የቋራውን ካሳ የጎንደሩን ቴድሮስ
ትንሳኤ አብሳሪውን አገር ሰሪ እንዳዲስ
አበሻ ምድር ላይ አፄ ብሎ ማንገስ
እንኳን በዚያ ጊዜ እንኳን በሱ ዘመን
ከሱ እሚስተካከል አሁንስ የት አየን
ከመቅደላ አፋፍ ላይ ለሃገር አንድነት
ከሞትም ሞተላት የጀግና ሰው ሞት
እጅ መስጠቱንስ ካሳ መች አውቆት

ዮሃንስ ካሳ ነው አባ በዝብዝ ካሳ
አገሩን ከደርቡሽ ሊመክት ተነሳ
ካገሩ ጥራጊ አፈር እንዳይወስዱ
እግር አሳጠበ አሉ ፈረንጆች ሲሄዱ
ኢትዮጵያ ተደፈርሽ መባልን ቢሰማ
ህይወቱን ሰዋልሽ ዮሃንስ መተማ

ምኒሊክ አሉና ሥም አወጡለት
የሸዋ ነጋሲ ዘረ መሳፍንት
ማዘመን አገሩን ዋና ነገር አርጎ
ዘመናዊነትን አጥብቆ ፈልጎ
ወደፊት አገሩን የሚመራ በእድገት
ለኢትዮጵያ ፋና ብርሀን አወጣላት
ባገር ከመጡበት በማርያም ነው ማላው
አድዋን የጥልያን ባድማ አደረገው

የአፍሪካ አባት ንጉሰ ነገስት
ስንቱን ያፍሪካ አገር ብርሃን አሳዩት
ላገር የከበዱ ብልህ አስተዋይ
ባለብሩህ አእምሮ ዘመን አልፎ የሚያይ
ያፍሪካን መሪዎች ማስማማት የቻሉ
ለአህጉሪቱ ሰላም መሰረት የጣሉ
ዘመናት አልፎ እንኳ ይመሰገናሉ

ካገር መሪዎች ጋር ስምህ እንዳይነሳ
ያደረግከው አንሶ ያረክብን በዛ
ወንድ አልውለድ ብላ እናት ስለት ገባች
የወለደችውም ልጇን ስደት ሸኘች
አገር መውደደህን አጥብቄ ብወድም
ፅድቅ የሚሆን ያህል ተግባርስ የለህም

ኢትዮጵያዊ ነህ ልል የአገሬ መሪ
እኮ ኢትዮጵያዊ እንዳንት ያል መሰሪ
ኧረ እንዴት ተደርጎ ከቶ በምን ታምር
የአሉላ አባ ነጋ የዮሃንስ አገር
አንተን አበቀለ ከቶ የትግራይ ምድር
ማለቂያ የሌለው ጥፋትህ ተቆጥሮ
እንዲህ ያለ ክፋት ሰው ከሰው ተፈጥሮ
እንዳገሬ ባህል ሙት ባይወቀስም
እንኳን ሞትክ ብዬ እስክስታ ባልወርድም
ሰው ሞተብኝ ብዬ ለቅሶ አልቀመጥም
ማቅ ጥቁር ለብሼም ነፍስ ይማር አልልም