በርካታ ምሁራንና አክቲቪስቶች ለአቶ ለማ መገርሳ ደብዳቤ ጻፉ – በኦሮሚያ ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆንና የሌሎች ማህበረሰባት መብት እንዲጠበቅ በመጠየቅ

ደብዳቤዉ በፒ.ዲ.ኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ጉዳዩ – በክልሉና ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ ኦሮምኛም በግዕዝ ፊደል ትምህርት እንዲሰጥ ስለመጠየቅ

ለተከበሩ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል መንግሥት ሊቀመንበር

ክቡር ሊቀመንበር ሆይ፦

በቅድሚያ እርስዎ፣ የክልል መንግሥትዎና ድርጅትዎ ኦህዴድ በአገራችን ያለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማሕበረሰባዊ ቀውሶችን ለማስወገድ በቀዳሚነት እያደረጋችሁት ስላለው ታሪካዊና አስደናቂ ተግባራት ያለንን ትልቅ ምስጋናና አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን። ቀደም ሲል ከነበሩ አመራሮች በተለየ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ መከፋፈል፣ ልዩነት፣ ዘረኝነት ተወግዶ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መተሳሰብና መያያዝን ለማምጣትና የጥል ግድግዳዎችን ለማፍረስ በመነሳታችሁ፣ ዘርና ኃይማኖት ሳይለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን እየሰጣችሁ ነው። ሕዝብ በፍቅር፣ በትህትና፣ በፍትህና በእኩልነት ሊያስተዳድረው የተነሳን አመራር ያከብራልና።

የጀመራችሁትን መልካም እንቅስቃሴ ለማገዝ፣ መቀራረቡንና አንድነቱን ለማፋጠን የተነሳችሁለትን አላማ እንድታሳኩ እጅግ በጣም ቁልፍና ጠቃሚ ለሆኑ ጉዳዮች ክቡርነትዎ ትኩረት ይሰጡት ዘንድ ይኸንን ጽፈናል። ከዚህ ደብዳቤ ጋር ግዕዝን በኦሮምኛ መጻፍ በብቃትና በአመችነት አንጻር የተሻለ እንደሆነ የሚያስረዳ ጥናታዊ ሰነድ አካትተናል።

አንደኛማርኛን በኦሮሞ ክልል ትምህርት ቤቶች ስለማስተማር

ቋንቋ መግባቢያ ነው። ቋንቋን ማወቅ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በኦሮሞ ክልል ብዙ ወገኖቻችን ኣማርኛ የማንበብና መጻፍ ችግር አለባቸው። ለብዙ ዓመታት ኣማርኛ ትምህርት አይሰጥም ነበር። መሰጠት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሚሰጠው ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ነው። ኣማርኛ  የፊዴራል ቋንቋ ነው። በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በኣማራ ክልል፣ በደቡብ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በጋምቤላ ክልል ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ ነው። በኦሮሞ ክልል ውስጥ እንደ አዳማ ባሉ ከተማዎችም የግል መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙት በኣማርኛ ነው። ኣማርኛ አለመጻፍና አለማንበብ የኦሮሞ ክልል ነዋሪዎችን ክፉኛ ጎድቷል። ሥራ የማግኘት፣ የመሻሻል፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ የማደግ ዕድላቸውን በጣም አጥብቧል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ባለባቸው ቦታዎች መወዳደርና መሥራት ካልቻሉ ሕይወታቸውን እንዴት ነው ማሻሻል የሚችሉት?

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ለኣማራ ቴሌቪዥን ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኣማራ ክልል ኦሮምኛ ማስተማር እንደሚያስፈለግ ገልጸው፣ በኦሮሞ ክልል ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ኣማርኛ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት ተናግረው ነበር። በኣማራ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደል እንዲሰጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲደርስ አድርገናል። በኦሮሞ ክልልም ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የኣማርኛ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረጉ ትልቅ ትኩረት ይደረግበት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

ሁለተኛየኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መሻሻል አስፈላጊነት

ክቡርነትዎና የትግል አጋርዎ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ብዙ ጊዜ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ክልል እንደሆነች ገልጻችኋል። የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት ግን እናንተ እየደጋገማችሁ በግልጽና በአደባባይ የገለጻችሁትን የሚያንጸባርቅ አይደለም። የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስምንት፣ የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው ይላል። ይህ ማለት የኦሮሞ ክልል ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ እንደሆነ፣ ኦሮሞ ክልል የኦሮሞዎች እንደሆነች፤ ሌላው በክልሉ የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነው ማሕበረሰብ ደግሞ፣ በኦሮሞ ማሕበረሰብ ፍቃድ እንደሚኖር፣ እንግዳ እንደሆነና የክልሉ የባለቤትነት መብት እንደሌለው የሚያመለክት ነው።

ይህ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ፡ ክቡርነትዎ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት ያሉትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ በሆነ መልኩ የዜጎችን የሰብአዊና የእኩልነት መብቶችን የሚገፍ ነው። ዜጎች በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል የመኖር፣ የመሥራት፣ የመነገድ፣ የመማር፣ የማስተማር፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብቶቻቸው ሊጠበቁላቸው ይገባል። የክልሉ ሕገ መንግሥት ማንም ኢትዮጵያዊ፣ በሁሉም መስፈርት ከኦሮሞው እኩል እንደሆነ የሚያረጋግጥ፣ የሌሎች ማሕበረሰባት በክልሉ የመኖር ዋስትናን የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ሆኖ መሻሻል አለበት ብለን እናምናለን። ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ስምንት የኦሮሞ ክልል ነዋሪ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው በሚል ቢሻሻል ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለን እንመክራለን።

ሦስተኛየክልሉ እንዲሁም ከመቶ በላይ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎች በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ማርኛም የሥራ ቋንቋ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።

የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፭ ኦሮምኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል። አንቀጽ ፴፫ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆነና የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ ወይም ተቀጥሮ የመሥራት መብት አለው ሲል ለክልሉ መንግሥት ኃላፊነት መመረጥ ወይም በክልሉ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥሮ መሥራት የሚችሉት ኦሮምኛ የሚናገሩ ብቻ መሆናቸውን በግልጽ ያስቀምጣል።

ይፋዊ የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ያለው፣ ከ፲፪ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ መስሪያ ቤት ይፋ የሆነው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ነው። በዚህ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት በወቅቱ ከተሸነሸኑት ሃያ የኦሮሞ ክልል ዞኖች በስምንቱ (ጂማ ልዩ፣ አዳማ ልዩ፣ ቡራዩ ልዩ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ጉጂና አርሲ ዞኖች) ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ከኣስራ አምስት በመቶ በላይ ናቸው። ይህ ቀላል ቍጥር አይደለም። በአዳማና ጂማ ልዩ ዞኖች ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ሰባ አራት እና ስድሳ በመቶ ናቸው። አዲስ አበባ በአካባቢዋ ከአሉ የኦሮሞ ክልል ዞኖች ጋር የተሳሰረች መሆኗ ይታወቃል። በአዲስ አበባ የሚኖረውን ሕዝብና የኦሮሞ ክልል ነዋሪ አንድ ላይ ብንደምራቸው ከመቶ ኣስራ አምስት የሚሆኑት ኦሮምኛ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አይደለም። አዲስ አበባ፣ አዳማና ቡራዩ ልዩ በኦሮሞ ክልል የሸዋ ዞኖችን ሁሉ ብናካትት ኣርባ ኣራት ከመቶ የሚሆኑት፣ አዲስ አበባ፣ ቡራዩ ልዩ፣ አዳማ ልዩና ምሥራቅ ሸዋ ዞንን ስንደምር ሰባ ኣንድ ከመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ አይደለም። ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት፣ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፭ እና አንቀጽ ፴፫፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያንን የመሥራትና የመመረጥ፣ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታቸውን የሚገፍ ነው። በአገራቸው እንደ ባይተዋር እንዲሆኑ ያደረገ ነው።

ላቲን፣ ላለፉት ፳፯ ዓመታት እንደ ትምህርት ይሰጥ ስለነበረና በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች የሚያውቁትና የተማሩት እርሱን በመሆኑ ብዙዎች ላቲን እንዲቀጥል ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። ሆኖም ግን በላቲን መጠቀሙ የአብዛኛው የኦሮሞ ማሕበረሰብና በተለይም በክልሉ ያሉ ኦሮምኛ የማይናገሩ ዜጎችን ፍላጎት ያካተተ ነው ብለን አናስብም።

