(አንጋፋው ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ አገር ቤት ለሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ ኢትዮጵያውያን ወደፊት እንጅ ወደ ኋላ መመልከት እንደሌለባቸው በመገልጽ ከአሁን በኋላ በዜጎች ላይ ከዘራቸው የተነሳ የሚደርሰው ጥቃትና የንብረት ወድመት እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል። የሪፖርተርን ጋዜጣ ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል)

እስክንድር ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት የታሰረው ባልሠራው ወንጀል በሐሰት ተከሶ ነው፡፡ ከሕይወቱ፣ ከልጁና ከባለቤቱ የጠቀሰውን ያህል ዕድሜ መቀነሱንና በአጠቃላይ በእስር ቤት ብዙ ነገሮችን ያሳለፈ ቢሆንም፣ ስላለፉት ጊዜያት ማንሳትና ቀደም ብሎ የተናገራቸውን መድገም እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡

‹‹ለአገራችን የሚበጃት ወደኋላ መመልከት ሳይሆን ወደፊት ማየት ነው፤›› የሚለው እስክንድር፣ እሱ ምንም ደረሰበት ምን የሚያስበው ስለድሮው ሳይሆን በቀጣይ ተስፋ በሚያደርገው ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

ከእስር ሲለቀቅ በኢሕአዴግ ላይ ጥላቻና ቂም በቀል ይዞ አለመውጣቱን የሚናገረው እስክንድር፣ ኢሕአዴግ ወደፊት በሚመጣው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ አንድ አካል ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳለው አስረድቷል፡፡

ኢሕአዴግ በእሱ ላይ በል ስላደረሰበት ቂም በቀል ይዞ እንደ ኢሠፓ ይበተን የሚል አቋም እንደሌለው ወይም እንዲበተን እንደማይፈልግ የሚናገረው እስክንድር፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የሚጠቅም ሥራ እንዲሠራና ከስህተቶቹ እንዲማር ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

በአውሮፓና በአፍሪካ አገሮች በተለይ በቦትስዋና፣ በጋና፣ በማላዊና በደቡብ አፍሪካ የታየው ብሩህ ተስፋ፣ በኢትዮጵያም የማይኖርበት ምክንያት እንደሌለ የሚናገረው እስክንድር፣ እነዚህ አገሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት የገነቡ በመሆናቸው፣ ለኢትዮጵያ ዓይነተኛ ምሳሌዎች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ በኢትዮጵያ በተጨባጭ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያስተምሩ ምሳሌዎች መሆናቸውንም አክሏል፡፡

በደቡብ አፍሪካ አምባገነኖች በሕዝብ ላይ በደል ማድረሳቸውን የጠቆመው እስክንድር፣ ናሽናል ፓርቲ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት በተደረገው ሽግግር የኮሻና የዙሉ ጎሳዎች መጨራረሳቸውን ጠቁሟል፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውንም አክሏል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲገነቡና ከገነቡ በኋላ ግን ወደ ኋላ ተመልሰው ያንን ግፍና በደል መመልከት አለመፈለጋቸውን አውስቶ፣ ኢትዮጵያም ውስጥ ስለተፈጸመው ግፍና በደል ወደኋላ መመልከት ተገቢና አስፈላጊ ባለመሆኑ፣ ወደፊት የሚታየውንና ያለውን በሰላም፣ በዴሞክራሲ፣ በወንድማማችነት፣ በፍቅርና በአንድነት ተስፋ ላይ መሥራት ተገቢ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የብሔር ጥቃት እየታየ መሆኑን የገለጸው እስክንድር፣ ‹‹የብሔር ጥቃት፣ የፋብሪካና ሌሎች ቃጠሎዎች፣ በንብረትና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም አለባቸው፤›› ብሏል፡፡ የሕዝብ ትግል ግቡ ለጥሩ ነገር ስለሆነ፣ ሥልቱም ጥሩ መሆን እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ሥልቱ ከተበላሸ ግቡን ማስተካከል ስለማይቻል፣ በተለይ ወጣቱ ሥልቱ ላይ መጠንቀቅ እንዳለበት ምክሩን አስተላልፏል፡፡ ለግቡ ያለውን ራዕይ በሥልቱ ማሳየት እንዳለበትም አክሏል፡፡ በኢትዮጵያ የብሔር ጥቃት በመታየቱ መፍራት ተገቢ አለመሆኑንን የገለጸው እስክንድር፣ በደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ወደ ዴሞከራሲ ሥርዓት በሚደረግ ሽግግር ተመሳሳይ ጥቃት የተፈጸመ ቢሆንም፣ ያንን ሁሉ ችግር አልፈው የዴሞክራሲ አገር ለመገንባት መቻላቸውን አስረድቷል፡፡ በኢትዮጵያ ግን የብሔር ጥቃት መፈጠርም ሆነ መታሰብ እንደሌለበትና ችግሩን በትክክል የማወቅ ግዴታ የኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ሕዝብ በመሆኑ በጋራና በአንድነት ተባብሮ በሰላማዊ መንገድ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታዩትን ግጭቶች ከምንጩ ለማድረቅ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሕጋዊ መድረክና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ጋር መደራደር እንዳለበት የተናገረው እስክንድር፣ ኢሕአዴግ ቀደም ብሎ የሚያስቀምጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ትቶ ካልተደራደረ ግጭቶች እየተባባሱና ሥር እየሰደዱ ሄደው አገር አደጋ ላይ እንደምትወድቅ ጠቁሟል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ፓርቲ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰና እየተበላሸ መሄዱን ሲያይ ከኤኤንሲ (ANC) በመደራደሩ ለውጤት መብቃቱን ጠቁሞ፣ ‹‹ይኼንን ጥበብ ኢሕአዴግም መማር አለበት፤›› ብሏል፡፡

ኢሕአዴግ በመርህ ደረጃ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተደራደረ መሆኑን እየገለጸ ቢሆንም፣ ‹‹ግን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? ቢሆንም እንኳን ግማሽ መንገድ ይቀረዋል፤›› የሚለው እስክንድር፣ ጊዜው አሁን ስለሆነ ከሁሉም ጋር በመደራደር የኢትዮጵያን አንድነት መጠበቅ ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ኢሕአዴግ ውስጥ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቁ ሰዎች እንዳሉ ስለሚታወቅ፣ ፓርቲያቸው ወደ ሰላም አቅጣጫ እንዲሄድ መታገል እንዳለባቸውም ጠቁሟል፡፡ የፖለቲካ እስረኞች የማይኖሩባት አገርና ሥርዓት መገንባት እንዳለበት የጠቆመው እስክንድር፣ የታሰሩ ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈትቶ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አካል መሆን እንዲችሉ ማድረግ ተገቢና የግድ መሆኑን አስረድቷል፡፡