ላለፉት 27 ዓመታት በአገራችንና በሕዝቡ ላይ የደረሰውን መከራና ግፍ በመሪነት ያቀነባበረና የሚመራ ወያኔ የተባለው የባንዳዎች ጥርቅም ሲሆን ፣የሱ ካባ፣መከታና  ጭፍራ በመሆን በክልል ደረጃ ተሰልፈው ተባባሪ የሆኑት ሁሉም የኢሕአዴግ ተብዬው ስብስብ አባላት የሆኑት የደቡብ ሕዝቦች ፣የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት(ኦሕዴድ)፣የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ብአዴን)  በመባል የተፈለፈሉት ድርጅቶችም  ጭምር እንደሆኑ መረሳት የለበትም።የሁሉም የጥምቀት ስማቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚል ሲሆን፣ የጥምቀት አባታቸው ወያኔ ነው።አንድም አራትም በመሆን እንደአባትና ልጅ እጅ ለእጅ ተያይዘው  በደል ሲፈጽሙ የኖሩና በመፈጸም ላይ ያሉ  የጥፋት ቤተሰቦች ፣በዘረፋ ሰንሰለት የተሳሰሩ የሌባ  ስብስቦች ናቸው።

የከባቢያቸውንና በስሙ የተቋቋሙበትን ሕዝብ ከፊት ለፊት የሚያስጠቁትና የሚያጠቁት፣የቅርብ ጠላቶቹ እነዚሁ የወያኔ ፈረስ የሆኑት ድርጅቶች ናቸው።ባይሆኑማ ኖሮ በከባቢያቸው የሚኖረውና በስሙ የሚነግዱበት ዜጋ በወያኔ ጥይት ሲረፈረፍ፣ሲቆስል፣ሲታሰር፣ሲሰደድና ሲፈናቀል ለምን ብለው ከሕዝባቸው ጎን በመሰለፍ በተከላከሉለትና መብቱን ባስከበሩለት ነበር።የእነሱ ተግባር ግን በቅርቡ የሚያጠቁና የሚያስጠቁ ፣አደንዛዥና ጠቋሚ የባንዳዎች ባንዳ ናቸው።በህብረት ያቋቋሙት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሃይሉም በወያኔ የአጋዚ ጦር የሚሽከረከርና  ተባባሪ በመሆን በሕዝቡ ላይ የሚዘምት፣ወታደራዊ ግፍ የሚፈጽም ተቋም እንጂ ለአገር አንድነትና ዳርድንበር የተሰለፈ ብሔራዊ የመከላከያ ተቋም አይደለም።በዘር አውጫጭኝ(ኮታ) የተመሰረተ ስለሆነ ኢሕዴግ ሲፈርስ ይፈራርሳል፣በየጉሮኖው ይገባል፣ ወይም እርስ በርሱ ይፋጃል።

ወያኔና ግብረአበሮቹ የህዝቡን  ጥያቄ የመለሱ ለመምሰል  የተወሰኑ እስረኞችን በመፍታት የሚወስዱት እርምጃ በነሱ መልካም ፈቃድ የተገኘ ሳይሆን የሕዝቡ የትግል ውጤት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።የገጠማቸውን ውጥረት ለማርገብ የሚወስዱት እርምጃ እንጂ ወደ አልነበራቸው ቀና ልቦና ለመመለሳቸው ምልክት አይደለም።የሕዝቡ ትግልና ጥያቄ የእስረኞች መፈታት ብቻ አይደለም፤የስርዓት ለውጥ ለማምጣት እንጂ!መታሰር የሌለባቸው በመፈታታቸው አሳሪውን ኢሕአዴግን  ቀና አሳቢ አያደርገውም ፤አላግባብ በማሰሩ የሚጠየቅበት ወንጀል ነው።