በላቲን መጠቀም የሚፈልግ ማሕበረሰብ አለ፣ ላቲን የመብት ጥያቄ ነው ከተባለ፣ ቢያንስ ሚዛናዊነትን በማሳየት ኦሮምኛ በግዕዝ መጠቀም የሚፈልጉ የክልሉ ነዋሪዎችን ፍላጎት ማስተናገድ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

ከ፳፯ ዓመታት በፊት ላቲን ለኦሮምኛ ሲመረጥ የሕዝብ አዎንታ አልተጠየቀም። ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ላቲንና ግዕዝን እኩል በጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ በጥናት ላይ የተመሠረተ ንፅፅር አልተደረገም። በወቅቱ በኃላፊነት ላይ የነበሩ፣ ከሌላው ማሕበረሰብ የተለየ የኦሮሞ ማንነትን ለመፍጠር የፈለጉ፣ የኦሮሞ ልሂቃንና ፖለቲከኞች በሕዝቡ ላይ የጫኑት ውሳኔ ነው። በመሆኑም “አንቀጽ ፭ ኦሮምኛና ኣማርኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ። ኦሮምኛም የሚጻፍበት ፊደል በሕዝብ ይወሰናል በሚል፣ አንቀጽ ፴፫ ደግሞ በክልሉ ውስጥ ነዋሪ የሆነና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ወይም ሕዝባዊ ሥራ ተመርጦ የመሥራት መብት አለው። ለሥራው ብቃት ያለው ማንም ኢትዮጵያዊ በክልል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የመሥራት መብት አለው” በሚለው ቢሻሻል ጥሩ ይሆናል ብለን እናስባለን።

አንዳንድ ወገኖች ለምን በኣማራ ክልል ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ አይሆንም? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ። ኦሮምኛም ሆነ ሌላ ቋንቋ በኣማራ ክልልም የሥራ ቋንቋ መሆኑ በመርህ ደረጃ ችግር የለውም። አስፈላጊ ከሆነ በሕዝብ ምርጫ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ግን አስፈላጊ ነው ወይ? የሚለው መታየት ያለበት ጥያቄ ነው።

በኦሮሚያ የሸዋ ዞኖችና አዲስ አበባ ኦሮምኛ አንደኛ ቋንቋቸው ያልሆኑ ነዋሪዎች ብዛት የሚያሳይ

ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ የሚከተለውን መረጃ እንመልከት። በኦሮሞ ክልል ከላይ እንደገለጽነው በሁለት ዞኖች ኦሮምኛ ውስጥ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ኣማርኛ ተናጋሪዎች ከግማሽ በላይ ናቸው። በኦሮሞ ክልል ካሉ ሃያ ዞኖች፣ ኦሮምኛ የማይናገሩ ኣምስት  ከመቶ በታች የሆኑበት ዞን አንድ እርሱም የምእራብ ወለጋ ዞን ነው። ኦሮምኛ የማይናገሩ ኣስር ከመቶ በታች የሆኑባቸው ዞኖች ደግሞ አራት ብቻ ናቸው፦ ቀለም ወለጋ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋና ኢሉባቦር።

በኣማራ ክልል ካሉ ኣስራ ሁለት ዞኖች ከአንድ ዞን በስተቀር ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከአምስት ከመቶ በታች ናቸው። በኣማራ የኦሮሞ/ከሚሴ ዞን ሰማኒያ ከመቶ፣ በአርጎባ ልዩ አራት  ከመቶ፣ በባሕር ዳር ልዩ ሁለት ከመቶ፣  በደቡብ ወሎ ሁለት  ከመቶ ሲሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በተቀሩት ስምንት  ዞኖች ከመቶ አንድ በታች ናቸው። እንደዚህም ሆኖ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በበዙበት የኣማራ ክልል የኦሮሞ ዞን፣ የክልሉ መንግሥት የኦሮምኛ ተናጋሪዎችን መብት በማክበር፣ በኦሮምኛ እንዲማሩ፣ በኦሮምኛ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

