February 17, 2018

ለማ መገርሳ

በመጀመሪያ ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን!! ይልቁንስ ለማ መገርሳና ቡድኑ ላደረገልንና እያደረጉት ላለው ቁርጠኛ እርምጃ እያመሰገንን አሁንም በአለበት ሆኖ ቀሪ ሥራውን እንዲፈጽም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ለማ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት መጣ ማለት በእኔ እምነት የተጀመረው ትግል ተመልሶ ወያኔ እጅ ሊገባ እንደሚችል ሥጋቴ ነው፡፡ እውነታው ዛሬ ላይ ጠቅላይ ሚኒሰቴሩ ምንም አይነት ሥልጣን እንዳይኖረው ወያኔ ሥልጣኑን ሁሉ ቆላልፋ እንደያዘችው ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይሄው እኮ በድጋሜ አስቸኳይ ብላ በሕዝብ ላይ አወጀች፡፡ እና ላማ እንደው ቢሆንስ እዚህ ቁማር ውስት እንዲሳትፍ ነው ወይስ፡፡ እሽ አይሳተፍም ለማ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ይምጣ የሚባለው ለመሆኑ ማንን ሊያዝ ነው፡፡ በሳሞራ ትዛዝ ሥር ያለውን መከላከያ ወይስ በጌታቸው አሰፋ ሥር ያውን ደህንነት ወይስ በብዙ ትግሬዎች የተያዘውን ሌላላ ሁሉ መዋቅር ፌደራል ፖሊስ በሉት ሌላ፡፡ ለማ እኮ ለወያኔ የእግር እሳት የሆነባት የሚያዘው ቢያንስ የፖሊስ ኃይልና የሚመራው የሚያምነው ሕዝብ ዙሪያው ስላለ ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ ቀላል ፈተና እንዳለሆነለት እናውቃለን፡፡ ብዙዎች እየረዱት ቢሆንም በሚፈለገው መጥን እገዛ አግኝቶ አደለም፡፡ መሥዋዕትነት እየከፈለ እንጂ፡፡ ለማ ኢሕአዴግ በተባለው ቡድን ውስጥ ኦሕዴድን ወክሎ የራሱን አቋም በመያዙ እኮ ብዙ ማስፈራራትና ልጆቹን ሳይቀር ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ለማ የሚያምንባቸውና የሚወዱት ጠባቂዎች ዙሪያው እያሉ በተገኘው ሁሉ አጋጣሚ እሱን ከያዘው የአይበገሬነት አቋም ለማስቆም ወያኔ በአላት አቅም ሁሉ ተጠቅማ ነው፡፡ በጽሁፍ በወጣው መግለጫ ለማ ያልፈረመበት በመሆኑ ይሄንኑ በጋዜጣዊ መግለጫ አራቱ ግለሰቦች እንዲናገሩ በተገደዱበትም ወቅት የለማ አቋም ግልጽና ከሶስቱ ፍፁም የተለየ ነበር፡፡ ለማ ስለማዕከላዊ ሲያወራ ማዕከላዊን መዝጋት ብቻ በቂ አደለም ብሎ የተናገረው የተለየ ተቃዋሚ እንጂ ኢሕአዴግ የተባለው ቡድን አካል ሆኖ አይደለም፡፡ አዎ ለማ የወከለው የሕዝብን ጥያቄ ነበርና እሱኑ እንደነበረ የራሱንም ፍልስፍና ጨምሮበት ተናገረው፡፡ እንደ ኃይለማሪያም ደርግ ሲጠቀምበት የነበረው ማዕከላዊ በማለት የወረደና የተዋረደ ንግግር አልተናገርም፡፡ በቀጥታ ሰዎች የሚኮላሹበት ሲል ማዕከላዊን ገለጸው እንጂ፡፡ ይሄን እንድታስተውሉ ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎች ከእስር እየተፈቱ ያሉት በለማና ቡድኑ ምክነያት