ተቃውሞ በኢትዮጵያ  ZACHARIAS ABUBEKER

በተከታታይ ዐብይ ፖለቲካዊ ክስተቶችን ባስተናገደው ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን በይፋ ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን ማጫር ጀምሯል ።

በአንድ በኩል ምንም እንኳ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ በየጊዜው እየተባባሰ መሄዱን እንዲሁም ብሔር ተኮር ግጭቶች እና ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ለአዋጁ አስፈላጊነት ምክንያት አድርጎ ቢጠቅስም፤ የተለያዩ መብቶችን የሚገድበው አዋጅን እንደመጨረሻ አማራጭ መቆጠር አለበት ከሚል ግንዛቤ በመነሳት፤ እነዚህን ፈታኝ ችግሮች የማስተናጋጃ ሌሎች መንገዶች አልነበሩም ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ሲሰነዘሩ ተሰምተዋል።

በሌላ ወገን የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አዋጁን ለመደንገግ የሚያበቃ አስገዳጅ ሁኔታ ያለመኖሩን በተናገሩ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሥራ መልቀቂያ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታክከው የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ “እዚህም እዚያም ከሚነሱ የፀጥታ ችግሮች” በስተቀር ምንም የተለየ ነገር ያለመኖሩን ከገለፁ በኋላ መታወጁ አግራሞትን አጭሯል።

በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች ለሃገራዊ መግባባት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በመፈታት ላይ ባሉበት ወቅት ፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ለመታሰራቸው ምክንያት ሆኖ የነበረው አዋጅ ተመልሶ መምጣቱ በገዥው ፓርቲ እና በመንግሥት ውስጥ የመልዕክት እንዲሁም የፍላጎት ወጥነት ላለመኖሩ እንደማሳያ የቆጠሩትም አሉ።

የአሜሪካ ኤምባሲ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ አኳኋን ጠንከር ባሉ ቃላት በተሞላው መግለጫዋ ከአዋጁ ጋር “በፅኑ እንደማትስማማ” ገልፃ ፤ ለአገሪቷ ችግር “የበለጠ እንጅ ያነሰ ነፃነት” መፍትሄ እንደማይሆን ምክረ ኃሳቧን ለግሳለች።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እና አዋጁን ለማስፈፀም የተቋቋመው ግብረ ኃይል ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ቅዳሜ ቀትር ላይ መግለጫ ከሰጡ በኋላ በአዋጁ እና ለጊዜውም ቢሆን አቅጣጫው ባልታወቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ያስነሳ ሆኗል።

ለባለፈው አመት የዘለቀው ተቃውሞ 
STRINGER

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ አቅሙ ምን ያህል ነው?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሚታወጅ መወራት ከጀመረበት ከባለፈው ሳምንት አጋማሽ አንስቶ ሁለቱ የገዥው ግንባር አባል ፓርቲዎች የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) እርምጃውን የመቃወም አዝማሚያ እንዳሳዩ የውስጥ አዋቂ ምንጮች አሉን የሚሉ ተንታኞች ሲናገሩ ቆይተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ግን እነዚህን አስተያየቶች በማጣጣል ውሳኔው ሙሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነትን እንዳገኘ ነው በመግለጫው የገለፁት።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እና የደህንነት ጉዳዮችን የሚያጠኑት አቶ ሃሌሉያ ሉሌ ሁለቱም አስተያየቶች ትክክል የመሆን ዕድል አላቸው ይላሉ።

ምንም እንኳ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ባለመኖራቸው በምን አኳኋን ውሳኔውን ባሳለፈው ስብሰባ ላይ እንደተሳተፉ ግልፅ ባይሆም፤ ምክር ቤቱ ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ ቢያሳልፍ የሚገርም አይሆንም የሚሉት አቶ ሃሌሉያ ይህ ግን ፓርቲዎቹ ሙሉ በሙሉ ውጥኑን ደግፈውታል ማለት ግን አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

ይህንን ሙግታቸውን ለማስደገፍ የሚያነሱት መከራከሪያ የፓርቲዎቹ ልብ እና አዕምሮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ አይገኝም በማለት ነው።

“በመጀመሪያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሉ ሰዎች በጣም ጠንካራ አይደሉም። ኦህዴድን እና ብአዴንን እንኳ ብናይ ጠንካራ የምንላቸው የሁለቱ ፓርቲዎች የፖሊት ቢሮ አባላት ክልል ላይ ነው ያሉት። የክልል ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአንፃሩ ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከትምህርት ተቋማት የብሔር ተዋፅዖ እየተጠበቀ የተመለመሉ በዛ ያሉ ባለሞያዎችን የያዘ አካል ነው” ይላሉ ተንታኙ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

የዚህ አንድ መገለጫ እና ምልክት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክልል መንግሥታት ከዚህ ቀደም ባልታየ መልኩ የፖለቲካ አቅም ማጎልበታቸው እንደሆነ ተንታኙ ይናገራሉ።

ሲራጅ ፈርጌሳ

የክልል መንግሥታት ተገለሉ?

