First Hijrah Foundation 
4324 Georgia Avenue NW, Washington, DC-20011
__________________________________________________________________________________________

February 18, 2018

ጀግኖቻችንን በደስታ እንቀበላለን፥
የታሰረውን ጥያቄያችንን እናስፈታለን!

የሕዝብ ጀግኖች አህመዲን ጀበል፣ በቀለ ገርባ፣ አህመድ ሙስጦፋ፣ ኦኬሎ አኳይ፣ እስክንድር ነጋ፣ ሙሐመድ አባተ፣ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ አንዱዓለም አራጌ፣ ኻሊድ እብራሂም፣ ጫልቱ ታከለ፣ ደረጀ ጣፋ፣ ጉርሜሣ አያኖ፣ አዲሱ ቡላላ፣ ግርማ ተስፋይ ሊበን፣ በየነ ሩዳ፣ ወ/ሮ እማዋይሽና ሌሎችም እንኩዋን ከምትወዱትና ከሚወዳችሁ ቤተሰቦቻችሁና ሕዝባችሁ ጋር ፈጣሪ አሏህ አገናኛችሁ ይላል ፈርስት ሒጅራህ ፋዉንዴሽን::
የህዝበ ሙስሊሙ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ከተመረጡበት ግዜ አንስቶ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች የሚያደርጉትን የመብት ትግል በመደገፍ ፈርስት ሒጅራህ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። ዛሬም ጀግና የሆኑት የህዝብ ወኪሎች ከሚሰቃዩበት እስር ቤት ተፈተው ቤተሰቦቻቸውንና ህዝብን መመቀላቀላቸው አንድ የትግል እርከን ነው ብሎ ፈርስት ሒጅራህ ያምናል። ህዝቡ ይህንን የትግል እርከን በመዉጣት፣ከወኪሎቹ ጋር ተገናኝቶ መደሰቱ ለፈርስት ሒጅራህ ማህበረስበ ታላቅ ደስታን ያጎናጸፈ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

የህዝብን ዉክልና የተቀበሉት ኮሚቴዎች አስታራቂ ሽማግሌ በመሆን የህዝብን ድምጽ ለማሰማት ጥረዋል። በህዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ ሆነው አገልግለዋል። ይህንን የተቀደሰ ተግባር በማከናወናቸው ሳቢያ ለከፍተኛ ምድራዊ ስቃይ መዳረጋቸው አለም የሚያዉቀው እዉነታ ነው።ዛሬም ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ፣በሐሰት ወንጅሎ የፈረደባቸው አምባገነናዊ መንግስት ሴራ ተጋልጦ ህዝብን መቀላቀላቸው ታላቅ ብስራት በመሆኑ ፈርስት ሒጅራህ ፋዉንዴሽን የደስታዉ ተካፋይ ሆኖ ደስታዉንም ይገልጻል።

ፈርስት ሒጅራህ ፋውንዴሽን በሐሰት ተወንጅለው እስርቤት የገቡት ኮሚቴዎች አጋር ሆኖ የዉስጥንም የዉጪንም ትግል ታግሏል። በገንዘብ፣በዲፕሎማሲ፣በህዝብ ግንኙነት ስራዎች፣የተለያዩ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን በማዘጋጀት፣አሜሪካንን ጨመሮ ሌሎች የዉጭ መንግስታት በአምባገነናዊው መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ በማነጋገር ፈርስት ሒጅራህ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። በህወሃት የሚመራዉ መንግስት ያሰራቸውን የህዝበ ሙስሊሙ

ጥያቄዎች ለማስፈታት ፈርስት ሒጅራህ ዛሬም ጠንክሮ እንደሚሰራ ሲገልጽ የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች አጋርና ተባባሪ ሆኖ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ይሰጣል።
ጀግና ወኪሎቻችን በክብር መፈታታቸው ጀግንነትን ከትውልድ ወደ ትዉልድ የሚያሻግር ታሪካዊ ክስተተት ነው።ጀግና ወኪሎቻችን «ይቅርታ ጠይቁ» ሲባሉ «እምቢኝ-አሻፈረኝ» ማለታቸው አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉ ትዉልዶች ይኖሩ ዘንድ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።ጀግና ወኪሎቻችን ከእስር ከተፈቱ በሗላ ያደረጓቸው ንግግሮች ሙስሊሙ ማህበርሰብ የክብር ካባ ደርቦ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ የሚያግደው ነገር እንደሌለ የተመላከተበት ሆኗል።ጀግና ወኪሎቻችን በአቋማቸው ጸንተው የመፈታታቸውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ሙስሊሙ ማህበረሰብ በስድስት አመታቱ የትግል ሒደት ዉስጥ የተፈጠሩበትን ክፍተቶች በመሙላትና በመቀራረብ የታሰሰሩትን ጥያቄዎች ለማስፈታት ከህዝብ ወኪሎች ዘንድ እንዲቆም ፈርስት ሒጅራህ ጥሪዉን ያቀርበል።

ፍትሕ ለሁሉም ዜጎች!
ትግላችን ባንድነት እስከድል በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!!

አሏህ አክበር !!!
ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን

ዋሽንግተን ዲሲ