«የሕዝቡን ስሜት ተረድተናል፣ጥያቄው አግባብ አለው» እያሉ የሕዝቡን ቁጣ ለማብረድና በትግሉ ላይ ውሃ ለማፍሰስ ለይስሙላ እየሰበኩ ጎን ለጎን ግን  እናስተዳድረዋለን በሚሉት ሕዝብ ላይ የአጋዚ ሰው በላ ወታደር በማሰማራት በአደባባይ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሂድ ሕዝቡ በራሱ ጥፋት ያመጣው ቅጣት እንደሆነ አፋቸውን ሞልተው ያወግዛሉ።ከሳምንታት በፊት በወልድያ፣ቆቦ፣መርሳ፣ራያ …ወዘተ የፈሰሰው የንጹሃን ዜጎች ደም ሳይደርቅ፣በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቁስል ሳያገግም፣በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የደረሱበት ሳይታወቅና በበረሃ እስርቤት የተወረወሩበት ሁኔት እየታወቀ፣ ይባስ ብሎ በትናንትናው ዕለት በሐረር ክ/ሃገር  ሃማሬሳ በተባለው ቦታ በሚኖረው ሕዝብ ላይ ዓይን ያወጣ ጭፍጨፋ ተፈጽሞ የ17 ሰዎች ህይወት መጥፋትና፣ ለብዙ ሰዎች የከባድ መቁሰል አደጋና እስራት ምክንያት ሆኗል።አሁንም የግፍ እርምጃው ቀጠለ እንጂ አልቆመም።ይህ ሁሉ ሲደረግ እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ የኢሕዴግ የተባለው ስብስብ አባል የሆኑት የከባቢ ሹመኞች አቋም የእርምጃውን ተገቢነት እንጂ ህገወጥነት የሚያሳይ መግለጫ አልሰጡም፣ድርጊቱንም አላወገዙም።

የሕዝቡ ትግል ከዳር ወደመሃል እየተቀጣጠለ የአዲስ አበባ ከተማ ውጥረት ላይ ወድቃለች። የሰውና የሥራ እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን ተገድቧል፤በእቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ተጥሏል።ተቃውሞው ሰደድ  ሃያት፣አየር ጤና፣ለገጣፎ፣ሱሉልታ፣ሾላ፣አቃቂ፣…..ወዘተ በሚባሉት የከተማዋ አካል በሆኑት ሰፈሮች ደርሶ አራት ኪሎን እየለበለባት ነው።  የወያኔ የበቀል እርምጃም በዚያው መጠን ተጠናክሮ የዜጎች ህይወት እንደተቀጨ ይሰማል።የሕዝቡን ስነልቦና ለመስለብና የፍርሃት ድባብ ለማስፈን በየከተማው አውራ መንገዶች ላይ ወታደራዊ ሰልፍ በሚመስል መልኩ  እንቅስቃሴ በመታዬት ላይ ነው።በሌላ በኩልም የሕዝቡን የትግል ስሜት ለመቀልበስ የግፍ ዋንጫው ሞልቶ በሚፈስበት አገር የህዳሴ ዋንጫ በሚል ፈሊጥ የሕዝብ ገንዘብ በአደባባይ እየተዘረፈ ነው።

የእስረኞች መፈታት አንዱ የትግሉ አካል እንጂ የመጨረሻውና ብቸኛው ስላልሆነ ኢትዮጵያ ከወያኔ የዘር ጥፋትና ከመበታተን እንድትድን የሚያበቃው ትግል መቀጠል ይኖርበታል።የጥቂት እስረኞችን መፍታት በማዬት የሕዝቡን የትግል ስሜት ለማፍሰስና ቀበቶውን ለማስፈታት በሚረዳ መልኩ እያሞካሹ የእርቅና መግባባት ምልክት አድርገው የሚወስዱና የምስጋና መግለጫ ለማውጣት የሚውተረተሩ ወገኖች ሰከን ብለው የሕዝቡን ጥሪ ለማድመጥና ከጎኑ ለመሰለፍ አቋማቸውን ቢፈትሹት መልካም ነው።

ዛሬ የወያኔ ደጋፊ የሆኑት የውጭ ሃይሎች በሙሉ አጋራቸውና የጥቅም አስከባሪያቸው የሆነው ቡድን ከቆመበት የሞት አፋፍ ለማዳን  በመሯሯጥ ላይ ናቸው።እነዚሁ የውጭ ሃይሎች ያለው ስርዓት በጥገና ለውጥ ጥቂት አስመሳይ የተቃዋሚ ቡድኖችን ያካተተ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ወይም ሰላምና መረጋጋት በሚል ፈሊጥ  የወታደራዊ አስተዳደር በማወጅ የሕዝቡን ትግል ለማኮላሸት እየተንቀሳቀሱ እንደነበር ምልክቶች ሲታዩ ቆይተዋል።የእነሱን ጥረት እንደመፍትሔ መቁጠር የባርነቱ ዘመን እንዲቀጥል መመኘትና መፈለግ ነው።ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ጥረትና ትግል እንጂ በውጭ ሃይሎች ደግነትና ፍላጎት አትድንም።ይህንንም የጥፋት ሃይል ሥልጣን ላይ ያስቀመጡት እነሱ በመሆናቸው የወንጀሉ ተባባሪዎች ናቸው።ሕዝብ የሚሞተው እነሱው ባስታጠቁት መሳሪያና የወታደሩም ቀለብና ደመወዝ የሚከፈለው በሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ነው።የሕዝቡ የትግል ግለት ሲጨምርና ወደ ድል ሲቃረብ ወያኔ ስልቱን እንዲቀይር ይመክራሉ፤ ካልሆነ በሌላ ተመሳሳይ ባሪያ መንግሥት እንዲቀየር ያደርጋሉ እንጂ አገር ወዳድ የሆነ መንግሥት ስልጣን ላይ እንዲወጣ አይሹም።