ነው፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ወቅት ለማንና ቡድኑን ማስነሳቱ ከመሠረቱ ጀምሮ አገርንና ሕዝብን ለማጥፋት የተነሱ ወንበዴዎች ለማሳፈርና አገርን ለመታደግ ጭምር እንደሆነ እናስተውል፡፡ አሁንም ብዙ ፈተናዎች አሉብን፡፡ ግን ያለተስፋ አደለንም፡፡ ዛሬ ላይ ለማና ቡድኑ ባይኖሩ አገሪቱ ምን ልትሆን እንደምትችል አስቡ፡፡ አሁን ብዙ ነገር ቀይረዋል፡፡ ግን ገና ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለማ የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት ስለሆነ ነው እንጂ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስለሆነ አደለም፡፡
ሥለዚህ ለማ አሁን በአለበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነ ማለት ለወያኔ ሌላ እድል ተሰጣት ማለት ነው፡፡ ለማ ጠ/ሚኒስቴር ለመሆን እሱ የሚመርጣቸው ጀነራሎች የአገሪቱን መከላከያ ሰንሰለት ሊቆጣጠሩ፣ ለማ የመረጣቸው ደህንነቶች የደህንነቱን ሰንሰለት ሲመሩ፣ ለማ የሚመርጣቸው አዛዦች ፌደራል ፖሊስን ሲመሩ ነው፡፡ ይህን የምለው ለማ በግሉ ፈላጭ ቆራጭ ይሁን ሳይሆን እያልኩ ያለሁት እነዚህ መዋቅሮች አግባብ በአለው ፍትሀዊነት ፍጹም የሆነ ለውጥ ሲደረግባቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ እንደማይሆን እናውቃለን፡፡
የገረመኝ አሁን ሳስተውል አብዛኛው የለማ ደጋፊ ነኝ የሚለውም በእርግጥም ለማን ከመውደድ ይሁን ከሸፍጥ ባይገባኝም ለማ ጠ/ሚኒስቴር ይሁን ባዩ ከምሁር እስከ ደቂቁ ነው፡፡ ማስተዋል ከቻልን ግን ለማ በአሁኑ ወቅት አሁን ያለበትን ቦታ ለማስለቀቅና በምትኩም ለወያኔ የሚመች ግለሰብ ለማስቀመጥ ከአልሆነ ለማ ጠ/ሚኒስቴር ቢሆን የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ እባብ ሞኝን ሁለቴ ነደፈው ሳይሆን ደጋግሞ ነደፈው እንደሚባለው ነው፡፡ ለማ ወደጠቅላይ ሚኒስቴርነት መጣ እንበልና በእሱም ቦታ አብይ ወይም ከለማ ቡድን አንዱ የእሱን ቦታ ተካ ማለት ሌላ ክፍተት ነው፡፡ በክፍተቱ ደግሞ የሚተካው ማን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ በጣም ጥሩ የሚባለው ሂደት ከሆነ ነው፡፡ ያም ሆኖ ለማ ከመሀል ሲጎድል አደጋው ብዙ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ አስቡበት፡፡
በአሁኑ ወቅት የለማ ደጋፊ የሚመስለው ሁሉ ደጋፊ እንዳይመስላችሁ፡፡ ነገሮች ስላልሆኑለት ደጋፊ መሆንን እንደስልት የሚጠቅም ስንት ሴራ አዘል አስተሳሰብ የሚነዛ አለ፡፡ ወያኔን በአፍ እየረገመ ለማን እያወደሰ ለወያኔ ለወያኔ ሥራአስፈጻሚ በየቦታው ነው፡፡ እንዲህ ቀላል አደለም፡፡ ደጋፊ መስሎም ሌሎችንም ብዙ ሴራዎች በማሴር ለማንና ቡድኑን ለማምከን የሕዝብም ድጋፍ ለማሳጣት የማይሴር ሴራ የለም፡፡ የሌሎች ብሔር ተወላጆችን በተለያየቦታ በማሰማራት የብሔር አዘል ጸብ እንዲነሳ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ በክልሉ በሚኖሩ ሌሎች ብሄሮች ላይ ኦሮሞ በሆኑ ሰዎች ጥቃት በማድረስ ብዙ ብዙ፡፡ ከዚህ በፊት የቡኖ በደሌውን ሰምተናል ሰሞኑን ከደቡብ ተልከው ሊሆን ይችላል ቢሾፍቱ (ደብረ-ዘይት) ላይ ሥራ እንሰራለን የሚሉ የደቡብ ተወላጆች በአንድ የኦሮሞ ተወላጅ ልጅ ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸማቸው ሕዝቡ እንዲቆጣ በማድረግ ቀጥለው ተሰብስበው አየር ኃይል ግቢ በመሄድ ኦሮሞዎች ሊፈጁን ነውና አስጥሉን ያሉበት ሂደት ከመነሻውም ሟቹን በመግደል የብሄር ጸብ እንዲነሳ ታስቦበት ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነበር፡፡ እንግዲህ ሂሳቡ በዚህ ምክነያት ከኦሮሚያ ፖሊስ ውጭ ሌላ ጣልቃ እንዲገባ መሆኑ ነው፡፡ ሂደቱንም ኦሮሞ ሌሎች ብሄሮችን እየጨረሰ ነው በሚል ሌላ መልክ ለማስያዝና ለማንም በኢትዮጵያ ሥም እየነገደ የኦሮሞ ጽንፈኞችን እያገዘ ነው ለማስባል ነው፡፡
እንዲሁ ሰሞኑን ቀላል የሚባል ክስተት የንግድና ድርጅት ማስታወቂያ ታፔላዎች በትክክሉ እንዲጻፉ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተደረግን እንቅስቃሴ ለማ አማርኛን ከኦሮሚያ ለማጥፋት የከፈተው ዘመቻ በሚል ብዙዎች ሲያራግቡት ነበር፡፡ እንግዲህ ሲጀምር ይሄ የማስታወቂያ ታፔላ ማስተካከያው የተወሰደው በጥቂት ወረዳዎች ምን አልባትም ይመስለኛል በዶዶላ ከተማ ነው፡፡ ማስታወቂያ ጽሁፉ ግድፈት ስላለበት፣ በኦሮምኛ የተጻፉት እንዳንዶቹ ስለማይነበቡ፣ አንዳንዶቹም ሌላ ትርጉም ስለሚሰጡ ሌሎቹ ደግሞ ከነ አካቴውም በአማርኛና ኢንግሊዘኛ ብቻ መጻፋቸው ነው፡፡ እንግዲህ አስቡት ይሄ በጣም ትንሹ ግን ብዙዎችን በአስተሳሰብ ብክለት የጣላት መሳሪያ እንዲሆኑ ምን ያህል ወያኔና አጋሮቿ እያሴሩ እንደሆነ ነው የሚየሳየን፡፡ በእርግጥ አሁን ላይ በዛው ልክ ብዙ የነቃ ስላለ የወያኔን ሴራ ከአፈር እየቀላቀልንው ነው፡፡
ሌላው እውነት ለመናገር የለማ የአፍ ደጋፊዎች ብዙ የሚባሉ ለማን የሚያዩት እነድ ኦሮሞ (አዎ ነው ግን ኢትዮጵያዊ ነው) እንደ ኢትዮጵያዊ አደለም፡፡ ሌላ ቀርቶ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ የሚለፈለፈው ሁሉ ለማን ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ በአፉ ቢደግፍም ውስጡ ሲኦል የሚያስብ ብዙ ነው፡፡ እውነታው ለማ አሁን በጀመረው ተሳክቶ ይች አገር አገር ሆና ከቀጠለች ኢትዮጵያን ዳግም የሰራ የሚኒሊክና ጎበና ልጅ ነው፡፡ በእርግጥም ለማ የተነሳው በእነዚህ የታሪክ ምልከቶች ወኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ውርደት በሆነበት በገዛ አገሩ ኢትዮጵያ ብለህ አትዝፈን በተባለባት ምድር ከ27 አመት የወያኔና አካሮቿ ጸረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ከዚህ በፊት በቀደሙት መንግስታት እንደምንሰማቸው ድምጾች በይፋ የተናገረ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማ በአልኩ ቁጥር ቡድኑንም ጭምር እያልኩ መሆኑ እንዲነበብልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ታዲያ ለማን አሁንም ኦሮሞ ስላልሆኑ ብቻ ሥሙ ሲነሳ ቅር የሚላቸው አሉ፡፡
ሌላው በዚህ ወቅት ከትብብር ይልቅ ነገሮች ወደ ፉክክር እንዲያመሩ የሚየሴሩ አሉ፡፡ ፍክክሩ ደግሞ እንዲሆን የተፈለገው በአማራና ኦሮሞ ነው፡፡ ለወያኔ ትልቅ ራስ ምታት የሆነውም የእነ ለማ ለዘመናት እንደጠላት እንዲተያይ ወያኔ ስንት የለፋችበትን የአማራና ኦሮሞ የመለያየት ሴራ ማፈራረስ ነው፡፡ እናም ሰሞኑንም የጠ/ሚኒስቴርነቱን ቦታ የፉክክር ሊያስመስሉት የሚሞክሩ አሉ፡፡ እውነታው አሁን በአለው ሁኔታ ጠ/ሚኒስቴር መሆን ልዩ ሥልጣን መያዝም አደለም፡፡ ወያኔ እንደተባለውም ለማን ልትል ትችላለች ከተሳካላት፡፡ እሱን ከዚያ ቦታ ለማንሳት፡፡ ከዛ ውጭ ግን የዚህ የጠ/ሚኒስቴርነት ጉዳይ እኮ ሲወራ ሰንብቷል አንዳንዶቻችን እንዴት እንደማናስተውል አይገባኝም፡፡ የአሜሪካው ያማሞቶ ኢትዮጵያ በጎበኘበት 2-3 ወር ገደማ እኮ ጌታቸው አሰፋ ለጠ/ሚኒስቴርነት ያዘጋጀሁት ሰው አለ ሲል ነበር፡፡ ልብ በሉ ጠ/ሚኒሰቴሩን የሚመርጠው ጌታቸው አሰፋ እንደሆነ፡፡ ደግነቱ ዛሬ (ከ3 ወር በፊት እነደዚያ አልነበረም) ላይ መቼም ጠ/ሚኒስቴር ሲመረጥ ፓርላማ መሰብሰቡ አይቀሬ ስለሚሆን ውጤቱ ጌታቸው አሰፋ እንደፈለገው ላይሆን ይችላል፡፡ ሌላው ምክትል ጠ/ሚኒስቴር ተብዬው እኮ ከኃይለማሪያም የማያንሰው (በምን እንዳትሉኝ…) እኮ እዛው አለላቸው፡፡ በዛውም ለአማራ ተሰጠ በሚል ሌላ ሴራ ይሰሩበታል ያው እነሱን ስለሚመስላቸው ማለቴ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሳሞራ ዩኑስና ጌተቸው አሰፋ በጋራ ሥልጣኑን እንዲይዙት ሊደረግ እንደሚችል መገመት ነው፡፡ ይም ሆነ ይህ ለማን እዚህ ቁማር ውስጥ ገብቶ ማጣት እንደሌለብን መሆኑን በአጽኖት ልናስብበት ይገባል፡፡ በአይሆን ከኦሕዴድ ይሁን ከተባለ ሌላ ሰው አድርጎ ለማ እንዲረዳውና ቀስ በቀስም ከውጭ ለማ ከውስጥ እሱ ሆነው የትግሬውን ሰንሰለት መበታተን ነው፡፡ ለማና ቡድኑ ደጉም ጉልበት ከአገኘ የያዘውን ይዞ ከውስጥ ለሕዝብ የሚታመን ሌላ ሰው ከአለ እነ ሳሞራ እናፍን ቢሉ እንኳን እነ ለማ ደጀን ሆነውት ቀስ በቀስ ወያኔን መበታተን ነው፡፡ ከታሰበበት ደግሞ ከለማም ጋር የሚሰሩ እኮ ብዙ ከኋላ አሉ ጠ/ሚኒስቴር መሆን የሚችሉ፡፡ ለማ ጠ/ሚኒሰቴር ሆነ ማለት ግን የሕዝብ ትግል በወያኔ ቀለበት ውስጥ ገባ እንደማለት ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ሁላችንም እናስብበት፡፡
አመሰግናለሁ!
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ! አሜን!
ሰርጸ ደስታ