• ሚኒስትሩንም ጄኔራሉንም፣ ወጣቱንም ሽማግሌውንም፣ ምሁሩንም ተመራማሪውንም የካህኑ ልጅ አድርጎ እግዚአብሔር ሰጥቶአል፤
  • የምእመናን የቅርብ ጠባቂ፣ ከላይ ያሉት ባለሥልጣናት ሳይኾኑ በነፍስ አባትነት ደረጃ በቅርብ ያሉ ካህናት ናቸው፤ በሌላ ማመካኘት ተቀባይነት አይኖረውም፤
  • ሌላው በራሱ ስሕተት ሲጠየቅ፣ ካህኑ ግን ሕዝበ እግዚአብሔርን የመጠበቅ ሓላፊነት ስለተሰጠው፣ በሕዝቡ ስሕተት የመጠየቅ ግዴታም አለበት፤
  • ወንድማማቾች ሲነታረኩ፣ መስቀሉን ይዞ ከመካከል በመግባት ስመ እግዚአብሔርን ከጠራ የማይሰማ የለም፤ ችግሩ ከአሰሚው ነው፤

†††

  • የጋራ ሓላፊነታችንን አልተወጣንም፤ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ ሀብተ ክህነት ያለው ሁሉ ለሰላምና ለሕዝብ አንድነት መጠበቅ ማስተማርና መስበክ አለበት፤
  • ክህነታዊ ተልእኮውን በስኬት ለማከናወን፣ በተሟላ መንፈሳዊ ሰብእና መቆም ያስፈልጋል፤ በግዴለሽነትና በኢቀኖናዊነት ከተፈጸመ ተጠያቂነቱ ከባድ ነው፤
  • ያለሰላም ህልውና፣ ያለሕዝብ አንድነትና ያለሀገር ልማት ቀጣይነቷ አስተማማኝ የኾነች ቤተ ክርስቲያን ልትኖር እንደማትችል ካህናት ማስተዋል አለብን፤
  • ለምትወደንና ለምንወዳት ቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል ስንል በሰላሙ ጥበቃ፣ በሀገር አንድነት፣ በሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና በልማቱ ሥራ ያለመታከት እናስተምር!!

†††

pat anba mathias 5th enth anniv

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

“አንትሙሰ ጽንዑ ከመ ዕብን መንፈሳዊ ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት ከመ ታቅርቡ ወታዕርጉ መሥዋዕተ መንፈሳዌ ዘይሰጠወክሙ እግዚአብሔር በእደዊሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ =

እናንተስ እንደ መንፈሳዊ ዕብነ ማዕዘንት ኹኑ፤ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ የሚቀበላችሁን መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡና ታሳርጉ ዘንድ ቅድስትና ንጽሕት ለኾነች ክህነት መንፈሳዊ ታቦት ኹኑ፡፡” (1ኛጴጥ.2፥5)

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

እግዚአብሔር የጎደለውና የሚጎድለው የሌለ ምሉእ ጸጋ ወጽድቅ አምላክ እንደኾነ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንማራለን፡፡ ይኹን እንጅ ደስ የሚያሰኘውና የማያሰኘው አካሔድና አቀራረብ እንዳለው ከጥንት ጀምሮ ገልጾአል፡፡ እግዚአብሔር ኹሉን የፈጠረና ያስገኘ፥ ኹሉን የሚያስተዳድርና የሚመግብ፥ ኹሉን የሚያስተባብርና የሚቆጣጠር፥ የፍጥረታት ኹሉ ባለቤት፥ የበላይ መሪና ገዥ በመኾኑ ይህን መለኰታዊ ኃይሉን ዐውቀን እንድንከተለው ይፈልጋል፡፡

አምልኮና ምስጋና፥ መታዘዝና ኅብረትም ከፍጡራኑ ይጠብቃል፡፡ አምላከ አማልክት እግዚአብሔር ከሰው የሚፈልገውን ኹሉ በቅዱስ መጽሐፍ በዝርዝር የገለጸ ሲኾን፤ ፈቃዱን የሚያስፈጽሙ አካላትንም በልዩ አጠራር እየሾመ ወደ ሥራ ሲያሠማራ፥ በሓላፊነትም ሲያስቀምጥ ኖሮአል፤ ለወደፊቱም እንደሚቀጥልበት በቃሉ አረጋግጦአል፡፡

ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የኾነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ እግዚአብሔር ደስ ከሚሰኝባቸው ነገሮች አንዱን ጠቅሶ ሲያስተምር፦ “መንፈሳዊ መሥዋዕትን ማቅረብ” እንደኾነ ይነግረናል፡፡ መሥዋዕት ከተነሣ ዘንድ ካህን ማስፈልጉ የግድ ነውና፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናትም ቅዱሳን ይኾኑ ዘንድ በመንፈሳዊ ዕውቀትና ብቃት መገንባት ሐዋርያው አበክሮ ያስተምራል፡፡

የክህነት አገልግሎት ከእግዚአብሔር ጋራ በቀጥታ ግንኙነት ያለው በመኾኑ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ከዚህ መረዳቱ አይከብድም፡፡ ቅድስና፥ ንጽሕና፥ ሓላፊነት፥ ጥንቃቄና ፈሪሀ እግዚአብሔርን ገዢ ባደረገ መልኩ ክህነታዊ አገልግሎት ሲከናወን የሚሰጠው ዋጋ ታላቅ የመኾኑን ያህል፥ በግድየለሽነት ሃይማኖቱና ቀኖናው ከሚያዘው ውጭ ከተፈጸመ ተጠያቂነቱ ከባድ እንደኾነ በቅዱስ መጽሐፍ የተገለጸ እውነት ነው፡፡

ሌላው ሰው የሚጠየቀው ራሱ በፈጸመው ስሕተት ሊኾን ይችላል፤ ካህን ግን ሕዝበ እግዚአብሔርን የመጠበቅ ሓላፊነት የተሰጠው ስለኾነ በሕዝቡ ስሕተት የመጠየቅ ግዴታም አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህ በዓለ ሢመተ ክህነት፣ ማስታወስና ማሰላሰል ያለብን እኛ ካህናት ልንሠራው ከሚጠበቅብን የሠራነው ምን ያህል ነው? የሚለውን ነው፡፡

ምናልባት አንዳንድ ሰዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት ከላይ በተቀመጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ብቻ እንዳለ ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ያለው አስተሳሰብ የጠሳሳተና ሌላውን ሳይኾን ራስን ለድክመት የሚዳርግ ኃጢአት ከሚኾን በቀር በእግዚአብሔርም ኾነ በሕግ ፊት ማምለጫ ሊኾን ከቶ አይችልም፡፡

ይልቁንም ጌታችን በቅዱስ ወንጌል በግልጽ እንዳስተማረን ባለአምስት መክሊትም፥ ባለኹለት መክሊትም፥ ባለአንድ መክሊትም እንደየአቅማቸው በተሰጣቸው ስጦታ መሠረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር፥ በጎቹን በቅርብ የሚጠብቅ የበጎች ባለቤት ሳይኾን ቀኑን ሙሉ ሳይለያቸው የሚውል እረኛው ነው፡፡ የምእመናን የቅርብ ጠባቂም ከላይ ያሉት ባለሥልጣናት ሳይኾኑ በነፍስ አባትነት ደረጃ በቅርቡ ያሉ ካህናት ናቸው፡፡ ይህም ከኾነ በእጅ ያሉ ምእመናንን ነቅቶና ተግቶ መጠበቅ ሲቻል በሌላ እያመካኙ ስንፍናን ማስተናገድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

ከዚህ አኳያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እያንዳንዱን ምእመን ከነቤተሰቡ የሚጠብቅ ካህን መድባ እያለ እነ ገብረ ሥላሴ፣ እነ ወለተ ሥላሴ በተኵላ ሲነጠቁ ካህኑ የት ሒዶ ነው? ሰላም፥ ፍቅርና መግባባት በወንድማማቾች መካከል እየተሸረሸረ የጎሪጥ መተያየቱ ሲሰፋ ካህኑ የት ሒዶ ነው? ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ለሦስት ሺሕ ዓመታት እንደ ዝናመ ክረምት ያለማቋረጥ በፈሰሱባት ምድር አንድነቱና ማኅበራዊ ትስስሩ እንደ ብረት የጠነከረ ሕዝብ ያላት ሀገር ወዲህ ወዲያ የሚያወዛውዝ ነፋስ በየት ገባባት? የዚህ ክፍተት ተጠያቂስ ከካህን በቀር ማን ሊኾን ይችላል? የሚል ጥያቄ ወቅታዊ ኾኖ ይገኛል፡፡

