አንጋፋው የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመነበር፣ አገር ቤት ለሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጸው፣ ኢሓዴግ ለ26 አመታት ዴሞርካሲን ሲዞረው ቆይቶ መጨረሻ ላይ ለዲሞክራሲ እቅፋት የሆነው ራሱ መሆኑን ማመኑና እስረኞችን ለመፍታት መሞከሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ በአገሪት አዲስ መራፍ መጀመር እንዳለበት ያሳስባሉ። አቶ አንዱዋለም ‹‹አሸባሪ፣ አገር ከጂና ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን መናገር ትርጉም የለውም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከችግር መውጣት አለብን” ሲሉ ኢትዮጵያ በፊቱ ትልቅ ችግር እንደተጋረጠባትና ኢትዮጵያዉይና በአንድ ላይ ሆነው በጋራ ማደግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

በአገሪቷ ያለው የዘር ግጭት ፣ የዘር ፖለቲካ ለብዙ ዜጎች መፈናቀል፣ መሞት ምክንያት መሆኑ ይታወቃል። አቶ አንዱዋለም ” ሥርዓቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም፣ ወጣቱ ግን መጠንቀቅና ከጥፋት መራቅ አለበት፡፡ በተለይ ወጣቱ፣ ዘረኝነት የሚሉትን ነቀርሳ መቋቋምና ማስወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያንን ዘረኝነት አይገልጸንም፣ አይወክለንምም” ሲሉ ዜጎች ከዘር ፖለቲካና አስተሳሰብ እንዲወጡ አሳስበዋል።

ሪፖርተር ጋዜጣ አቶ አንዱዋለማ አራጌ በተናገሩት ዙሪያ ያሰፈረውን እንደሚከተለው ቀርቧል፡

——

ሰሞኑን ከተፈቱት ፍርደኞች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) አመራር የነበረው አቶ አንዱዓለም አራጌ በበኩሉ እንደተናገረው፣ ‹‹እስር ቤት ያሳለፍኩትን የግፍ፣ የመከራና፣ የስቃይ ዓመታት ወደኋላ ሄጄ ማሰብ አልፈልግም፤›› ይላል፡፡

‹‹በደሌን መቁጠር ከጀመርኩ ቁስሌ ያመረቅዛል፣ ሕመሜን ማዳመጥ አልፈልግም፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ብዙ የተጎዳም ቢሆን ፈጣሪው ፀጋውን አብዝቶለት እስሩንና የደረሰበትን በደል ተቋቁሞ መፈታቱን ተናግሯል፡፡

በተለይ በመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት ተኩል አይደለም በአገር ዜጋ ላይ ቀርቶ በሌላ አገር ዜጋ ላይም ቢሆን ሊፈጸም የማይገባ በደል እንደተፈጸመበት ገልጾ፣ እስከ መጨረሻው የእስር ዘመን (ስድስት ዓመታት ከስድስት ወራት) የደረሰበት በደል የሚሰቀጥጥ በመሆኑ ማንሳት እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡ ግን ያ መስዋዕትነት እንደሚፈጸምበት አስቀድሞ ስለሚያውቅ ለመሞት ጭምር ተዘጋጅቶ እንደነበር አስረድቷል፡፡

ወንጀል ሳይሠራ ነፃ ሆኖ መወያየትና መከራከር ኢሕአዴግን እንደ መድፈርና አልገዛምና የበላይነትን እንደ ማስፋፋት ስለሚቆጠር፣ ጥቃት እንደሚደርስበት ያውቅ እንደነበር ገልጾ፣ ለነፃነት የከፈለው መስዋዕት በመሆኑ እንደማይበዛ ተናግሯል፡፡ በእሱ ላይ የደረሰው እስራት፣ በደልና ስቃይ በቀለ ገርባና ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ በሌሎችም ወገኖች ላይ የደረሰ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከማዕከላዊ ወደ ማረሚያ ቤት ሲወርድ የታሰረው አገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ አደገኛ እስረኞች በሚታሰሩበት ‹‹ቅጣት ቤት›› በሚባል ማሰቃያ ቦታ መሆኑን ጠቁሞ፣ መዳፍ በምታክል ቦታ ላይ እስከ በር ድረስ በተነጠፈ ፍራሽ ላይ በወንጀል የማይመሳሰሉ 18 ታሳሪዎች እርስ በርስ ተደራርበው፣ በተለይ ለሁለት ዓመት ተኩል መቆየቱን አስታውቋል፡፡

አቶ አንዱዓለም ወደፊት በምን ሁኔታ እንደሚቀጥል ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ስለወደፊቱ ለመናገር ገና ነኝ፡፡ ታስሬ የነበረው ምንም መረጃ በሌለበት ቦታ ነው፡፡ መጀመርያ ጆሮና ዓይኔን ከፍቼ አካባቢውን መረዳት አለብኝ፡፡ እኔ ባልነበርኩበት ጊዜ የተፈጠረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበርና የአገሪቱን ሁኔታ በጥሞና ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ፤›› ከዚያ በኋላ የራሴን ትንተና ሠርቼ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ፤›› ብሏል፡፡

አቶ አንዱዓለም እንደሚለው ሕይወት ማለት ነፃነት ነው፡፡ ነፃነት የሌለበት ሕይወት ብዙም ትርጉም እንደማይሰጠውና ህሊናው እየወቀሰው ራሱን ሳይሆን ‹‹ቀንበር›› እየሳበ በአገሩ ላይ መኖር እንደማይፈልግም ተናግሯል፡፡ ‹‹ታሪካችን ሁሉ የአገዛዝ ነው፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ከእነ ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግሥት ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ድረስ የሚደረገው ትግል፣ በተለያየ መንገድ ይገለጽ እንጂ የዴሞክራሲ ትግል መሆኑን አብራርቷል፡፡ ብዙ መስዋዕትነት መክፈሉንና አገሪቱ በአንጡራ ሀብቷ ያስተማረቻቸውን ልጆቿዋን ማጣቷን አክሏል፡፡ በዚያ ጊዜ የተጀመረው የዴሞክራሲ ምጥ አለመወለዱና አገሪቱ አሁንም ጭንቅ ላይ በመሆኗ፣ መገላገልና ታሪኳን መቀየር እንዳለባትም ተናግሯል፡፡ ያ ደግሞ የሚሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ሲመጣ ነው ብሏል፡፡ አንድ ሕዝብ ትልቅ ነው የሚባለው ሉዓላዊ ሲሆንና አገርም ሉዓላዊ የሚባለው ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት ሲሆን መሆኑን አቶ አንዱዓለም አስረድቷል፡፡

ከነፃነትና ዴሞክራሲ ውጪ በሚመረተው ስንዴ ብዛት ወይም ሌላ ቁሳቁስ ሕዝብን ታላቅ ማድረግ ስለማይቻል፣ ሉዓላዊነቱ መከበር እንዳለበትም አውስቷል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ ሉዓላዊነታችን ተከብሮ አያውቅም፡፡ ይኼ ትልቅ ጎደሎነትና ክፍተት ነው፡፡ አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ በዚህ ዘመን አሳክተን ማለፍ አለብን፡፡ ይኼንን ለማሳካት ደግሞ ሰላማዊ ትግል ሁነኛው መንገድ ነው፤›› ብሏል፡፡ ዋጋ ቢያስከፍልም ከተመጣበት አዙሪት ተወጥቶ በሰላማዊ መንገድ መታገል አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን አክሏል፡፡ ለማሰርና ለመግደል መዘጋጀት እንደማያስፈልግ አክሏል፡፡

መንግሥት አሁን እስረኞችን መፍታቱንና ያለበትን ሁኔታ በሚመለከት አቶ አንዱዓለም፣ ‹‹ኢሕአዴግ የዴሞክራሲን ነገር ዙሪያውን ሲዞረው ነበር፡፡ ከ26 ዓመታት በኋላ ግን የዴሞክራሲ እንቅፋት መሆኑን አምኗል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮቹ ላይ ችግር መፍጠሩን በመገናኛ ብዙኃን ተናግሯል፤›› በማለት ይኼንን ያከብርለታል፣ ያደንቅለታል፡፡ ‹‹እየገደለ ራሱን እንደ መላዕክት ከመቁጠር ስህተቱን በትክክል ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ እስረኞችንም ለመልቀቅ የመጣበት ሒደት የሚበረታታ በመሆኑ ጥሩ ነው፤›› ሲል አቶ አንዱዓለም ተናግሯል፡፡ ‹‹አሸባሪ፣ አገር ከጂና ሌሎች የተለያዩ ነገሮችን መናገር ትርጉም የለውም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከችግር መውጣት አለብን፤›› ብሏል፡፡