አራተኛላቲን የኦሮምኛን እድገት ክፉኛ የሚገታ ነው።

ዜጎች ብዙ ቋንቋዎች ባወቁ ቍጥር ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም። ኣማርኛ የኣማራዎች ብቻ ቋንቋ እንዳልሆነ ኦሮምኛም የኦሮሞዎች ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ናቸው። ኦሮምኛ በኦሮሞ ክልል ብቻ መወሰን የለበትም በሚል በዐማራ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ ፊደል እንደ ትምህርት እንዲሰጥ የሚጠየቅ ደብዳቤ፣ ከተያያዥ ጥናታዊ ሰነድ ጋር፣ ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ልከናል። ለአቶ ገዱ የላክነውንም ሰነድ ለክቡርነትዎ ግላባጭ አድርገናል።

ለተከበሩ አቶ ገዱ የጻፍነውን ደብዳቤ ተከትሎ የደረሱን አስተያየቶች አንዱ በኣማራ ክልል ኦሮምኛ ተማሩ ስትሉን፣ ለምን በኦሮሞና የሌሎች ማሕበረሰባት መብት እንዲከበር አትሠሩም? ለምን መጀመሪያ በኦሮሞ ክልል ኦሮምኛ በግዕዝ እንዲጻፍ አትጠይቁም የሚል ነበር። ኣማርኛ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ነው እየተባለ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መማር ተትቶ ኦሮምኛን ሌሎች ይማሩት ማለት ብቻ በቂ አይደለም።

ሌላው ኦሮምኛን ለመማር በኣማራ ክልል በሚኖረው ማሕበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ተረድተናል። ሕዝቡ ኦሮምኛን የራሱ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ሆኖም ግን ኦሮምኛን ለመማር ትልቅ ፍቃደኝነት ቢኖርም፣ ካገኘናቸው አስተያየቶች ለመረዳት እንደቻልነው፣ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል፣ በላቲን ፊደል ለመማር ፍላጎት የለም ብቻ ሳይሆን፣ ትልቅ ተቃውሞ ነው ያለው። ኦሮምኛ በላቲን ፊደል የሚጻፍ ከሆነ ከኦሮሞ ክልል ውጭ የማደግ፣ የመስፋፋት ዕድሉ እጅግ በጣም የመነመነ ነው የሚሆነው። ያለ ፍላጎት ደግሞ በዜጎች ላይ ምንም ነገር መጫን አይቻልም። “ኦሮምኛ የእኛ፣ ላቲን የሌላ” ነው እየተባለ ያለው።

የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፣ በሕዝብ ይሁንታ ኦሮምኛ ከኣማርኛ ጋር የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅትዎ እንደሚሠራ ገልጿል። የሕዝብ ይሁንታን አስፈላጊነት ድርጅትዎ ማስመሩ ሊያስመሰግነው ይገባል። ኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ የኢትዮጵያ ፴፭ ከመቶ አካባቢ ነው። ከእዚህ ኦሮምኛ ተናጋሪ በላቲን ፊደል መጻፉን የሚደግፍ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም፣ ከግማሽ በላይ ይሆናል ብለን ግን አናስብም። ያ ማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከሦስት አራተኛው በላይ የላቲን ፊደልን የሚቃወም ነው ማለት ነው።  ሦስት አራተኛው ተቃዋሚ በሆነበት በላቲን የሚጻፍ ኦሮምኛን የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሕዝብ ይሁንታን ማግኘት የማይታሰብ ነው።

ኦሮምኛ በግዕዝ ከተጻፈ ግን በኣማራ ክልል ካገኘነው አስተያየት ለመረዳት እንደቻልነው፣ ብዙዎች ሳይገደዱ፣ ደስ ብሏቸው ቋንቋውን ይማራሉ። ቋንቋውን የሚናገሩ ይበዛሉ። ቋንቋው የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋም እንዲሆን የሕዝብን አዎንታ ለማግኘት ቀላል ይሆናል።

አምስተኛየግዕዝ ፊደላትን መጠቀም የአገር ቅርስ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተሻለም ነው።

ምዕራባውያን ለጥቁር ሕዝብ መሸጥና መዋረድ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሙበት አንዱና ትልቁ መከራከሪያቸው “ጥቁሮች የራሳቸውን ስነፅሁፍና ፊደል መቅረፅ ያልቻሉት በዕውቀት ዝቅተኞች ስለሆኑ ነው” የሚለው ነው። ይኸን ትርክት ውድቅ ለማድረግ፣ የግዕዝ ፊደላችን ወደቀረው አፍሪቃ እንዲስፋፋ መታገል ነበረብን። ሆኖም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች በመወጠራችንና በሃገራችን የሰፈነው የማንነት ፖለቲካና ከኢትዮጵያ የተለየ ማንነት ይፈልጉ በነበሩ አክራሪ ብሔርተኞች አሉታዊ ጫና ምክንያት አላደረግነውም። እንኳን ወደ አፍሪካ አገሮች ግዕዝን ልንወስድ ቀርቶ በአገራችን ምዕራባውያን ፊደል፣ ላቲን፣ ለአንዳንድ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እየተጠቀምን ነው።

አንዳንድ ወገኖች የግዕዝ ፊደልን የአንድ ብሔረሰብ ርስት አድርገው የመቍጠር ዝንባሌ ሲኖራቸው አንዳንዶች ደግሞ የግዕዝ ፊደል ብቃት እንደሌለው አድርገው ያስባሉ። የላቲን ፊደላት ተናጋሪው እንደሚናገረው አይጻፉም። የቃላት አጻጻፍን/ሥርዐተ ኆሄያትን ለማወቅ ችግር ነው። በኢትዮጵያ ፊደላት ግን ሰዉ እንደሚናገረው ስለሚጻፉ፣ የሥርዐተ ኆሄያት/የቃላት አጻጻፍ የፊደል ስሕተት ሊሠራባቸው አይችልም። ስለዚህም ከላቲን ፊደል ይልቅ ግዕዝ የበለጠ ይመረጣል፣ ይልቃልም።

ኤርትራውያን መቼ የግዕዝን ፊደል አንፈልግም አሉ? እንዲያውም እነሱ ቀደም ሲል በጣልያን ቅኝ ግዛት ተገዝተው ስለነበር፣ በላቲን እንቸክችከው ቢሉ፣ ጥሩ ሰበብ በሆናቸው ነበር። ከላቲን ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ፊደላት ብዙ ጥቅሞች እንዳላቸው በኋላ ግን ግዕዝ መሻሉን ተገንዝበው ወደ ግዕዝ ተመልሰዋል። ግዕዝ የአማራ ማሕበረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅርስ ነው። ከአረብኛ ውጭ ብቸኛው ጥንታዊ የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሃዲይኛ፣ ከንባትኛ፣ ኑኧርኛ፣ አኝዋክኛ፣ አገውኛ፣ አደሪኛ፣ ስልጢኛ.. በአሁኑ ጊዜ የግዕዝ ፊደላትን ነው የሚጠቀሙት። አደሪኛ ተናጋሪዎች ለአስር ዓመታት ላቲን ይጠቀሙ የነበረ ቢሆንም ግዕዝ ይሻላል ተብሎ ወደ ግዕዝ ተዙሯል።

ኢትዮጵያ በአባቶቻችንና እናቶቻችን መስዋዕትነት ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች አገር ናት። የራሷ ባህል፣ የራሷ ቋንቋዎች፣ የራሷ ፊደል፣ የራሷ ቅርሶች አሏት። በአገራችን የሌለን ነገርና፣ ለአገር የሚጠቅም ከሆነ፣ ከባእድ አገር ብንወስድ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ግን የተሻለ ነገር ከእኛ ጋር እያለ የሌሎችን ማምጣት ተገቢ አይደለም። ፊደል እንደሌለንና ቅኝ የተገዛን ይመስል፣ የእኛን የተከበረ ፊደል ጥለን ላቲንን ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጠቀም አግባብ አይደለም።

