የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (መካነ ትምህርት) ሴት ተማሪዎች የሚንቀሳቀሱበት እራሳቸውን yellow movements ሲሉ የሚጠሩ ሴቶች ላይ አተኩሮ የሚሠራ ንቅናቄ አለ፡፡ የሚሠሩት እዚህ ሀገር ውስጥ እንደመሆኑና እንሠራለታለን የሚሉት ማኅበረሰብም ለኢትዮጵያውያን እንደመሆኑ ቢጫ ንቅናቄ ማለት እየቸሉ ለምን የእንግሊዝኛ ሥያሜ በመምረጥ yellow movements ሲሉ ለራሳቸው ሥያሜ እንዳወጡ እራሳቹህን እየጠየቃቹህ ቆዩኝ ወደኋላ ግልጽ የሚሆንላቹህ ነገር አለ፡፡

እነኝህ ሰዎች ችግረኛ ሴት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለመርጃ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴ ለመፍጠር!” በሚል በፍቅረኛሞች ቀን (በቫላንታይንስ ዴይ) በኤምባሲዎችና ሆቴሎች እየተገኙ አበባ በመሸጥ በምናገኘው ትርፍ እንረዳለን!” ብለው ተነሥተው ሲንቀሳቀሱ ስሰማ ቅን አስተሳሰባቸውን በማድነቅ ነገር ግን ይሄ ፈጽሞ ኃላፊነት የሚባል ነገር በማይሰማቸው ከርሳምና ደናቁርት ነጋዴዎችና የሬዲዮና የቴሌቪዥን (የነጋሪተ ወግና የምርዓየ ሁነት) የመዝናኛ ዝግጅቶች አዘጋጆች እየተራገበ ያለው የፍቅረኛሞች ቀን የሚባለው የምዕራባውያኑ በዓል ለአቅመ ሔዋንና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ተማሪዎቻችንን ዕድሜያቸውና ሌሎች ሁኔታዎች ሳይፈቅዱላቸው ወደ ወሲብ እንዲገቡ በማድረግ ሕይዎታቸው እንዲበላሽና ሕልማቸው እንዲጨነግፍ ከፍተኛ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑ፣ በዓሉ እንደ የዝሙት ቀን ተቆጥሮ ኅብረተሰባችን ለብዙ ዓይነት ችግሮች እየተዳረገበት በመሆኑ፣ ለርካሽ ባሕል ወረራ ሰለባ ስላደረገን ወዘተረፈ. በርካታ ዓይነት ጣጣዎችን እያመጣብን በመሆኑ መልካም ለመሥራት ሲሉ ይሄንን በዓል ሲጠቀሙ በሀገርና በኅብረተሰቡ ላይ ጠንቅ ለሚፈጥረው ለዚህ መጤ በዓልና ለሚያደርሳቸው ጉዳቶች መስፋፋት ሳያውቁት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ስለሚያደርጋቸው በዚህ ቀን አበባ ሸጠው አገኘን ከሚሉት አነስተኛ ገቢ ይልቅ ብዙ ጊዜ እጥፍ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉባቸውን የሚከተሉትን የገቢ ማግኛ መንገዶች በመጠቆም፦

* አዲስ ዓመትን ወይም እንቁጣጣሽን ጨምሮ በበዓላት ቀን ወደ ታላላቅና ታዋቂ ሰዎች ቤቶች በመሔድና የ እንኳን አደረሳቹህ!” የመልካም ምኞት መግለጫ አበባ በማበርከት እንኳን አደረሳቹህ!” እያሉ ቢጎበኙ ቢጠይቁ፡፡

* በታላቁ ሩጫ እና መሰል ዝግጅቶች ላይ ለታዳሚው የመዓድን ውኃ አቅርበው ቢሸጡ፡፡

* የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ምርቃት በሚሆንበት ቀን ለተመራቂዎች የሚበረከቱ አበቦችን ቢሸጡ፡፡

እያልኩ ጠቃቅሸ ሕዝቡ ዓላማቸውን ስለሚያውቅና ስለሚረዳ አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ተጨማሪ ልገሳዎችን በተጨማሪ እንዲያገኙ ስለሚያደርጋቸው ጠቀም ያለ ገቢ በማግኘት ዓላማቸው ግቡን እንዲመታ ሊያደርግላቸው እንደሚችል በመግለጥ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት አይ አንፈልግም የፍቅረኛሞች ቀንን ነው የምንጠቀመው!” ያሉ እንደሆነ ግን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመግለጥ ችግር እንፈታለን ብለው የባሰውኑ አሳሳቢ ችግር ውስጥ ሊከቱን ስለሚችሉ እንዲታረሙ ምክርና አስተያየት ለግሸ ይሄንን የፍቅረኛሞች ቀንየሚባለውን እንዲተውት ቢጫ ንቅናቄዎች yellow movements ችግር አቅላይ ወይስ ችግር ፈጣሪ?” http://www.satenaw.com/amharic/ቢጫንቅናቄዎች-yellow-movements-ችግርአቅላይወይስ/ በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ አሳስቤ ነበር፡፡

