ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ሥልጣን መልቀቃቸውን የሰማነው “በድንገት” ቢሆንም፣ ሥልጣን ከተረከቡ ወዲህ በተለይም ላለፉት አምስት ዓመታት ህዝባችን ሲያነሳ የነበረውን የመብት ጥሰቶችንና፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰላማዊ ህዝቦች ላይ ሲወስዱ የነበሩትን እርምጃዎች ለተመለከተው   ሰው   “መንገዱን   ጨርቅ   ያርግልህ”   የሚል   ይመስለኛል።   አቶ   ኃይለማርያም ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ያገሪቷን መከላከያ ሠራዊት ከመደበኛው ያገር ድንበር ጥበቃ ሥራ አስጠርተው፣ በሰላማዊ መንገድ ለመብቱ መከበር ሰላማዊ ሰልፍ የወጣውን ህዝብ በጥይት ያስደበደቡ ግፈኛ ግለሰብ ነበሩና። ጤነኛ ሰው ቢሆኑ ኖሮ በሳቸው ትዕዛዝ መከላከያ ሠራዊቱ ወጣቶችን ሴቶችንና ሲገድል በጸጸት ብዛት ሥልጣን ከለቀቁ ቆይተው ነበር ማለቴ ነው።

አሁን ታድያ “በሰለጠነ መንገድ ሥልጣንን በሰላም ማስረከብን ለማስተማር ብዬ” ሲሉን፣ የፖሊቲካ መሃይም ሆነው ህዝብንም መሃይም አድርገው ከመገመት የተነሳ ይሆናል እንጂ፣ እሳቸውማ ያደረጉት “ሥልጣን ለቀቁ” እንጂ “አላስረከቡም”። ይህ ደግሞ የቃላት ጨዋታ ሳይሆን በሁለቱ ድርጊት መካከል መሰረታዊ ልዩነት ስላለ ነው። አንድ ሰው የፖሊቲካ ሥልጣንን የሚያስረክበው፣ ሀ) በህገ መንግሥቱ መሠረት የተፈቀደለትን የሥልጣን ጊዜ ገደብ ሲጨርስና፣ ለ) በህገ መንግሥቱ መሠረት ሥልጣኑን የሚረከብ ባለሥልጣን ሲመረጥ ነው። ተረካቢ ሳይገኝ፣ መልቀቅ እንጂ ማስረከብ አይቻልም። ስለዚህ የአቶ ኃይለማርያም ሥልጣን መልቀቅ ምክንያቱ፣ የውጪና (ህዝባዊ ዓመጽ) የውስጥ (የኅሊና ጸጸት) ክስተቶች ድምር ያስከተሉት ጫና እንጂ እሳቸው እንዳሉት በፈቃደኝነትና በሰላም ሥልጣንን ለማስረከብ አደለም። ምናልማትም ፈረንጆቹ እንደሚሉት “መርከቢቷ እየሰጠመች መሄዷን ተገንዝበው” ቀድመው መዝለላቸው ይሆን? እንደዚያም ከሆነ ትልቅ ስህተት ሠርተዋል፣ መርከብ ሲሰምጥ፣ ካፒቴኑ የሚዘለው ተሳፋሪው በሙሉ መውጣቱን ካረጋገጠ በኋላ መጨረሻ ላይ ነው። ስለዚህ ቀድመው መዝለላቸው ሌላ ወንጀል ሊሆንባቸው ነው።

ወደ ዋናው ጉዳይ ስንመለስ፣

አዎ እየተቀጣጠለና ለማደፈንም ያልተቻለው ህዝባዊ ዓመጽ፣ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የማይደፈር መስሎ ይታይ የነበረውን የወያኔን ምሽግ በማንኳኳት ላይ ስለሆነ፣ የሥርዓቱ ቍንጮዎች መውጫቸውን ለማዘጋጀት መጣራቸው የሰው ልጅ ዓይነተኛ ጠባይ ነውና መኮነን ባልተገባ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ይህንን ገንፍሎ የወጣውን ሕዝባዊ ዓመጽ እንደ ተራ የመንደር “ጸጥታ መደፍረስ” ቆጥሮ በተራ ድለላ ለማሸነፍ መሞከር ደግሞ ዓይነተኛ የአምባገነኖች ጠባይ መሆኑ ነው። ዛሬ ላጋጣፎና ሰበታ ላይ የሚቃጠለው ጎማ ሳይታሰብ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ደርሶ ሊጨስ እንደሚችል ለመገመት አለመቻል የድንቁርናና የዕብሪት ሰለባ ከሆኑ የወያኔ መሪዎች በስተቀር ሁላችንንም እያሰጋን ያለ አገራዊ ጉዳይ ነው።

