(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፲፤ ረቡዕ ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች ሙስና እና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ አስተምህሮ እና ሥርዐት እንዲጠበቅ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ውሳኔ እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ አስታወቀ፡፡

የሰንበት ት/ቤቶቹ፣ በአማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎች እና በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ኾነው አስተምህሮዋን እና ሥርዐቷን በሚፃረሩ የተሐድሶ መናፍቃን ላይ ያሰባሰቧቸውን ማስረጃዎች አሠራሩን እና መዋቅሩን ተከትለው ሲያቀርቡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተገቢ ርምጃ እንደሚወስድ ሰብሳቢው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ገልጸዋል፡፡

ላለፉት አንድ ወራት በሀገረ ስብከቱ የሚገኙትን ከ160 በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች በማስተባበር÷ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ እና የዕቅበተ እምነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩት የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች ትላንት በጥያቄዎቻቸው ዙሪያ ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋር ለሰዓታት ተወያይተዋል፡፡ Continue reading

ቋሚ ሲኖዶስ የሰንበት ት/ቤቶችን የፀረ ሙስና እና የፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ እንደሚደግፍና ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፤ ፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች መመሪያ ሰጡ

Holy Synod Miyaziya 13 Meglecha

  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሀ/ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር በማነጋገር ትእዛዝ ሰጥቷል
  • መዋቅሩ ችግሮችን በየደረጃው የሚፈታበት ፍትሐዊነት እና ተአማኒነት መፈተሽ ይኖርበታል
  • ከቤተ ክህነቱ በላይ የሚያሾሙና የሚያሽሩ አማሳኝ አለቆች እንዳሉ መግባባት ላይ ተደርሷል
  • በፓትርያርኩ ዙሪያ ያሉትን ጨምሮ በፀረ ሙስና እየተመረመሩ በሕግ እንዲዳኙ ተጠይቋል

*          *          *

  • ዋ/ሥ/አስኪያጅ የማነ÷ ‹‹በፀረ ሙስና አብሬ እሠራለኹ፤ በፀረ ተሐድሶ አቋምም እንግባባለን››
  • የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራው በካሽ ካውንተር መከናወኑ የመቶ ሺሕዎች ልዩነት እያመጣ ነው ብለዋል
  • የካህናት የምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችን ያሟሉ ሰ/ጉባኤያት ጥቂት እንደኾኑ ተመልክቷል
  • በማስታወቂያ በተቋቋመው የሰሚ/መድኃኔዓለም ሰ/ት/ቤት የደብሩ ሠራተኞች አመራሮች ኾነዋል

*         *         *

  • ትላንት፣ ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋር ለአራት ሰዓታት (ከጠዋቱ 4፡00 – 8፡00) በተደረገው ውይይት፣ የሀገረ ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮችን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተገኝተዋል፡፡
  • ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራር ጋር የዕለቱን ጨምሮ ለሦስተኛ ጊዜ መገናኘታቸውን ቢገልጹም፣ጥያቄዎቻቸውን በተመለከተ የቀረበላቸው እና የደረሳቸው ነገር እንደሌለ፤ አንድነቱም ስለመኖሩ እንኳ እንደማያውቁ መናገራቸውአግራሞትን አጭሯል፡፡
  • በሰንበት ት/ቤቶቹ እንቅስቃሴ እንዳይናገሩ እየታፈኑ መሥራት እንዳልቻሉና እየተዘመተባቸው እንዳለ ጠቅሰው፣ ‹‹ከሀስብከቱ ጋር በመነጋገር ሳይኾን በራሳቸው እየተጓዙ ነው፤ የአገልግሎት መስጫውን ዩኒፎርም ለብሰው እየወጡ አድማ መቀስቀሻ አድርገውታል››ሲሉም ከሠዋል፡፡
  • የሰንበት ት/ቤቶቹ በርክበ ካህናት የቅ/ሲኖዶስ መክፈቻ ጸሎት በብዙ መቶዎች የአባላት ፊርማ አስደግፈው ያቀረቡትን አካሔዱን የጠበቀ አቤቱታ እና ጥያቄ ‹‹ፊርማ እና ባለቤት የለውም›› ያሉት ልዩ ጸሐፊው አሠራራቸው መፈተሽ እንዳለበት በሚገልጽ ቀጥተኛ ምላሽ ተሸንቁጠዋል፡፡

