ጌታቸው መታፈሪያ

መንደርደሪያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተቀጣጠለና ገንፍሎ የወጣው ህዝባዊ እንቢተኝነት ለዓመታት ታምቆ የቆየው የህዝብ ብሶት ነፀብራቅ ነው። በጣም ረጅም ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ታሪክ ህዝቡ ክፉንም ሆነ ደጉን በአንድነት ሲጋራ የኖረውን፣ ተጋብቶና ተዋልዶ፣ እንዲሁም ባህል ተወራርሶ ያተረፋቸውን እሴቶች የሚያናጋ ሥርዓት በመዘርጋት ኢትዮጵያዊያንን ሆድና ጀርባ እንዲሆኑና እንዲከፋፈሉ ተደርጓል። ኢትዮጵያዊነትና አገር ግንባታ ለዘመናት ሲካሄድ የቆየና ረዥም ታሪክ ያለው ሂደት ነው። ይህም ሂደት በህዝቡ መካከል አንድ ዓይነት ሥነ-ልቦናና እይታ እንዲሠርፅ አድርጎታል። በአንፃሩም እንደማንኛውም አገር ውጣ ውረድ የነበረበትና አሉታዊ ገጽታዎችም የተከሠቱበት ሁኔታዎችም መኖራቸውን መካድ አይቻልም። በመጨረሻም አንድነታቸው እውን ሆኖ የመጡ ወራሪዎችን በጋራ ሆነው መክተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች ሳይሆኑ የወል ስም ያዘለ የኢትዮጵያ ህዝብ ( ህዝበ ኢትዮጵያ) የሚለውን ተላብሰዋል። ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት እንደ እምነትና ፍልስፍና ተወስዶ የጥቁር ህዝብ (በአሜሪካ፣ በካሪቢያን፣ በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ) ለነፃነትና ለእኩልነት ላደረጉት ተጋድሎ የአርነት አርማ አድርገውት ነበር። (ይህንን በተመለከተ የግርጌ ማስታወሻውን ያገናዝቡ። ) በአንድ ወቅት የኤርትራ አዛውንት ተናገሩት የተባለው ልብ የሚያረካ ነበር። ይኽውም “ኢትዮጵያ ለእኛ አገር ሳትሆን ሃይማኖት ነች” አሉ ይባላል። አሁንም ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጋ አመቺ እንድትሆን ለማድረግና ታሪኳን ለማደስ የተዛነፈውን ማቃናት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው። ታሪክ አይካድም። ይህንን መሠረታዊ ግንዛቤ ካስጨበጥኩኝ በኋላ ወደ ቅርብ ጊዜ ክስተቶች ልሂድ።

የቅርብ ጊዜ ክስተቶች የኦርሞ ህብረተሰብ ወጣቶች (ቄሮዎች) የመንግሥትን አምስት ለአንድ (፭/፩) ዓይነ ቁራኛ መረብ ጥሰው ለም የሆነው የመሬታችን ቅርመታ ይቁም፤ የመንግሥት ጭቆና ያብቃ፤ የወያኔ የበላይነት ይክሰም፤ አመርቂ የሆነ የሥራ ዕድል ይከፈት፤ የፖለቲካ፣ የህሊና፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች እሥረኞች ይፈቱ በማለት ገዢው ክፍል ባልጠበቀበት ሁኔታ ገንፍለው ወጡ። ይባስ ብሎም ክልል ዘለል የሆነና አገራዊ እይታ ያነገበ “የአማራ ደም ደማችን ነው” በማለት የአንድነት ቁርኝታቸውን አደሱት። ይህ ለወገን ኩራት ሲሆን እኩይ መንፈስ ለተጠናወታቸው መራር እሬት ነው። ለሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያውያን መካከል የተገነባው የመለያየት ግንብ ተናደ። ንጉሡ ዕርቃኑን ቀረ።

በመሠረቱ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህልና ልማድ ያለን፣ በታሪክ ሂደት፣ በመልከዓ ምድር አቀማመጣችን ፣ ባህል መወራረሳችንና ታሪክ መጋራታችንን በማጎልበት ተሣስረን የኢትዮጵያዊነት ሸማ መላበሳችንን ታሪክ ይመሰክራል። ይህ ነው አገር ግንባታ (Nation building) ማለት:: ይህንን ለረዥም ዘመናት የተሳሰረውን ህዝብ ነው ከፋፍሎና እያዳከሙ ለመግዛት እንዲያመች ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጠባብ ብሔርተኝነት፣ ክልላዊነትና ጭለምተኝነትን ሆን ተብሎ እንዲነግሥ የተደረገው። ለዚህ እንዲያመች አገሪቱን በጎሣ በመሸንሸን፣ የይስሙላ የፌደራል ሥርዓት ተቋቁሞ በአዙሪት በአንድ አካባቢ ሰዎችና በሸሪኮቻቸው መዳፍና ቁጥጥር ሥር አገሪቷ ወደቀች። ሲናገሩት ቀልብ የሚስብ ነፃ ዲሞክራሲ ሰፈነ ተብሎ ኢዲሞክራሲያዊ ወይም ባዶ ዲሞክራሲ (Illiberal democracy) ሥር የሰደደበት፣ ሹማምንት ከተጠያቂነት ያመለጡበትና፣ የመናገር፣ የመጻፍና ህዝባዊ ነፃ ድርጅቶች የታፈኑበት ሥርዓት ተፈጠረ። ልቅ የሆነ የኤኮኖሚ ሥርዓት (Neo liberal) ተዘረጋ ተብሎ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት፣ የአገር መከላከያ፣የፀጥታ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶችን የመሳሰሉት በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ወደቁ። ከነአካቴው በገዢው ፓርቲ ቁንጮ (ህወሃት)ና በመንግሥት መካከል መኖር የሚገባው ልዩነት ፈጽሞ ጠፋ። ስለሆነም ህወሃት/ ኢህአደግ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ህወሃት / ኢህአደግ ሆነ። ባጠቃላይ መንግሥት የገዢው ፓርቲ ይዞታ ሆነ።

ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ተደማምረው ባጠቃላይ ውጤታቸው የሰብዓዊ መብቶች መደፈር፣ ያለአግባብ ብልጽግናና የሃብት ዘረፋ እሽቅድምድም፣ የአገር ልዑላዊነት መደፈር፣ የህዝብ የኑሮ ሁኔታ ማሽቆልቆልና መቆርቆዝ፣ የአካባቢ ሃብት መዘረፍና መራቆት ሥር እንዲሠድ ተደረገ። ሆኖም ግን ውሎ ቢያድርም መንግሥት በህግና በታሪክ ከመጠየቅ አይድንም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ ዕጣና ዕድል ተረካቢዎች በመሆናቸው ከወዲሁ አገራዊና ህዝባዊ ራዕይና ጥያቄዎችን አንግበው የተነሱት። ይህ ተገቢ ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅባቸው የዜግነት ግዴታቸው ነው። መንግሥት ለጥያቄያቸው በፍጥነትና በአግባቡ መልስ ካልሰጣቸው አማራጭ የሆነው በአደባባይ ወጥቶ ጩኽታቸውን ማሰማት ነው። ጎሣ ሳይለያያቸው ኢትዮጵያዊነትን አንግበው ለአገራቸው፣ ለነፃነታቸውና ለክብራቸው የተዋደቁት የቀድሞው ትውልድ ደም ከያለበት እየጮኸ ነው። ስለዚህ በወቅቱ መድረስና አገርን ማዳን ከሁሉም የሚጠበቅ ቅዱስ ተግባር ነው። እንግዲህ የአገራችን የቅርብ ጊዜ ክስተቶችና ባጠቃላይ ግንዛቤው ይህን ይመስላል።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ምን ይጠበቃል ? ከኢህአድግ/ህወሃት ከእንግዲህ ወዲያ እውነተኛ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ግልጽነትና የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም እኩልነት ይመጣል ብሎ መጠየቅ ቀቢፀ ተስፋ ከመሆኑም ባሻገር ላም ባልዋለበት ኩበት ለመልቀም በከንቱ መባዘን ይሆናል። ለጥያቄያቸው ምልስ ውሎ በማደሩ የህዝቡ ምሬትና ጥያቄ አሁን የሥርዓት ተሃድሶና ጥገና ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ ነው። ቁም ነገሩ ህወሃት/ ኢህአደግ ለዚህ መዘጋጀቱ ላይ ነው። ያለወትሮው የፖለቲካ እሥረኞችን ለቅቄ ማዕከላዊ እሥር ቤትን ሙዚየም አደርገዋለሁ በማለት የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። በመሠረቱ በተለያዩ እሥር ቤቶች ታጉረው ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸው ዕንቁ የሀገር ልጆች በሞላ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መፈታት አለባቸው። ይህን ለማድረግ ግን የሞራል ብቃት ያለው ሆደ ሠፊና ይቅር ባይ፤ (Magnanimous) በህግ የበላይነት፣ በህዝብ እኩልነት፣ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በግልፃዊነትና በተጠያቂነት የሚያምን መንግሥት መኖር አለበት። እነኝህን ፀጋዎች የኢትዮጵያ መንግሥት ተላብሷል ማለት በፍጹም አይቻልም። ስለዚህ ነው በወቅቱ የተነገረው የፖለቲካ እሥረኞችን የመፍታት ሁኔታ በጉም የተሸፈነ ወይም እውን ሊሆን ያልቻለው። የተሰጠው ተስፋ እንደወትሮው ከቃላት ጋጋታ አላለፈም። የዘገየ ፍርድ እንደተነፈገ ፍርድ ይቆጠራል።