አንዱ እየገነባ ሌላው እያፈረሰ፣ አንዱ እየተናገረ ሌላው እየተቃወመ፣ መደማመጥና መናበብ ሳይኖር ይችህን አገር እንገነባታለንና በርቀት እናስጉዛታለን ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑንም አክሏል፡፡

ኦሮሚያ ላይ ተጀመሩት ነገሮች ጥሩ መሆናቸውንና በሌሎችም ክልሎች ‹‹የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል፤›› የሚል አስተሳሰብ መምጣት እንዳለበት የተናገረው አቶ አንዱዓለም፣ በውጭው ዓለም ያደጉት አገሮችም የፖለቲካ ልዩነት የላቸውም ማለት ሳይሆን፣ ተቻችለውና በያገባኛል መንፈስ ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ባለሥልጣናት ላይ የታየው ሆደ ሰፊነት በኢሕአዴግም ላይ ሊተገበር እንደሚገባ አክሏል፡፡

ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ አብረውት እንዲመክሩና እንዲሠለፉ ቆራጥነት እንደሚስፈልገውና ከዚህም የሚበልጥ ዕድል እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ‹‹ከተወሰኑ አሥርት ዓመታት በኃላ ሁላችንም የለንም፤›› የሚለው አቶ አንዱዓለም፣ ግን ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የተሻለ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ መንበርከክና ማንበርከክን ትቶ ሆደ ሰፊ ሆኖ ለሁሉም የሚበጅ ነገር መሥራት ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ የተፈጠረን ችግር ለማክሸፍ ብሎ ኢሕአዴግ ማሰር መፍታቱን ከቀጠለ፣ የባሰ ነገር ውስጥ እንደሚገባና አደገኛ መሆኑንም አሳስቧል፡፡ አዲሱ ትውልድ ዝም ብሎ የሚቀበል ሳይሆን ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚለወጥና ፈጥኖ አሳቢ በመሆኑ፣ በአገሪቱም ላይ አዲስ ዘመን እንዲመጣ ተባብሮና ፈጥኖ የሚያስብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መሪ አስፈላጊ መሆኑን አቶ አንዱዓለም አስረድቷል፡፡

ወጣቱ ምን ማድረግ እንዳለበት ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ ወጣቱ ንብረት ማቃጠል የለበትም፡፡ ሥርዓቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም፣ ወጣቱ ግን መጠንቀቅና ከጥፋት መራቅ አለበት፡፡ በተለይ ወጣቱ፣ ‹‹ዘረኝነት የሚሉትን ነቀርሳ መቋቋምና ማስወገድ አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያንን ዘረኝነት አይገልጸንም፣ አይወክለንምም፤›› ብሏል፡፡ ‹‹አባቶች የዓድዋን ድል የተቀዳጁት፣ ከየአቅጣጫው ተጠራርተውና አንድ ሆነው ባደረጉት ተጋድሎ በመሆኑ፣ አብረው ሞተው አብረው የተቀበሩ እንጂ ዘር ቆጥረው አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፤›› ሲል አውስቷል፡፡ ከመቶ ዓመታት በኋላ ፍቅርና ታሪክ መሥራት ይገባል እንጂ፣ ሰው ዘሩ ተቆጥሮ ጥቃት ለመፈጸም መዘጋጀትና ማሰብ ፀያፍ መሆኑን አክሏል፡፡ ከዘረኝነት ታቅቦ ለሰላማዊ ትግል በመሠለፍ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ተቀዳሚና ዋናው ተግባር የወጣቱ መሆን እንዳለበት አቶ አንዱዓለም አብራርቷል፡፡