የጎሰኞች ስብስብ የሆነም የወያኔ ተቃዋሚ ቡድን የተሻለ ስርዓት እንደማያመጣ መታወቅ አለበት።አገራችንን ለዚህ ያበቃት የጎሳ ፖለቲካና ጎሰኞች ስለሆኑ ላንዴና ለመጨረሻው ጎሰኝነትን ታግለን ድል መምታት አለብን።ለዚያም ነው ከዘር ወደ ክ/ሃገር፣ከክ/ሃገር ወደ አንድ አገር በማለት የክ/ሃገራት ህብረት የተመሰረተው።

የኢትዮጵያ ክፍለሃገራት ህብረት ላለፉት 27 ዓመታት በአገራችንና በሕዝባችን ላይ የደረሰው በደል፣ጭቆና፣ግድያ፣እስራት፣መፈናቀል፣ስደት፣ድህነት፣ዘረፋ….ሁሉ በኢሕአዴግ ጭንብል የተሰበሰቡ በወያኔ የሚሽከረከሩ ድርጅት መሪዎችና  አባላት የጋራ ድርሻ እንደሆነ ያምናል።እነዚህ ድርጅቶችና መሪዎች ባለፈው ለፈጸሙት ሁሉ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀው እራሳቸውን ከወያኔ ታዛዥነት ካላራቁና አገር አፍራሽ የሆነውን ሕገመንግስት ተብዬ  እስካልተቃወሙና በዛ ሕግ እንደማይተዳደሩ በይፋ እስካልገለጹ ድረስ ለለውጥ ተነሳስተዋል ብሎ አያምንም።ማውራትና መስራት የተለያዩ ናቸውና በጆሮ በምንሰማው ተረት ተረት ከመነሁለል በተግባር ለሚታየውና ለታላቁ ጥያቄ ለስርዓት ለውጥ  ትኩረት መስጠቱ ይገባል።የወያኔ አገልጋይ ሆኖ የኖረው ሃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣኑ ለመውረድ ጥያቄ አቅርቧል።ለይስሙላ ጥያቄውን ተቀብሎ ማጽደቁ የወያኔ መሳሪያ  የጎሰኞች በረት የሆነው ፓርላማ ተብዬው ነው።ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎሳ ፖለቲካ የጸዳ  የስርዓት ለውጥና ለአገር አንድነት ጥያቄ መልሱ  የጠ/ሚኒስቴር ሹም ሽር ማድረግም ሆነ ወያኔ  በተቃዋሚ ስም የፈለፈላቸው ድርጅቶች የሚፈጥሩት የሽግግር መንግሥት አይደለም።የወያኔ ስልት  ዶሮን ሲያታልሏት ወይም የጉልቻ ለውጥ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም። በሽርፍራፊ መሸንገያ የትግሉ አቅጣጫ እንዳይቀለበስ መጠንቀቅ ይገባል።የተበታተነው ሕዝባዊ ትግል መያያዝና መቀጠል ይኖርበታል።አንዱ በተናጠል የሚጠቀምበት ዕድል የለም።እጠቀማለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ስህተት ነው። “ሁሉም ነጻ እስካልሆነ ድረስ አንዱም ነጻ አይሆንም!”