ይህን በተመለከተ ከእሥር ቤቱ የፖለቲካ እሥረኞች ተፈተው በቦታቸው ግፍ ፈጻሚዎች ይተኩበታል የሚሉ ከምሬታቸው ብዛት የሚናገሩ አልጠፉም። ማንም ሰው ሃሳቡን የመግለጽ መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም ነገርግን በድህረ ኢህአደግ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የሠፈነባትና ቂም በቀል ወይም የጥላቻ ሥርዓት ቦታ እንደሌለው ማድረግ ይጠበቃል። ሆኖም ግን ማንም ሰው (በተለይ ባለሥልጣናት) ለድርጊታቸው ሁሉ ከተጠያቂነት ማምለጥ መቻል የለባቸውም። በደፈናው ግን ዓይን ያጠፋ ዓይኑ መጥፋት አለበት የሚል የቂም በቀል ህገ ሥርዓት ሊገዛና ቦታ ሊሰጠው አያስፈልግም ። ለዚህ ነው የሰላም ተሟጋች ማኅተመ ጋንዲ “ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ ካልን ዓለም በሞላ ዓይነስውር ይሆናል” ያለው።

በተለይ አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ የአገራችን ጋንዲ፣ ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተር እና ሌሎችም የሰላም፣ የዕርቅ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርቡ መሪዎች ከማንኛውም ጊዜ የበለጠ ዛሬ ያስፈልጉናል። መልሱን አንጋጠን ከመንግሥት የምንጠብቀው ሳይሆን መልሱ የሚገኘው ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።

ማጠቃለያ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን ልብ ብንል ኢትዮጵያ የሥርዓተ መንግሥታት ቤተ ሙከራ ሆናለች ለማለት ይቻላል። የአፄዎች (ሞናርኪ) ፣ ወታደራዊ መንግሥት ሆኖ የሶሻሊስት ሥርዓት አቀንቃኝና አሁን ደግሞ የሪፑብሊክ (የህዝብ የበላይነት የተረጋገጠበት) የሚል ጎሣን ማዕከል ያደረገና የሊብራል ኤኮኖሚን ሥርዓት አራምዳለሁ የሚል ሦስት መንግሥታት ተፈራርቀውባታል። ወደፊት በረቀቀ ሁኔታ ታሪካችንን፣ ትሥሥራችንን፣ የህዝባችንን መብቶችና የአገራችንን ልዑላዊነት በመሳሰሉት ላይ ያተኮረ ሥርዓተ መንግሥት ለመተለም ብቁ ተመክሮ አለን። ካለፉት ሁለቱና ከአሁኑ ሥርዓተ መንግሥታት የምንማረውና፣ የምናዳብረው እንዲሁም የምናስወግደው አሉን። የጊዜውንና የመጪውን ሁኔታዎች ያገናዘበ፤ የአካባቢያችንንና (geopoltical) የዓለም ፖለቲካ ሂደትን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለአገራችንና ለህዝባችን ተባብረንና ተመካክረን ከታች ወደላይ የሚፈልቅ ሥርዓት ለመቀየስ የሚችሉ ብዙ ዜጎች አሉን። እነዚህም ተመክሮ ያካበቱ ፣ ዕድሜ ጠገብ አዛውንቶችና እንሆ አሁን ትኩስና አዲስ ኃይል የሆኑ ወጣቶች አገራችን በብዛት አሏት። ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት

ዕድሏን ለመቀየስ ሁሉም የተሳተፉበት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህዝባዊና ሰብዓዊ ድርጅቶች ተመክሮአቸውንና በህዝቡ ውስጥ የዘረጉትን የግንኙነት መረብ በመጠቀም አገር ለማዳንና ህዝብን ለመታደግ በተቀናጀ መልኩ መረባረብ ወቅቱ፣ ጊዜውና ሰዓቱ አሁን ነው። ሁኔታዎች መልካቸውን ቀያይረው አገር ወደ ባሰ ማጥ ውስጥ እንዳትገባ በአንድ ላይ መረባረብና ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን የመፍትሔ አካል መሆን አሁን ነው። ከዚያ በኋላ የፖለቲካው ይዘት ፣ የሥርዓት መዘርጋት፣ ሰላም፣ እርቅና የሥልጣን ሽግግር ውይይት ውሎ የሚያድር አይደለም። ወትሮውን እንደሚባለው “እኛው ካልሠራነው ማንስ ሊሠራልን ነው፣ ዛሬስ ካልሆነ መቼ ሊሆን ነው። ” በመጨረሻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመቀራረብና እጅ ለእጅ በመያያዝ የአገር መልሶ ግንባታ መሠረት መጣል ይጠበቅበታል። በየአቅጣጫው ፈንቅሎ የወጣውን ኃይል ማቀነባበርና ለአመርቂ ውጤት አቅጣጫ ለመቀየስ ሁላችንንም የሰሎሞንን ጥበብ ያድለን፣ ያጎናፅፈን።

ኃይል ለህዝባችን፤ አንድነት ለኢትዮጵያችን:: _____________________________________________ የግርጌ ማስታወሻ 1. ጌታቸው መታፈሪያ “ Ethiopian and Ethiopianism in the Pan African Movement” Africa and the World, Vol.1.No 4, July 1988 2.

ጌታቸው መታፈሪያ “ The Ethiopian Connection to the Pan African Movement,” Journal of Third World Studies, Vol. XII, No.2, Fall 1995.