18/02/2018

ዘረኛውና ዘራፊው የወያኔ አገዛዝ በሞት ዋዜማ (ጻዕረ ሞት) ላይ እንደሚገኝ ለኢትዮጵያውያን የአደባባይ
ምሥጢር ነው፡፡ ለማይጠረቃው የሥልጣንና የዝርፊያ ፍትወቱ ሲል እስከ መጨረሻው ትንፋሽ/ሕቅታ እንደሚፍጨረጨር እና ከጥፋቱ እንደማይመለስ ላለፉት 27 ዓመታት በገሃድ ካሳየን ባህርይው የታወቀ ነው፡፡ የአሁኑም ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ›› ወያኔ በሚያምንበት ጉልበት (ለራሱ ህልውና ባቋቋመው ሠራዊትና የግል ደኅንነት ኃይል) በቀቢፀ ተስፋ የሚያደርገው አልሞት ባይ ተጋዳይነት ነው፡፡ ደጋግሞ እንደተነገረው አገዛዙ በዐዋጅም ሆነ ያለ ዐዋጅ ከ‹‹አስቸኳይ ጊዜ›› ሁኔታ ወጥቶ አያውቅም፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሲገዛ በመቆየቱ የአሁኑንም እንደ አዲስ ክስተት ልናየውና ሊያስበረግገን አይገባም፡፡ የአገዛዙ ቋሚ መገለጫ ነውና፡፡ እውነቱን ለመናገር በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ያለው በድንቁርናና በጥላቻ በሽታ ተይዞ አገራችንን ያዋረደው እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላምና ጸጥታ ያደፈረሰው ራሱ አሸባሪው የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡

ይህ አገዛዝ ከመነሻው በሕገ አራዊት የሚተዳደር በመሆኑ ስለ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማንሳት የትኛውም
ዓይነት ብቃት የለውም፡፡ በመሆኑም የሚናድ ‹‹ሥርዓት›› ካለ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት የተነሱ የጥቂት መንደርተኞችና ወሮበሎች ቡድን እንጂ ሕግና ሥርዓት ያለው መንግሥት አይደለም፡፡ ነቀርሳ የሆነውን የጎሣ ‹ፌዴራሊዝም› (ክልላዊ አፓርታይድ ወይም የውስጥ ቅኝ አገዛዝን) እና ተያያዥ ደዌያትን የተከለው የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› እገዛዋለኹ በሚለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ እንዲያካሂድ፣ በሰብአዊነት ላይ ወንጀል እንዲፈጽም፣ በአመለካከት እና በእምነት ምክንያት እልፍ አእላፋትን ለወህኒ ቤት እንዲዳርግ፣ በዚያም የሚፈጸም አረመኔያዊ/ኢሰብአዊ አያያዝ፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሕይወትና የንብረት ዋስትና የሌለበት የሰቆቃ ሕይወት እንዲመራ የሚፈቅድ አልነበረም፡፡ የአሁኑ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዓላማ ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን ወንጀሎች በስፋት ለመፈጸምና እንደ ሰደድ እሳት በመላ ኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በማቆም ለአፓርታይዲያዊ ሥርዓቱ ፋታ መግዣነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ቆሻሻ አገዛዝ ከሚችለውና ከሚሸከመው በላይ ታግሦ የግፍ ጽዋው ሞልቶ ሲፈስ ነው
– ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሽቶ፣ በአእምሮ ድንክዬዎች ሳይሆን በሕግ የበላይነት ለመተዳደር ፈልጎ፣ የአገዛዞች
መፈራረቅ አንገሽግሾት መንግሥተ ሕዝብ ለማቆም – በዓመፃ ገንፍሎ የወጣው፡፡ ስለሆነም በወያኔ ትግሬዎች አገዛዝ ስለሚናድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማውራት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው የሚሆነው፡፡

የወያኔ አገዛዝ የጉልበት መሆኑን ለምን እንዘነጋለን፡፡ በርካታ አፋኝና ፀረ-ሕዝብ ‹ሕጎችን› ሙሉ በሙሉ
በተቆጣጠረው የደናቁርት ‹ሸንጎ› አማካይነት እያወጣ ተግባራዊ በማድረግ በአገርም በሕዝብም ላይ ይቅርታ የማያሰጥ ጥፋት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ሕጋዊ መሠረት አለው የለውም የሚለው ጉዳይ ጠያቂ ለሌለበት የወንበዴዎች ቡድን ምኑም አይደለም፡፡

