣናት የሚታወቁበት መገለጫቸው ነው፡፡ ይሄ ሚስጢሩ ተጋለጠ የተባለው ግለሰብ ከጫካ ጀምሮ ሲሰራቸው የነበረውን ወንጀል አንዱንም እንኳን ጠቆመ?  ይልቁንም ኢሳት እንደለመደው ሌላ ውዥንብር በመፍጠር የሕዝብን ትኩረት ለመቀየር ይሆን? ብቻ ይገርማል!
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