በኢትዯጵያ ከረሀብና ግጭት ጋር በተያያዘ በአሁኑ አመት ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችትምህርታቸውን የማቋረጥ አደጋ ላይ እንደሆኑ ዓለም አቀፉ የህፃናት ድርጅት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የአለም አቀፉ ህፃን ድርጅት የሀገሪቱ ዳይሬክተር ኤኪን ኦጉቶጉላሪ እስካሁን ባለው ሁኔታም ወደ አራት መቶ ሺ የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንደተፈናቀሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር መረጃን ጠቁመው እንደተናገሩትም ከየካቲት 2009 ጀምሮ 623 ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ይህም በየወሩ የሚዘጉ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር 51 ያደርሰዋል።

ይህ ድርቅም ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እንዲሁም ኬንያ 90 ሺ ያህል ልጆች በየሳምንቱ ከትምህርት ገበታቸውም የመፈናቀል አደጋ ላይ እንደሆኑ ዓለም አቀፉ የህፃናት ድርጅት ሰሞኑን ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

ይህ ቁጥርም በዓመቱ 4.7 ሚሊዮን ያህል ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ ያስረዳል።

ልጆቹ ከትምህርት ቤት ውጭ ሲሆኑ ለተጓዳኝ ችግሮች እነዚህም ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ህገ-ወጥ የሕፃናት ዝውውር እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዮች ተጋላጭ እንደሆኑ ሪፖርቱ የገለፀ ሲሆን በአስደንጋጭም ሁኔታ እስከ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ህፃናት ጀምሮ በአካባቢው ባሉ ወታደሮች እየተመለመሉም እንደሆነምሪፖርቱ ጨምሮ ያስረዳል።

ህፃናት በድርቁም ሆነ በረሀቡ በክፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዱ የሚናገሩት ኤኪን ” ምንም ሆነ ምንም ትምህርት ቤቶቹ የማይዘጉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፤ ይህም ልጆቹንም በአንድ ቦታ ላይ በማድረግ መርዳት የሚፈልጉ ድርጅቶች እንዲረዱ እንዲሁም ከሚደርስባቸው ጥቃቶችም ለመከላከል ያስችላል” ይላሉ።

የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የአለም አቀፉ ህፃናት አድን ድርጅት ተወካይ ዴቪድ ራይት ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ ገልፀዋል።

” በየቀኑ 12ሺ የሚሆነ ተማሪዎች በየዓመቱ የትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙ ከሆነ በዚህ ቀጠና የሚገኙ ቀጣዩ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ከፍተኛ አደጋ ላይ ይወድቃል። ማንኛውም ልጅ ቢሆን ከትምህርት ገበታው መፈናቀል የበትም፤ የመማር መብታቸውም ሊጠበቅላቸው ይገባል። በድርቅም ሆነ በረሀብ ጊዜ ትምህርት ቤቶቹን ክፍት ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው ምክንያቱም ትምህርት ቤቶቹ ምግብ፣ ውሀም ይሁን ክትባትም ማቅረብ አለባቸውም” ብለዋል።

የዓለም አቀፉ ሕፃናት አድን ድርጅትም በዚህ አመት የያዘውም ዕቅድ ትምህርት ቤታቸውን ሳይለቁ እንደተጠበቁ ቤተሰቦቻቸው እንደገና መልሰው የሚያገግሙበትና ለወደፊቱም የሚያቅዱበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሆነም ሪፖርቱ ያትታል።

የውሃ እንዲሁም የክትባት አቅርቦት ወይም ዘመቻዎች አደገኛ የሆኑ ወረርሽኞችን እንደ ኮሌራ ያሉትን ለመካከል ያስችላል ያለው ሪፖርቱ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ልጆችም ባሉባቸው መጠለያዎች ዛፍም ስር ቢሆን የተለያዩ ትምህርቶችን ሊወስዱ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ይገኙበታል።

በአጠቃላይ በክልሉ 21 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በምግብ እጥረት እየተሰቃዩም እንደሆነ ሪፖርቱ ጨምሮ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ቆላማውን ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃው ይህ ረሀብ በታሪክም ክፉ የሚባል ረሀብ እንደሆነ ኤኪን ይገልፃሉ።

“በጣም አደገኛና ከ1970ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያ አስተናግዳው የማታውቀው ክፉ ረሀብም ነው” ይላሉ።

ይህ ረሀብም የቀጠለ ሲሆን በዚህ ዓመትም ያለው ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

በተከታታይም የዝናብ ዕጥረት በማጋጠሙ ረሀቡ ሊቀጥል እንደቻለም አሁንም የአየር ሁኔታ ትንበያዎች ዕጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ኤኪን ለቢቢሲ ፍራቻቸውን ገልፀዋል።

“ይሄ ማለት የድርቁም ሆነ የረሀቡ ሁኔታ በቆላማው የኢትዮጵያ ክፍል እንደሚቀጥል ነው”ይላሉ።

በምላሹም ድርጅቱ ልጆችን የመመገብ ፕሮግራም እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁሶችን የለገሱ ሲሆን በዚህም 11ሺ የሚሆኑ ህፃናትም ተጠቃሚ እንደሆኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ልጆቹንም በየአመቱ ትምህርት ቤት ለመመለስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልፀው በአጠቃላይ ግን ለኢትዮጵያ ድርቅና ረሀብ ከለጋሾች የሚሰጠው ምላሽ እያሽቆለቆለ መሆኑንም ይገልፃሉ።

የድርጅቱን ምሳሌም በማንሳት ከሁለት ዓመታት በፊት መቶ ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን በተሰጠው ምላሽ አምስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ይገልፃሉ።

“ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ ናት። ረሀቡን ለመቋቋም እየታገለች ነው፤ በዚህም ወቅት ኢትዮጵያ መደገፍ አለባት” ይላሉ።