ምክንያቱም እግዚአብሔር ባለሥልጣኑንም፥ ምሁሩንም፥ ተመራማሪውንም ኹሉ የሰጠ ለካህን በመኾኑ ነው፤ ሚኒስትሩንም ጄኔራሉንም የካህን ልጅ አድርጎ እግዚአብሔር ሰጥቶአል፤ ሽማግሌውንም ወጣቱንም፥ ወንዱንም ሴቱንም፥ ሀብታሙንም ድኻውንም፥ ገበሬውንም ነጋዴውንም ኹሉ ለካህን ሰጥቶአል፡፡ ሌላው ኹሉ ከካህን በኋላ ነው፡፡

ሕዝቡም ይህን በሚገባ ስለሚያውቅ አልቀበልም፤ አልሰማም ብሎ አያውቅም፡፡ ችግሩ ከሰሚው ሳይኾን ከአሰሚው እንደኾነ ማየቱ አይከብድም፡፡ ኹለት ወንድማማቾች ሲነታረኩ፣ ካህኑ እንደ አባቶቹ መስቀሉን ይዞ በመካከል በመግባት ስመ እግዚአብሔርን ከጠራ የማይሰማ እንደሌለ በርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ታድያ ይህን የሰላም መስቀል ይዘን ሕዝቡን የሰላም ኃይል ማድረግ እንዴት አቃተን?

28471256_1827435253943065_4663614715656667136_n

ኹለት ወንድማማቾች ሲነታረኩ፣ ካህኑ እንደ አባቶቹ መስቀሉን ይዞ በመካከል በመግባት ስመ እግዚአብሔርን ከጠራ የማይሰማ እንደሌለ በርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ታድያ ይህን የሰላም መስቀል ይዘን ሕዝቡን የሰላም ኃይል ማድረግ እንዴት አቃተን?ችግሩ ከሰሚው ሳይኾን ከአሰሚው እንደኾነ ማየቱ አይከብድም፡፡ (ፎቶ: Birhan Bihil)

ከዚህ አኳያ ሲመዘን፣ የጋራ ሓላፊነታችንን በመወጣት ረገድ ክፍተት እንዳለ እየታየ ነውና ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሀብተ ክህነት ያለው ኹሉ፣ በዚህ ዘመን ከምንም በላይ ለሰላምና ለሕዝብ አንድነት መጠበቅ ያለዕረፍት ማስተማርና መስበክ አለበት፡፡ ይህን አምላካዊ ተልእኮ በስኬት ለማከናወንም፣ በተሟላ መንፈሳዊ ሰብእና መቆም ያስፈልጋል፡፡ “መሥዋዕትን ሳይኾን ምሕረትን እወዳለሁ” ብሎ ራሱ የመሰከረለትና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የይቅርታ መንፈሳዊ መሥዋዕት ማለት ይህ ነውና፡፡

የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የኾን ካህናት፣ በውል ማወቅና ማስተዋል ያለብን፣ ያለሰላም ህልውና፥ ያለሕዝብ አንድነትና ያለሀገር ልማት ቀጣይነቷ አስተማማኝ የኾነች ቤተ ክርስቲያን ልትኖር የማትችል መኾኑን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከሌለች ደግሞ፣ የምድሩም የሰማዩም ቤታችን ይናዳል፡፡ ይህ እንዳይኾን፣ ለምትወደንና ለምንወዳት ቤተ ክርስቲያን ህልውና መቀጠል ስንል በልማቱ ሥራ፥ በሰላሙ ጥበቃ፥ በሀገር አንድነት፥ በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ያለመታከት ማስተማር፥ መምከር፥ ማሳመን ይጠበቅብናል፤ በማለት መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት