በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ጠንከር ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተደረጉ፡፡ ዛሬ ሐሙስ ጥር 10 ቀን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ፣ የህወሓት አገዛዝ ሲብጠለጠል እና ሲወገዝ ውሏል፡፡ በተለይ በአምቦ እና በነቀምት ከተሞች በተካሄዱት ህዝባዊ ሰልፎች፣ ‹‹ዳውን ዳውን ወያኔ!›› የሚሉ መፈክሮች የተስተጋቡ ሲሆን፤ በተጨማሪም ‹‹ቻው ቻው ወያኔ!›› የሚሉ የተቃውሞ ደምጾችም ተደምጠዋል፡፡ በሺህ የሚቆጠር ህዝብ በተገኘባቸው በእነዚህ ሰልፎች፤ ህዝቡ የህወሓትን አገዛዛ እንደማይፈልግ ዳግም አረጋግጧል፡፡

በዛሬው ዕለት ሲከበር የነበረውን የከተራ (ጥምቀት) በዓል ማብቃቱን ተከትሎ፣ ህዝቡ የተቃውሞ ድምጾችን ማሰማት እንደጀመረ የገለጹት የዓይን እማኞች፤ ህወሓትን በጽኑ የሚቃወመው ህዝባዊ ሰልፍ የተካሄደውም ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ለጥምቀት በዓል የወጡ ታቦቶች ወደ ማደሪያቸው ከገቡ በኋላ መሆኑን እማኞቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ ይህም የህዘቡን ጨዋነት እንደሚያሳይ የተናገሩት እነዚሁ እማኞች፤ ሁኔታው ህዝቡ ምን ያህል ሰላማዊ ትግል እንደሚያካሂድ እንዳስገነዘባቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ህዝቡ የተከተለው ጨዋነት ለስርዓቱ የፈጠራ ክስ የማይመች ሆኖ መገኘቱንም ከእማኞች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በነቀምት ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ፤ ከትንሽ እስከ ትልቅ የህወሓትን አገዛዝ አምርሮ እንደሚጠየፍ አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም፤ በአምቦ ከተማ በተካሄደው ጸረ-ህወሓት ሰልፍ፣ የተለያዩ መፈክሮች የተደመጡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የመፈክሮቹ ይዘትም አገዛዙ ስልጣኑን እንዲለቅ የሚጠይቁ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ በሁለቱም ከተሞች በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ፣ ህዝቡ ትላንት ከእስር ለተፈቱት ዶ/ር መረራ ጉዲና ያለውን አጋርነት እና አክብሮት መግለጹን የዓይን እማኞች ገለጻ ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታም፤ በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ወልድያ ከተማ ህዝባዊ ተቃውሞ መካሄዱ ታውቋል፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ የተካሄደው ከጥምቀት በዓል አከባበር በኋላ መሆኑን የገለጹት መረጃዎች፤ ሰልፉ በኦሮሚያ ክልል እንደተደረገው ሁሉ፣ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ-ህወሓት ስልጣን እንዲለቅ የተጠየቀበት ነበር፡፡ በሰልፉ ላይ ከተደመጡ ህዝባዊ መፈክሮች መካከል፡- ‹‹ወያኔን በለው! ወያኔ ሌባ›› የሚሉት እንደሚገኙበት መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ዛሬ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች፤ አገዛዙ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ቢሊም ባይልም፤ ቢፈታም ባይፈታም ህዝባዊ ትግሉ እንደማይቋረጥ አረጋግጠዋል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

 

BBN Daily Ethiopian News January 17, 2018