የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ የተቀዋሚ ፓርቲ መሪውን ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞችን መልቀቋን አደነቀ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሁኔታ ዳግም አጢኖ እንዲለቅ ጠይቋል፡፡

Merara Gudina Vorstizender der OPC (Getty Images/AFP/E. Goujon)

የመንግሥታቱ ድርጅት በዛሬው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት የጸረ-ሽብር ሕጉን እንዲያላላ፤ በመብት ተሟጋቾች እና በመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃም እንዲያቆም አሳስቧል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቃል ቃል አቃባይ ሊዝ ትሮሴል፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን የጀመረውን አበረታች እርምጃ በመቀጠል በፖለቲካ አመለካከታቸው እና እምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ሌሎች ሰዎችን እንዲለቅቅ እናሳስባለን” ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ በወሳኝ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ እናስባለን፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለመርዳት ዝግጁ ነው ነን የምንለው፤” ሲሉ ቃል አቃባይዋ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አክለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዉስጥ አሁን በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር እንደሌላቸው ነገር ግን በሺህዎች እንደሚቆጠሩ ጠቁመዋል፡፡ “ባለመረጋጋቱ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ታስረው እንደነበር የሚያሳዩ ዘገባዎች አሉን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ተለቅቀዋል ነገር ግን አሁንም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ ሰዎች በእስር ላይ እንዳሉ እናምናለን” ሲሉም አክለዋል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት በመጀመሪያው ዙር በጥቅሉ 528 እስረኞችን እንደሚለቀቅ አስታውቀው ነበር፡፡ ይቅርታ የመስጠቱ እና ክስ የማቋረጡ ሂደት ለሁለት ወር ያህል እንደሚቀጥል መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የጸረ-ሽብር ሕጉን እንደገና እንዲከለስም የጠየቁት ቃል አቃባይዋ፤ ሕጉ “ለትርጉምም ሆነ ለአተገባበር ሰፊ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ውሎ ሰዎች በስህተት ወይም በዘፈቀደ ለእስር እንዳይዳረጉ እንዲያረጋግጥም፤” አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና የመገናኛ ብዙሃን ሥራ ላይ ገደብ የሚጥሉ ሕጎቹን ሊያሻሽል ይገባዋል ማለታቸዉን የሮይተርስ ዘገባ ዘርዝሯል።

ተስፋለም ወልደየስ
ሸዋዬ ለገሠ

Source    –   DW