ጓደኛዬ “ገሃነም ውስጥ ያሉት ሙቀቱ አይሰማቸውም” እንደሚለው፣  ባለሥልጣኖቻችንና የጥቅም  ተካፋይ ደጋፊዎቻቸው አይሰማቸው ይሆናል እንጂ፣ ሰሞኑን የወሰዱት እርምጃ በሙሉ “ዐልጋው እየተንገዳገደ” አመላካች ነው። ለዓመታት ባገራችን አንድም የፖሊቲካ እስረኛ የለም ሲሉ እንዳልነበሩ፣ የፖሊቲካ እሥረኞች መኖራቸውን ማመን ብቻ ሳይሆን፣ “በሙሉ እንፈታቸዋለን” ማለታቸው፣ እስረኞችን ደግሞ “ስህተት ሰርተናል፣ የዚህ ወይም የዚያ አሸባሪ ድርጅት አባል ነን ብላችሁ ፈርሙና እፈታችኋለሁ” ብለው ለማስፈራራት ቢሞክሩም፣ እስረኞቹ ግን አሻፈረኝ አንፈርምም እያሉም በነጻ መለቀቃቸው፣ እስረኞቹን አጅበው ቤት እንዲያደርሱ የክልል ፖሊሶች ሲታዘዙ፣ የኢህአዴግ ባላሥልጣናት ተፈቺዎቹን “እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ሲቀበሏቸው” ማየቱ፣ ወያኔ ምን ያህል እየደከመ እንደሄደ አመላካች ነው። ጉልበት እየከዳ መሄዱ የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ ማስገረም የለበትም፥ የተወለደ ሁሉ ያድጋል፣ ይጎረምሳል፣ ያረጃል፣ ይሞታል። የሚያስገርመው ግን ማርጀትና ለሞት መቃረብን ተረድቶ ንስሃ መግባትን፣ የበደሉትን ይቅርታ መጠየቅና ከፈጣሪም ጋር ታርቆ ለወዲያኛው ዓለም ጉዞ ስንቅ መሰነቅ እንደ መጀመር፣ “አይ አሁንም ጎረምሳ ነኝ፣ ጉልበት አለኝ” ብሎ ራስን መሸንገል፣ ባልታሰበ ቀንና መንገድ የሞት መልዓክ መጥቶ ከተኙበት አዋክቦ ሊወስድ እንደሚችል አለመገንዘብን ነው።

ህዝባዊ ዓመጹ በተፋፋመ መልኩ ቢቀጥል እንጂ የሚያቆም አይመስለኝም። ህዝብ ደግሞ በተቀነባበረ ትግሉ እስረኛን ማስፈታትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ማውረድ መቻሉን ካረጋገጠ፣ ጥያቄውን  ከፍ  አድርጎ  “ኢህአዴግ  ሥልጣን ያስረክብ” ይላል እንጂ እስካሁን ባስመዘገበው ድል ብቻ ረክቶ ወደ ቤቱ አይመለስም። ስለዚህ እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ለወያኔ/ኢህአዴግ የሚከተለውን  አጭር  መልዕክት ማስተላለፍ  እሻለሁ፣ ካንድ ዓመት  ባልበለጠ  ጊዜ ውስጥ  ሁሉን ዓቀፍ ህዝባዊ ምርጫ እንዲደረግ፣ አዲስ የምርጫ ህግ ማውጣትና የሁሉንም ተቃዋሚ ኃይላት ተወካዮችን ያቀፈ የምርጫ ኮሚሽን እንዲቋቋም፣ ሁሉን ዓቀፍ ምርጫ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲረዳ ደግሞ፣ የሽብር ዓዋጁን ባስቸኳይ ማንሳት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት እላለሁ። ባንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እናንተም የሰረቃችሁትን ተንቀሳቃሽ ንብረት ለማሸሽ በቂ ጊዜ ታገኛላችሁ፣ ተቃዋሚ ኃይላትና ህዝብም ለሰልፍ መውጣቱን ትተው በምርጫው ላይ ያተኩራሉ ማለት ነው።   በቸር ይግጠመን።