የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27 አመታት በፋሽስት ወያኔ አገዛዝ ዘግናኝ የሆነ ጭቆና እየደረሰበት ይገኛል። ለዚህም ዋነኛው መንስኤ እራሱን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር እያለ የሚጠራው ድርጅት አንግቦት የተነሳዉና እያስፈፀመው ያለዉ ብልሹ የፓለቲካ ርዕዮተዓለም ነው:: ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሃይማኖት ከፋፍሎ በግፍ መግዛት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከጥቂት የስርዓቱ ደጋፊዎችና ጥቅመኞች በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያውያን የግፈኛው ስርዓት ተጠቂ ቢሆኑም የአማራው ህዝብ ግን የስርዓቱ ልዩ ኢላማ መሆኑ ይታወቃል::
ወያኔ ከተመሰረበት ጊዜ ጀምሮ ሰፊውን የአማራን ህዝብ እንደ “ጠላት” በመፈረጅ በተደራጀና በተቀነባበረ መልኩ በጅምላ ሲያሳድድ ሲያስር ሲያሰቃይ ሲዘርፍና ሲገድል የኖረ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነዉ።
የወያኔ ስርዓት በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ ከፈፀማቸው በደሎች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መዘርዘር ይቻላል፣
1. የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት ለማፍረስ ብዙ ማስኗል።
2. በሚሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ህዝብ በግፍ ከሀገሩ ውጥቶ እንዲሰደድና ከፊሉ ውሃ በልቶት እንዲጠፋ አድርጓል።
3. የኢትዮጵያን ታሪክ አጉድፏል።
4. የኢትዮጵያ ዳር ድንበር አፋልሶ ህጋዊ ቅርፅ እንዲይዝ አድርጓል።
5. በኢትዮጵያ “ብሔረሰቦች” ስም ብዙ ሸፍጦችን ፈፅሟል።
6. የአማራን ህዝብ በህግ አገር አልባ አድርጓል።
7. አማራ በእናት አገሩ ውስጥ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከማህበራዊና ከፓለቲካዊ መድረኮች ላይ እንዲገለልና ባይተዋር እንዲሆን አድርጓል።
8. አማራው በቀየው ያፈራዉን ሀብትና ንብረቱን ጥሎ እንዲፈናቀልና ከርታታ እንዲሆን አድርጔል።
9. የአማራው ህዝብ ቁጥር እድገት ከሌሎች ተለይቶ እንዲገታና እንዲቀንስ አድርጓል።
10. የተለያዩ የህብረተሰባችን ክፍሎች የአማራዉን ማህበረሰብ በጥርጣሬ እዲያዩ ብዙ መሰሪ ዘመቻዎችን ፈጽሟል።
11. የአማራዉን ህዝብ አኩሪ ታሪክ፣ ሰብዕና እና ባህል ጥላሸት ለመቀባት ብዙ ሞክሯል።
በዚህም ምክንያት የአማራዉ ህዝብ ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመሆን ይህን አስከፊ ፋሽስት ስርአት ለማስወገድና ፍትህና እኩልነት በአገሪቷ ለማስፈን እልህ አስጨራሽ ትግል እያደረገ ይገኛል። እስካሁን ለዚህ ቅዱስ አላማ በርካታ የአማራ ልጆች መስዋዕትነት ከፍለዋል። ብዙዎች ለእስር ተዳርገው መከራ እየተቀበሉ ይገኛሉ። ሌሎች በርካቶች አገር ለቀዉ እንዲሰደዱ ቢገደዱም በውጭ ሆነው ለትግሉ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የተቀረዉ ደግሞ በእናት ሀገሩ ውስጥ ክብሩን ለማስመለስ እየተዋደቀ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ የፓርቲ እና የመንግስትን ሃላፊነት ቀላቅሎ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ “ሁሉንም የ ፖለቲካ እስረኞች እንፈታለን” ብለው መግለጫ ከሰጡና ዜናው