በተጨማሪም ስርዓቱን ወጥሮ የያዘው የወጣቱ እንቅስቃሴ የሚደነቅና መደገፍም ያለበት ነው።ይህ የወጣቶች ትግል ቄሮና ፋኖ በሚል ጎሳን አንጸባራቂ ከሆነ ስያሜ ይልቅ ሁሉንም የኢትዮጵያ ወጣት በሚያካትትና በሚማርክ መልኩ  ገላጭ በሆነ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረት ወይም ግንባር እንቅስቃሴ ቢባል” የተሻለ  ይሆናል። የአማራውና የኦሮሞው ወጣት ትግል ብቻ  ተደርጎ ከተወሰደ የሌላውን ጎሳ ተወላጅ ወጣት የትግሉ አካል እንዳልሆነ  ያስመስለዋል።

የጥቂት እስረኞች መፈታት የሁላችንም ደስታ ሲሆን፣በሕዝቡ ትግል እንጂ በወያኔ ቸርነት የተገኘ ውጤት አይደለም።ትግሉ በዚህ መገታት የለበትም።ሌሎቹም በሽህ የሚቆጠሩ በሥር ላይ አሉ፤ሁሉም  ካለምንም ቅድመሁኔታ መለቀቅ አለባቸው።ግድያና አፈሳ መቆም አለበት፤ሕዝቡ በነጻ ሃሳቡን የመግለጽ መብቱ መከበር አለበት።

ወያኔ በውስጡ ያለበትን ቅራኔ አሶግዶ በናት አገር ጥሪ መልክ የትግራይ ተወላጆች ከያሉበት ተጠራርተው መቀሌ ውስጥ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ  አድማ በመምታት ላይ ናቸው።ከዚያም አልፈው እገነጠላለሁ ብሎ ከተሰለፈ ጸረ ኢትዮጵያ ቡድን፣ ከኦጋዴን ነጻ አውጭ ጋር የስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል።ስምምነታቸው የመገንጠልን ሂደት የሚያካትት ለመሆኑ  አያጠራጥርም።ይኸው የኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅት ቀደም ሲል ግንቦት ሰባት ከተባለው ድርጅትና ከቀሩት ጋር ጥምረት በሚል ስምi ውል የተፈራረመ ነው።የዚያ ውል ትርጉምና ዋጋ ምን ይሆን?

የመጨረሻ ሙከራቸውን በሃይል ለማስፈን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በሚል ሰበብ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ለማወጅ የመጨረሻ መሰናዶ ማድረጋቸው ይሰማል።በቀናት ውስጥ ሳይሆን በሰዓታት ውስጥ ግልጽ ሊሆን ይችላል።ይህ ከሆነ ሕዝቡ እራሱን ከአደጋ ለማዳን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።ትግሉን ስልታዊ በሆነ መንገድ መቀጠል እንጂ በፍርሃት ማፈግፈግ አይኖርበትም።በሁሉም ቦታ የተያያዘ ትግል ቢደረግ የወያኔን ስርዓት ማንበርከክ ይቻላል።በተነጣጠለ መልኩ ከሆነ ግን ለመጠቃት አመቺ ነው።ሁሉም ሕዝብ በሁሉም ቦታ እምቢ ሊል ይገባዋል።የኢትዮጵያ ክፍለሃገራት ህብረት ለሕዝባዊ ትግሉ የሚችለውን ያህል ድጋፍና እርዳታውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽና ለማረጋገጥ ይወዳል።

በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙት የተቃዋሚ ድርጅቶች በተናጠል የሚያደርጉትን እሩጫና የየግል የሽግግር ሰነድ ውድድር አቁመው አንድ የጋራ አመራር መስርተው የሕዝቡን ትግል ማቀናጀት ይጠበቅባቸዋል።የስልጣን ክፍተት ሊኖር ይችላል ብሎ የስደት መንግሥት  በማቋቋም መሽቀዳደሙ የስልጣን እብደት ከመሆኑም በላይ መሳቂያ መሳለቂያ ያደርጋል።ሕዝቡ ከራሱ መካከል መርጦ መንግሥት ያቋቁማል እንጂ አንደ መኪና ከውጭ አገር አያስገባም።አመራር ከውጭ በሪሞት ኮንትሮል የሚሰጡት ትእዛዝ  ሳይሆን በሕዝቡ መካከል ሆኖ በሚያደርጉት ተጋድሎ ነው።

ለአገራችን የወደፊት ሰላምና መረጋጋት ወያኔ  ይወገድ!

ትግሉ እስከነጻነት ድረስ ይቀጥላል እንጂ በሽርፍራፊ ጥገና አይቆምም!!

ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘላለም ትኖራለች!!!

የኢትዮጵያ ክፍለሃገራት ህብረት