ቁም ነገሩ የጀመርነውን ኢትዮጵያን የመታደግና የነፃነት ትግል ግለቱን ጠብቀን ማሰቀጠሉ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ
ይቻላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የገፈቱ ቀማሽ በሆኑ ኢትዮጵያውያን እናትና አባቶች እንዲሁም ወጣቶችና ሕፃናት ስም በጥብቅ ማሳሰብ የምፈልገው ራሳችሁን ‹የአገር መከላከያ ሠራዊት› አካል አድርጋችሁ የምትቆጥሩ የሠራዊት አባል (ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ አየር ኃይል) ካላችሁ ለልጆቻችሁ/ለቤተሰባችሁ፣ ለራሳችሁ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ ከሁሉም በላይ ለሁላችን የጋራ ቤት ኢትዮጵያ ስትሉ ወደ ልቦናችሁ ተመልሳችሁ፣ ለአገርና ለሕዝብ ታሪክ የሚያስታውሰው ገድል የምትፈጽሙበትና ማንነታችሁን የምታሳዩበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ይህ ጥሪ ወያኔ ለሥልጣኑና ዝርፊያው ቀዳሚ መሣሪያው ያደረጋችሁ የአግአዚ ልዩ ጦርንም ይመለከታል፡፡ የእምቦቃቅላዎችን ግምባር በጥይት እየቦረቀሱ በነገዋ ኢትዮጵያ ቦታ ይኖረናል ማለት ዘበት ነው፡፡

ሌላው ከወያኔ ባልተናነሰ የማዝንባችሁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም በእጅጉ ያዘነባችሁ፣ በተቃዋሚ ስም ለወያኔ
በአድርባይነት ያደራችሁም ሆነ የሕዝብ እውነተኛ ውክልና ሳይኖራችሁ በተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበር ስም የምትንቀሳቀሱ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ኃይሎች ናችሁ፡፡ ሕዝብ የተበታተነ ትግል እንዲያደርግ የተገደደው በእናንተ ተስፋ ቆርጦ መሆኑን የምትረዱት መቼ ነው? በውኑ ቀዳሚ አጀንዳችሁ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ናቸው? 27 ዓመታት ሙሉ የኢትዮጵያን ህልውና መታደግ የሚለው ብሔራዊ ጉዳይ የማያስተባብራችሁ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕፃናቱንና ወጣቶችን ገብሮ በሚያገኘው ነፃነት ማግስት እንዴት አድርጎ ነው እምነቱን የሚጥልባችሁ፡፡ ትግሉንስ አገር አቀፍ አድርጎ ማን ያስተባብር/ይምራ? ብዙዎቻችሁ ጎሣ ለተባለ ጣዖትስ እስከ መቼ ትንበረከካለችሁ? በውኑ የሠለጠነ የፓርቲ ፖለቲካ ገብቶናል ወይ? ታላቅ የሕዝብ አደራ፣ ኃላፊነትና ግዴታ ያለው ተግባር መሆኑን አምነንበት ነው ወይስ ሥልጣንና በሥልጣን አማካይነት የሚገኘውን ጥቅም እያሰብን በፖለቲካ ለመደራጀት የወሰነው? ለመሆኑ ዓላማችሁ ምንድን ነው? የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ ያልተባበረ ኃይል የሕዝባችንን የቋንቋና ባህል ልዩነትን የሚያስተናግድ አንድነት፣እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ያለበት መንግሥተ ሕዝብ ለመትከል የሚያስችል ሕጋዊ ሥርዓት
ለመመሥረት ምን ዓይነት ብቃት ይኖረዋል? የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገር ባለቤትነትና የሉዐላዊነቱ መገለጫ የሆነውን የመንግሥት ሥልጣን በውክልና አሳልፎ እንዲሰጣችሁና ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመቀበል በመጠኑም ብቁ ሆኖ ለመገኘት በትንሹ መታመናችሁን የምታሳዩበት ጊዜ ዘግይቷል የሚባል ካልሆነ በቀር ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡

ቀሪውን ትግል በጎሣ መስመር (የኦሮሞ የአማራ የሚለውን አቁመን) ሳይሆን ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን
ኢትዮጵያ መሆኗን አውቀን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንድናጠናቅቀው ታናሽ ወንድማችሁ ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ በማለት እማፀናለኹ፡፡

 ለማጠቃለል የወያኔ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወያኔ በሞቱ ዋዜማ ያወጣው ዐዋጅ መሆኑን እና ሞቱንም  እንደማያስቀርለት በማመን ኢትዮጵያችንን ለመታደግ ከትግራይ እስከ ሞያሌ፣ ከወለጋ እስከ ሐረርጌ ያለን
ኢትዮጵያውያን በሙሉ በፍቅር፣ በኅብረት ባንድነት እንነሳ፡፡

ከዚህ ቀደም ባቀረብኋቸው አስተያየቶች ደጋግሜ እንደገለጽኹት ይህ በተንኮል የተጠበበና በቅጥፈት የተካነ
አገዛዝ ከእውነትና ንስሓ ጋር እንደተፋታ ወደ ታሪክ ቆሸሻ ቅርጫት እንደሚጣል አልጠራጠርም፡፡ በመሆኑም አንዳንዶች ከቅንነትና ከሥጋት በመነጨ የምታነሱት ‹‹የእውነት እና ዕርቅ ማፈላለግ›› ፍላጎት ለዚህ አገዛዝ ባህርይ የሚስማማ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ረገድ እኔ ተሳስቼ ተአምር ቢፈጠር ደስተኛ ነኝ፡፡

የንጹሐን ሕፃናትን ደም ቸል የማይል የኢትዮጵያ አምላክ ትንሣኤዋን በቅርብ ለማየት ያብቃን፡፡