በሀገር ቤትና በውጭ መገናኛ ብዙሃን ከተራገበ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ “የፖለቲካ እስረኛ የለም የምንለቀውም አንዳንድ እስረኞችን ብቻ ነው” በማለት የተለምዶ ቅጥፈታቸው ላይ ፀንተዋል። እነሆ አንድም እስረኛ ሳይፈቱ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የወያኔን መሰሪ ምግባርና ፕሮፖጋንዳ ለሚያውቅ ይህ ውሳኔ የሳምንት ወሬና የአማራዉን ፋኖ፣ የኦሮሞን ቄሮና የሌላዉንም የህብረተሰብ ክፍል ከተያያዙት እልህ አስጨራሽ ትግል ለማዘናጋትና ብሎም ስልጣኑን ለማራዘም የጠነሰሰው ስልት መሆኑን ለመረዳት አይከብድም።
በዚህ ወቅት የህሊና እስረኞችን የመፍታት ሂደት ትርጉም የሚኖረዉ ቢያንስ
1. አንዱን ከአንዱ ሳይለይ በይፋ በሚታወቁና በማይታወቁ የማሰቃያ እስር ቤቶች ያሉ የአማራ፣ የኦሮሞና ሌሎችም የመላዉ ኢትዮጵያ ልጆችን በሀይማኖት፣ በፓለቲካ፣ በአሸባሪነት፣ ህገመንግስት በመጣስ፣ ሁከት በመቅስቀስና ሌላም ሌላም ስም እየተሰጣቸው የታሰሩትን ሁሉ ያለ ምንም መድሎና ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣
2. ከእስር የተፈቺዎቹን ሙሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ነፃነት ማክበርና ለደረሰባቸው እንግልት ተጊቢውን ካሳ መክፈል፣
3. በተለይም ንፁሀንን አላግባብ አስሮ መፍታት ውጤት ወይንም እመርታ አለመሆኑን ተገንዝቦ የህዝብን የዲሞክራሲ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መመለስ።
4. አገዛዙ ከቀያቸው ያፈናቀላቸዉን በርካታ የአማራና የሌላም ጎሳ ተወላጆች ወደ ቀደመ እርስታቸዉ እንዲመለሱ ማድረግና፤ ለደረሰባቸዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ተገቢውን ካሳ መስጠት ይገባል።
ከሁሉም በላይ ሌባ የቀማውን ቢመልስ ለጋስ እንደማይባል ሁሉ ንፁሃን ዜጎችን በግፍ አስሮ መፍታት ፍትህ አለምሆኑን ተገንዝቦ የአማራውም ይሁን ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ትግሉን አፋፍሞ መቀጠል ይገባዋል። ይህ ወቅት የአማራና የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ታጋዮች አገዛዙን አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱበት ወቅት ሲሆን አገዛዙ ምንም አይነት መሰረታዊ ማሻሻያ ሳያደርግ ህዝብን ለመሸንገልና ከትግሉ ለማዘናጋት የይስሙላ ጥገናዊ ለውጦች ወደፊት ለማድረግ እንደሚሞክር ይጠበቃል። ሆኖም ጀግናው የአማራ ህዝብና ሌላውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ አገዛዙ በሚያደርጋቸው ጥገናዊ ለውጦች ሳይዘናጋና ፋታ ሳይሰጥ ለዘላቂ ፍትህና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል እንዲቀጥል አምባ ያሳስባል።
በሀገር ዉስጥና በስደት የምትኖር የአማራ ተወላጅ ሁሉ ዛሬ ከመቸውም ጊዜ በላይ የማህበረሰብህና የእናት አገርህ ኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ተገንዝበህ ይዋል ይደር ሳትል ለፍትህ፣ ለዕኩልነትና ማንነትን ለማስከበር የሚያደርገውን ትግል እንድትቀላቀል፣ እንድትደራጅና ለትግሉ የሚያስፈልገውን ማንኛውም እርዳታ እንድታደርግ አምባ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!! ድል ለአማራ ህዝብ!!! ክብር ለአገርና ለህዝብ መስዋዕትነት ለሚከፍለው ትውልድ!!!
አምባ የአማራ ባለሞያዎች ማህበር ዋሽንግተን ዲሲ