አቶ ሲራጅ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር ጉዳዮችን ባስረዱበት መግለጫቸው ካብራሯቸው ጉዳዮች መካከል ድንጋጌውን በበላይነት ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ግማሽ ደርዘን አካባቢ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል የክልል ፕሬዚዳንቶችን ያለማካተቱ የአዋጁ ቅቡልነት እና ተፈፃሚነት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አቶ ሃሌሉያ ግምታቸውን ይገልፃሉ።

“አዋጁ ሲጀመርም የተቀባይነት ጥያቄ አለበት፤ የብሔር ፖለቲካ ገንኖ ባለበት ከባቢ ግብረ ኃይሉ ተመጣጣኝ የብሔር ውክልና ያለመያዙ ችግር አለው። ክልሎች ያለመካታተቸው ደግሞ በተቋም ደረጃና በመንግሥት ደረጃም ወካይ እንዳይሆን ያደርገዋል” ይላሉ ተንታኙ።

እነዚህ እውነታዎች በአዋጁ አፈፃፀም ላይ እንቅፋት ቢፈጥሩ የሚገርም አይሆንም ለተንታኙ። በዚህ ላይ በግንባሩ ውስጥ የአቅጣጫ መከፋፈል እና የፍላጎቶች ግጭት እንዳለ መታመኑ ጥርጣሬውን ያጎላዋል።

የሁለት አዋጆች ወግ

በ2009 መግቢያ ላይ ለስድስት ወራት የታወጀውና ቆይቶም ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ችግሮችን መቅረፍ መቻሉ ላይ ጥያቄ መነሳቱ ቢስተዋልም፤ ለጊዜውም ቢሆን ግን የነበረውን የፀጥታ ችግር ተግ ማድረጉ ይታወሳል።

ተመሳሳይ ውጤት እንዳይጠበቅ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ሲዘረዝሩ ከሁለት ዓመት በፊት እና አሁን ያለው መንግሥት አንድ ዓይነት ያለመሆኑን አቶ ሃሌሉያ ያነሳሉ። ይህም በተለይ በክልል መንግሥታት ላይ ይንፀባረቃል ባይ ናቸው።

ከዚህም ባሻገር “ሕዝብ ለሦስት እና ለአራት ዓመት መንግሥትን እየተቃወመ ሲቀጥል በራስ መተማመኑ እየጨመረ ፤ ጥያቄዎቹ ይበልጥ ግልፅ እየሆኑ፤ የተቃውሞ መዋቅር ኢመደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ ይሄዳሉ።” ይላሉ።

ቀዳሚው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከፍተኛ ሐገራዊ ድንጋጤ የቅስም መሰበር እና ሐዘን ከፈጠረው የእሬቻ ክብረ በዓል ክስተት ማግስት መምጣቱ ወዲያውኑ ለተፈጠረው ፀጥታ አንድ እርሾ እንደነበረም ጨምረው ይናገራሉ አቶ ሃሌሉያ።

ቀጣዮቹ አስራ አምስት ቀናት ከፍተኛ ወሳኝነት እንዳላቸው ይታመናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ መፅደቅ ይኖርበታል።

የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ ተንታኙ አዋጁ የፓርላማውን ይሁንታ አግኝቶ ቢፀድቅም እንኳ ለታሰበለት የስድስት ወራት ይዘልቃል የሚል እምነት የላቸውም።

ከባለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት አዋጁ እንደተባለውም ለስድስት ወራት ያህል ሥራ ላይ ከዋለ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር መገመት ይቻላል።

ይሁንና ገዥው ግንባር ጀምሬዋለሁ የሚለው የመታደስ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለመገመት አዳጋችነቱ ከወትሮም እየበረታ የመጣውን የፖለቲካ መልክዓ ምድር ላይ ምንም ዓይነት አሻራ እንደሚያሳርፍ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።