*         *         *

  • ለማንም በመወገን በማንም በመቀስቀስ ሳይኾን የራሳቸውን ጥያቄ ይዘው እንደመጡ የተናገሩት አመራሮቹ÷ ‹‹ፍትሕ ቢኖር፣ ችግሮች ደረጃቸውን ጠብቀው ቢፈቱ እዚኽ አንመጣም፤›› ካሉ በኋላ በአካሔዳቸው ስሕተቶች ካሉ ለመታረምና ለመመከር ዝግጁ መኾናቸውን በመግለጽ ከአጥቢያ እስከ ልዩ ጽ/ቤቱ በረዘመው የአማሳኞች ሰንሰለት የተጠለፈው መዋቅር ተአማኒነት እና ፍትሐዊ አሠራር መፈተሽ እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡
  • የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስከበር ልዕልናውን ለማስጠበቅ እንደቆሙ የገለጹት አመራሮቹ፣ ውሳኔዎቹ እንዳይተገበሩ የሚሹ አማሳኞች እና በውግዘት ከተለዩ በኋላ ወደ መዋቅሩ የሰረጉ የተሐድሶ መናፍቃን በየአጥቢያው በአስተዳደር ሓላፊነት እየተቀመጡ ትምህርተ ሃይማኖት እና ሥርዐተ እምነት እንዳይጠበቅ፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሕ እንዳይሰፍን ስለሚፈጥሩት ችግር በስፋት አብራርተዋል፡፡
  • በአራት እና አምስት ሺሕ ብር ደመወዝተኞች የ1ነጥብ8 ሚልዮን ብር መኪና ይነዳል፤ ቪላ ቤቶች እና ሕንፃዎች ይሠራሉ፤ ፈሰስ እንዲከፈል ወጪ ከተደረገ በኋላ አየር ባየር እየተበላ አጥቢያዎች ባለዕዳ ኾነዋል፤ በሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ እና በጨረታ ሽያጭ የምዝበራ ድርሻቸው የቢሯቸው ጠረጴዛ ላይ የሚመጣላቸው የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች አሉ፤ ሰንሰለቱ ሲበጠስ ጠጋኙ ያለው እዚኹ በዙሪያዎ ነው፤ ዛሬ ፉክክሩ ኤሮትራከር ለማስመጣት ነው፡፡
  • የሚሾሙ የሚሽሩ አለቆች አሉ፤ የማኅበረ ካህናት፣ የማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ተሟልተው የሚገኙባቸው ሰበካ ጉባኤያት ስንት ናቸው? ጥያቄ የሚያነሡና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የሚጠይቁ አመራሮች ይታሰራሉ፤ ይባረራሉ፤ ተረጋግቶ መሥራት አልተቻለም፡፡
  • ‹‹የሰረቁ ጣቶች ባለመቆረጣቸው ሌሎች እንዲሰርቁ በር ከፍቶላቸዋል፤›› ያሉት አመራሮቹ በአንዳንድ አጥቢያዎች ምእመኑ ፍትሕ በማጣቱ አለቆችን እስከማባረር መድረሱን ጠቅሰዋል፤ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያካበቱ አለቆች ለሌላ ተግባር እያዋሉት ስለኾነያለተጠያቂነት በየአጥቢያው እያዘዋወሩ ለዘረፋ ማበረታታቱ ቆሞ በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩና በአገሪቱ ሕግ እንዲዳኙ አመልክተዋል‹‹በእኛ እጅ ማስረጃው አለ፤ እናንተ ወስኑ፤ በዚኽ እንርዳችኹ፡፡››

