የግብፁ ፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አል ሲሲ የሀገራቸውን የውሃ አቅርቦት እያስጠበቁ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ጋር ያላቸው ሰላማዊ ግንኝነት ዙሪያ አትኩረው እንደሚሰሩ መናገራቸውን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ግብፅ ከሱዳን እና ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር እና በአባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ አለመግባባት ውስጥ መሆኗ ይታወቃል። ግብፅ የውሃ አቅርቦቷ የተመሰረተው ሙሉ በሙሉ አባይ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገሪቱ የውሃ ድርሻ ይጎዳዋል ሲሉ ይናገራሉ። ግብፅ ለረዥም ዓመት አባይን መጠቀም ተፈጥሮአዊ መብቷ እንደሆነ በመጥቀስ በዓለም ትልቁ ወንዝ ላይ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶችን ትቃወም ነበር። ግብፅ ለረዥም ጊዜ የቆየ በማእድን ሃብቱ የታወቀው እና ቀይ ባህር አቅራቢያ በሚገኘው ሀላየብ ትራያንግል ጋር በተያያዘ ከሱዳን ጋር ግጭት ውስጥ ናት። ሁለቱም ሀገራት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን ቦታው በግብፅ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

ባለፈው ግንቦት ወር ሱዳን ከግብፅ የሚገቡ የግብርና እና የእንስሳት ተዋፅኦችን ማገዷ ይታወሳል። በቅርቡም “ለመመካከር” በሚል ሰበብ አምባሳደሯን ከካይሮ ጠርታለች። አል ሲሲ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ወታደራዊ አቅሟን ታጠናክራለች። በተጨማሪም “ይህ ደህንነታችን ነው፤ ሀገራችንን መከላከል የሚችል በቂ ወታደራዊ ሃይል አለን። አሁን የምናገረው ይህንን ሰላም ለማስጠበቅ ነው። በድንበር አካባቢ ያለውን ሁሌም እናጠናክራለን፤ ከማንም ጋር አናብርም በሌላ ሃገር ጉዳይ ጣልቃ አንገባም” ብለዋል። አል ሲሲ መልእክታቸው ለግብፃውያን ቢመስልም “ለኢትዮጵያ እና ሱዳን ወንድሞቻችን ጉዳዩ ግልፅ ይሆንላቸዋል” ብለዋል። የግብፅ ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንት ያለውን የውሃ እጥረት ያስወግዳል ተብሎ የታለመ ከየቤቱ የሚወገዱ ውሃዎችን ለማከም የሚያገለግል ትልቅ የውሃ ማጣሪያ እየገነባች እንደሆነ ይፋ አድርገው ነበር። ባለፈው ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ በአዲስ አበባ በመገኘት ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መነጋገራቸው ይታወቃል። የሃይል ማመንጫ ግድቡ 6000 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የታሰበ ሲሆን ይህም ከስድስት የኒውክሌር ማብላያ ጣበያ ጋር የሚስተካከል ያደርገዋል።

BBC

ግንባታው በ2012 የተጀመረ ሲሆን ግድቡ እስካሁን ድረስ 60% ብቻ መጠናቀቁን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።