እነሱ ለካ ዓላማቸው ሰውን መርዳት ሳይሆን ትውልድን ማጥፋት ኖሯል ለካ እዚያ ጽሑፍ ላይ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ግምት ውስጥ እንዲያስገቧቸው ለጠቃቀስኳቸው አሳሳቢ ችግሮች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ይሄው ዘንድሮም ገቢ በማሰባሰብ ሽፋን የተለመደ ነውረኛና ጸያፍ ተግባራቸውን ለመፈጸም ዝግጅታቸውን እያጧጧፉት ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ባደረስኳቸው ጽሑፍ ላይ እንዲጠቀሙበት ያቀረብኩላቸውን አዋጪ አማራጮችና ኃላፊነት እንደሚሰማው ፊደል የቆጠረ ዜጋ ግምት ውስጥ እንዲያስገቧቸው ያሳሰብኳቸውን አሳሳቢ ነጥቦች እንዴት ሳይቀበሉ ሊያልፉ እንደቻሉ በጣም ቢገርመኝ ምክንያቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመመርመር በሚል ስለነሱ መጠነኛ ምርመራ አድርጌ ነበረ፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እነኝህን ሰዎች ከዚህ በዓልና ከደንበኞቻቸው ጋር ያቆራኛቸው የተደበቀው ምክንያት እጅግ ለጆሮ የሚከብድ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

እንደሰማሁት በዚህ የሴቶች ንቅናቄ ውስጥ ያሉ ሴቶች አብዛኞቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በደላሎች አማካኝነት ከውጭ ዜጎች ጋር የወሲብ ንግድ በመፈጸም የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይሄንን በዓልም አበባ ለመሸጥ በሚል ሽፋን በየኢምባሲውና ታላላቅ ሆቴሎች እየተገኙ በተለይ ከውጭ ዜጎች ጋር ለመጣበሻ ለመቀለጣጠፊያ ተግባር እንደሚያውሉት ነው የሰማሁት፡፡

የሚያሰማሯቸው አለቆቻቸው ደግሞ መንግሥታዊ ባልሆኑ የውጭ ድርጅቶች (NGO’s) ላይ ዘመዶቻቸውን ለማስገባት ከኢምባሲዎች ጋር የመግባቢያ መንገድ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ነው የሰማሁት፡፡ አይገረሙም? ምን ዓይነት ሰዎች ቢሆኑ ነው ችግረኛ ሴት ተማሪዎችን ለመርዳት!” የሚል ምክንያት ወይም ሽፋን ፈጥረው ሲያበቁ እንዴት እንደተጠቀሙባቸው አያቹህ??? ሰው የዚህን ያህል ይሉኝታውንና ምን ይሉኝ ማለትን ጥሏል???

ታዲያ እነዚህማ እንዴት ነው ሊሰሙና ሊገነዘቡስ የሚችሉት??? ለካ ለዚህ ኖሯል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የክርክር መድረኮችን እያዘጋጁ የሀገራችን ሕግ ወንጀል ነው!” ያለውን ሕግ በመተላለፍና ዜጎች እንዳያከብሩት በመገፋፋት ሴት ልጅ እንደፈለገች መልበስ መብቷ ነው! ይሄ መብቷ መከበር አለበት! አለባበሷ ለመጠቃት ምክንያት ሊሆን አይገባም!” ምንትስ ምንትስ እያሉ ሴት ተማሪዎች የተራቆተና ከሥርዓት ከወግ ከባሕል የወጣ አለባበስ እንዲጠቀሙ ለማድረግና ለመበከል ጥረት ያደርጉ የነበሩት፡፡ የሀገራችን ሕግ ወሲባዊ ስሜትን የሚቀሰቅስ አለባበስን በአደባባይ፣ በትምህርት ተቋማት፣ ሕዝብ በሚሰባሰብባቸው ቦታዎች መጠቀም በሕግ የሚያስቀጣ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው!” ይላል፡፡

እነኝህ ሰዎች ግን ድብቅ ነውረኛና ጸያፍ ዓላማቸውን ለማሳካት እንዲያመቻቸው እንዲህ እያሉ ተማሪውን ሲሰብኩት ቆዩ፡፡ ይህ አሳሳች ስብከታቸው በብዙኃን መገናኛዎች ሳይቀር ተላልፏል፡፡ ዘንድሮማ ጭራሽ እንዲያውም በስልክ ጥሪ ቢደረግላቸው አበባውንከተፈለገው ቦታ ድረስ በማድረስ ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት እንደተዘጋጁ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በእውነት እጅግ በጣም ጸያፍ አሳፋሪና ነውረኛ ተግባር ነው እየተፈጸመ ያለው፡፡ እዚህ ዘመን ላይ እንድረስ? መንግሥት እንኳ የለንም ሕዝቡ ግን ይሄንን አሳፋሪ፣ አዋራጅ፣ የሀገርንና የኅብረተሰባችንን ገጽታ የሚያበላሽ፣ እሴት የሚያጎድፍ ነውረኛ ተግባር በዝምታ መመልከት አለበት ወይ??? እነኝህ ሰዎች ብዙ እኅቶቻችንን ሳይበክሉ፣ የቅጥረኝነታቸውን ግብ አሳክተው ለርካሽ ባሕል ወረራ ሰለባ ሳያደርጉንና ለማኅበራዊ ቀውስ ሳይዳርጉን በፊት ከወዲሁ ልናስቆማቸው ይገባል!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com