የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለሜጀር ጄኔራል አለምሸት ደግፌ እና ለብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ለአገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት የነበራቸው ወታደራዊ ማዕረግና ደረጃ ተጠብቆላቸው በጡረታ እንዲሰናበቱ ወሰኑ፡፡
(EBC)

 

ጌታቸው ሽፈራው

የብ/ጄ አሳምነው ፅጌ እና የሜ/ጀ አለምሸት ደግፌ ማዕረግ እንደተመለሰ እየተገለፀ ነው። የጡረታ መብታቸውም ይከበር ተብሏል!

አንድ ወዳጄ በእነዚህ ጀኔራሎች ላይ የተፈፀመውን በደል እያጫወተኝ ነበር። ለምሳሌ ፃድቃን እና አበበ ተክለሀይማኖት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሊያደርጉ ነው የሚል መረጃ ስለነበር (የአንጃው ደጋፊዎች ናቸው ተብሎ) ከእነ ማዕረጋቸው እንዲወጡ ተደርጓል። እነዚህ ጀኔራሎች ህወሓቶች ናቸው። አሳምነው ከብአዴን፣ አለምሸት ደግሞ ከኦህዴድ ናቸው ስለተባለ ማዕረጋቸው ተገፍፎ ተባርረዋል። የሚያሳዝነው ደግሞ እነ አለምሸት ማዕረጋቸው ተገፍፎ የተባረሩት “ሪፎርም አደናቅፈዋል” የሚል ምክንያት ተሰጥቶት እንደሆነ ይገለፃል።

አሳምነው ፅጌ ማዕረጉ የተቀማበት ምክንያት ደግሞ በሳሞራ ምክንያት ነው። አሳምነው የመከላከያ ኮሌጁ ሀላፊ እያለ ለስልጠና ያለፉት ወታደሮችን ስም ዝርዝር ያየው ሳሞራ “አማራ በዛ” ይላል፣ አሳምነው “በቃ! ፈተናውን ራሳችሁ አውጡና እንደገና ፈትኑ!” ይላል። ሳሞራ አሻፈረኝ አለ። በዚህ ወቅት አሳምነው በቀጥታ ለመለስ ዜናዊ ደብዳቤ ይፅፋል። መለስ ዜናዊ ለሳሞራ ይነግረዋል። ሳሞራም “አማራ ከሚባርበት ኮሌጁ ይፍረስ” ብሎ ኮሌጁ ስራ ያቆማል። በጊዜያዊነት ፈረሰ ተባለ። በሳሞራ የተጠመደው አሳምነው ትክክለኛ ስራውን በመስራቱ ብቻ ማዕረጉ ተገፍፎ አቶ ተብሎ ተባረረ። ኮሌጁም የትህነግ/ህወሓት ሰው ተመደበለትና የአማራና ኦሮሞ ወታደሮች ስም እየታየ በሰበብ እየተመለሱ የትግራይ ልጆች እንዲማሩበት ሆነ።

ዶ/ር አብይ አህመድ የሁለቱን ጀኔራሎች ማዕረግ እንዲመለስ ማድረጋቸው ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን እነ ሳሞራና መሰል በእድሜ የገፉ የትህነግ ጀኔራሎች በተቋሙ በሚጨማለቁበት ወቅት እነዚህ በእድሜ ከእነ ሳሞራ ያነሱ፣ የተበደሉ፣ በአንፃራዊነት በጎ የሰሩ ሰዎች በጡረታ ሊገለሉ አይገባም ነበር። የምር ዶክተሩ ሰራዊቱን መገንባት ቢፈልጉ እነዚህ ጀኔራሎች መመለስ ነበረባቸው። ዶክተር አብይ ባለፈው እንደተናገሩት የተከበረ ጀኔራል ቢፈልጉ ሰራዊቱ ከእነ ሳሞራና መሰሎቹ አሁን ማዕረጋቸው ተመልሶ ጡረታቸው ይጠበቅ የተባሉት ጀኔራሎች በአንፃራዊነት እንደሚከበሩ የታወቀ ነው።

በተጨማሪም እነ አሳምነውንና መሰሎችን ቀና በመሆናቸው ከጦሩ እያባረሩ፣ ተራ ሰራዊትን ሳይቀር በጎጥኝነት ሲጠቅሙ፣ ሲሾሞ፣ ሰላም አስከባሪነትን ንግድ፣ ለጎጣቸው ሰው ሲያደርጉ የነበሩት መጠየቅ ነበረባቸው። ይህን ለማድረግ ከከበዳቸው ግን ማዕረግ መመለስ ብቻውን ፍትሕ አይደለም። ከእነ ሳሞራና መሰሎቹ ከሚጨማለቁበት እነ አሳምነውና አለምሸት ወደ ሰራዊቱ ቢቀላቀሉ የተሻለ እንደሚሆን ግልፅ ነው። በሕገወጥነት የተገለሉት ፍትህ አገኙ ከተባለ ፍትህ የሚሆነው እስከ ማእረጋቸው መመለሳቸው ብቻ ነው!