ስድስተኛየግዕዝ ፊደላትን ለኦሮምኛ ስለመጠቀም።

አፋን ኦሮሞ በላቲንም በግዕዝም ይጻፋል። በኦሮሞ ክልል በተለይም ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የተወለዱ ወገኖች አፋን ኦሮሞን በላቲን ነው የሚጽፉትና የሚያነቡት። ሆኖም ላቲኑ በጣም ውስንነት አለው። በኦሮሞ ክልል የሚኖሩ ሌሎች ማሕበረሰባትና ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑ ኦሮሞዎች ግዕዝ ፊደልን ማንበብ ነው የሚቀናቸው። ቋንቋው በላቲኑ ምክንያት በኦሮሞ ክልል የከተወሰኑ ወገኖች አጥር ውጭ ሊያድግ አልቻለም።

ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ለክቡርነትዎ በታህሳስ ወር ፳፻፲ ዓ.ም. በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ ለኦሮምኛ ከላቲን ይልቅ ግዕዝን መጠቀም ምን ያህል በቃላት ቁጠባ፣ በትምህርት ቅልጥፍና፣ በቋንቋ ጥናት ጥበብ እና በሳይንስ አንጻር የተሻለ መሆኑን አስነብበውናል። ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የጻፉትን፣ ዶ/ር ኣበራ ሞላ እና ሌሎች በርካታ ምሁራን ያደረጉትን ጥናት በተወሰነ መልኩ ያካተተ ተያያዥ ሰነድ ማቅረባችን ይታወሳል። ይኸው ሰነድ ተሻሽሎ ከእዚህ በታች ቀርቧል።

በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ በግዕዝ ፊደላት መጫፈ ቁልቁሉ ተብሎ ከተተረጐመው የኦሮምኛ መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ የተወሰዱ ሁለት ገፆችን አብረን አያይዘናል።

ክቡርነትዎ ሆይ!

እርስዎ እንደሚገነዘቡት፣ በባዕዳን ፊደል የሚጽፉ አፍሪቃውያን፣ በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች ሲገዙ የነበሩና ራሳቸው የፈለሰፏቸው የፊደላት አማራጭ ያልነበራቸው ሕዝቦች ናቸው። እኛ በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ደምና አጥንት ነፃነታችን ተከብሮልን የኖርንና አኩሪ ቅርስ የሆነ የራሳችን ፊደል ያለን ሕዝብ ቅኝ እንደተገዙትና እንደተዋረዱት ያልታደሉ ሰዎች ልንሆን አይገባም። በእዚህና እላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች፣ እንዲሁም ስለ ክብራችንና ማንነታችን ሲባል እርስዎና የአስተዳደር ባልደረቦችዎ፣ አፋን ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደመሆኑ በኢትዮጵያዊ ፊደል በግዕዝ እንዲጻፍ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቅዎታለን። በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት፣ በኦሮሞው ቄስ አባ ኦነሲሞስ ነሲቡ፣ በግዕዝ ፊደላት “መጫፈ ቁልቁሉ” የኦሮምኛ መጽሓፍ ቅዱስ ተተርጕሟል። የዛሬ ፻፳ ዓመት እንኳን፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያህል በራሳችን ፊደላት መፃፍ ከቻልን፣ አሁንማ በዘመነ-ቀመር፣ በቀላሉ ኦሮምኛን በግዕዝ ኢትዮጵያዊ ፊደል ያለችግር መክተብ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። ዋናው ቀና ልቦና፣ በራስ ፊደል ኩራትና ፍላጎት ናቸው!!

ከታላቅ አክብሮት ጋር፣

  1. መምህር ልዑለቃል አካሉ
  2. ዶ/ር ኣበራ ሞላ
  3. ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ
  4. ፕ/ር ማሞ ሙጬ
  5. ፕ/ር ባዬ ይማም
  6. ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ
  7. ዶ/ር አክሎግ ቢራራ
  8. ዶ/ር አበባ ደግፌ
  9. የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ
  10. አቶ ያሬድ ጥበቡ
  11. አቶ ሰይፉ አዳነች ብሻው
  12. አቶ ተፈራ ድንበሩ
  13. አቶ ብርሃኑ ገመቹ
  14. አቶ አብርሃም ቀጄላ
  15. አቶ ታደሰ ከበደ
  16. ወ/ሮ እስከዳር አውላቸው
  17. አቶ ተመስገን መኩሪያ
  18. አቶ ግርማ ካሳ

ግልባጭ፣

ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ኣአማራ ክልላዊ መንግሥት ሊቀመንበር