*         *         *

  • ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት አንዱ የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ እና የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች የሰጡት ማብራሪያ ችግሩ ሥር መስደዱን እንዳስገነዘባቸው ገልጸዋል፡፡‹‹እውነት ነው፤ ትክክል ነው፤ አንዳንድ አለቆች ከቤተ ክህነቱም በላይ ኾነዋል፤ ማን እንደሚያሾም ማን እንደሚያሽር ይታወቃል››ያሉት ብፁዕነታቸው ማስረጃው ከቀረበ በሚመለከተው አካል ታይቶ እንደሚወሰንበት ጠቁመዋል – ‹‹በእኛ ደረጃ ብቻ የሚያልቅ አይመስለኝም፤ ወደሚቀጥለው አካልም የሚደርስ ነው፤ ቦዩን እኛ ጋር ብቻ ባንገድበው››
  • በዕለቱ ውይይት የአንድነት አመራሮቹን መግለጫ በጥሞና ሲያዳምጡ እና መልእክቱንም መውሰዳቸውን በአካላዊ ኹኔታዎች ሲያረጋግጡ የተስተዋሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር ላይ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የእርሳቸው መመሪያ ውጤት መኾኑን ያወሱት፣ ‹‹ከገባኹ ጀምሮ ሙስናን በሕጉና በአግባቡ እንድንዋጋው አግዙኝ ብዬ ያወጅኹት እኔው ነኝ›› በማለት ነበር፡፡
  • በሒደት ሲፈጠር የቆየው ችግር በአንድ ጊዜ ስለማይስተካከል ቀጣይ ጥረት እንደሚጠይቅ ያስገነዘቡት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ልጆቻችን እኛም እንደግፋችኋለን›› ሲሉ ማስረጃቸው ተጠናቅሮ ሲቀርብ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል – ‹‹በሙስናም በተሐድሶም ረገድ ያሉትን ማስረጃዎች አቅርቡ፤ ርምጃ እንወስዳለን፤ ሲኖዶስ ታዲያ ምን ሊሠራ ነው የተቀመጠው፤ ይህን ሊሠራ አይደለም ወይ፤ ይህ ሲኾን ግን ሕጉን፣ መዋቅሩንና አሠራሩን በጠበቀ መንገድ ይኹን፡፡››
  • ከዕለቱ ውይይት መጠናቀቅ በኋላ ፓትርያርኩ ኹለቱን የሀገረ ስብከት ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ወደ ኋላ አስቀርተው ጥብቅ የተባለ ነው አጠቃላይ መመሪያ መስጠታቸው ተሰምቷል – ‹‹ልጆቹን ስሜታዊ እያደረጋችኹ ያላችኹት እናንተ ናችኹ፤ በሚያቀርቡት ነገር አንዳች ነገር የለባቸውም፤ ሁከት እየተነሣ ነው እየተባለ ከየአቅጣጫው እየተወጠርን ነው፤ የሚጠይቋችኹን አዳምጧቸው፤ ትኩረት መሰጠት ያለበትን ትኩረት ስጡ፤ አብራችኹ መሥራት አለባችኹ፡፡››
  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራሮችን ጠርቶ የማነጋገሩ እና ፓትርያርኩ ለሰንበት ት/ቤቶች የሰጡትን የፀረ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ተጋድሎ መመሪያ ባስረገጠ አኳኋን በውይይቱ የተደረሰበት መግባባት ብፁዓን አባቶችን ያስደሰተና ለንቅናቄው ድጋፍን ያጎረፈ ቢኾንም በአማሳኝ አለቆች ዘንድ ብስጭትም ድንጋጤም መፍጠሩ ተሰምቷል፡፡
  • መነጋገሩ መግባባቱ የሚፈለግ እና የሚበረታታ ቢኾንም አኹንም ጥያቄው ተግባር ተግባር ተግባር የሚል ነውና አመራሮቹ እንዳሉትየዕቅበተ እምነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ ንቅናቄው ሰላማዊ ይዘቱንና ግለቱን እንደጠበቀ ይቀጥላል….

Leave a Reply