December 11, 2018

https://ethiothinkthank.com/2018/12/12/the-sebhat-mafia-part-two/

በክፍል አንድ ለመግለጽ እንደተሞከረው፣ በ1970ዎቹ አጋማሽ አከባቢ ዋናዎቹ የህወሓት መስራቾች በሞትና ስደት ተለይተው አባይ ፀሓዬ እና ስዩም መስፍን ብቻ መቅረታቸውን ተመልክተናል። ከእነዚህ አንፃር ሲታይ አቶ መለስ ዜናዊ የተሻለ የትምህርት ዕድል ግንዛቤ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። በመጀመሪያ መለስ ዜናው የህወሓት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የነበረው የአቶ አባይ ፀሓዬ ምክትል ሆኖ ሲሰራ ነበር። ትግሉን በተቀላቀለ ሁለተኛ አመት ከእነ ስዬ አብረሃ ጋር ምክትል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ተመርጧል። በድርጅቱ ውስጥ ተፅዕኖ መፍጠር የጀመረው በህወሓት ውስጥ ትማሌሊ የተባለ ሌላ ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ ነው። ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ መለስ ዜናዊ ከአቦይ ስብሃት ጋር በመሆን ተቀናቃኞቹን በማስወገድ የህወሓት ሊቀመንበር፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ የሽግግሩ መንግስት ፕረዜዳንት፣ እንዲሁም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ለመሆን በቅቷል።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በጥናታዊ ፅሁፋቸው፣ አቶ መለስ ዜናዊ መጀመሪያ ላይ አክራሪ ብሔርተኛ ነበር። በትማሌሊ ምስረታ ወቅት ወደ አለም አቀፍ ኮሚኒስትነት የተቀየረ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ ከማዖዊስት ሶሻሊዝም ወደ መንግስት መር ካፒታሊዝም የአቋም ለውጥ ማድረጉን በመጥቀስ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንደሌለው ይገልፃሉ። ከትማሌሊ ምስረታ እና ድርጅቱ ከሚከተለው የትግል አቅጣጫ ጋራ በተያያዘ በመለስ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በማዳፈን፣ እንደ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ያሉ መስራቾችን በማስወገድ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆን፣ እንዲሁም በ1993 ዓ.ም የአቶ መለስ ቡድን አሸንፊ እንዲሆን ያስቻለው አቶ ስብሃት ነጋ ነው።

Photo – Sebhat Nega, EPRDF and TPLF veteran

በመሰረቱ ስልጣን ማለት በራስ ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት የነበራቸው አቶ ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው። ሌሎች የህወሓት አመራሮች እና አባላት በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ቀርቶ በድርጅቱ ደንብና መመሪያ መሰረት የመወሰን ነፃነት የላቸውም። ከራሳቸው ህሊና እና ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይልቅ ለአቦይ ስብሃት እና መለስ ዜናዊ ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ ከእነ ስብሃትና መለስ የተለየ አቋምና አመለካከት የነበራቸው እንደ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ያሉ የህወሓት መስራቾች ዕጣ-ፈንታን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ ህወሓት ውስጥ እንደ አቶ ስዩም መስፍን እና አባይ ፀሓዬ ለአቶ መለስ ዜናዊ ታዛዥና ተገዢ ካልሆኑ በስተቀር መጨረሻቸው ስደት ወይም እስራት ይሆናል ነገር ግን ያለ አቦይ ስብሃት ድጋፍና እርዳታ አቶ መለስ ዜናዊ እንደ እነ አረጋዊ በርሄ ያሉ የድርጅቱን መስራቾች በማስወገድ የህወሓት ሊቀመንበር መሆን፣ እንዲሁም እንደ እነ ስዬ አብርሃ ያሉ አቻዎቹን በማሰር እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መቀጠል አይችልም ነበር። ስለዚህ የህወሓት አባላትና አመራሮች ለአቶ መለስ ዜናዊ ተገዢና ታዛዥ የሆኑት በአቦይ ስብሃት አማካኝነት ነው። አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ለመቀጠል ከፈለገ ለአቦይ ስብሃት ነጋ ተገዢና ታዛዥ መሆኑ የግድ ነው።

ነገር ግን የህወሓትን ታሪክ በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራንና የድርጅቱ የቀድሞ አመራሮች አቦይ ሰብሃት ነጋ በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ ሚና እንደሌላቸው ይገልጻሉ። በእርግጥ ከደርግ ውድቀት በኋላ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ውስጥ የረባ ስልጣን አልነበራቸውም። ይሁን እንጂ ከደደቢት እስከ ቤተመንግስት ድረስ የህወሓት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የስልጣን እድሜ የሚወሰነው በዋናነት በእሳቸው ፍቃድና ምርጫ እንደነበር ግልፅ ነው። ዶ/ር አረጋዊ በርሄ አቦይ ስብሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ስለነበራቸው የአመራርነት ሚና እና ተፅዕኖ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-

“Woldesilassie Nega (Sibhat) .A TPLF CC member since 1976 was born in a village called Adi-Abune near Adwa where his father was a fitawrari who owned substantial farmlands. Sibhat claims to be a descendant of a legendary warrior known locally as Wa’ero, who is said to have owned large tracts of land in the district of Adwa. In this sense he was filled with ‘feudal sentiments’, which earned him the nickname ‘feudal intriguer’. He finished high-school in Meqele and studied agricultural economics at H.S.I.U. He joined the Front at Dedebit and was an ordinary member until he was elected to the leadership at the Fighters’ Congress in 1976. He showed to be strongly ethno-nationalist, and organized likeminded individuals around himself and considers any ‘Amhara’ as his enemy. His relations with the other people in the Front are reputed to be clannish and nobody knows what tangible political or military contribution he had in the struggle; but, as Tecola W. Hagos (1995: 8) rightly put it, indeed he ‘is the ‘Exchequer’ of the TPLF’.” A Political History of the Tigray People`s Liberation Front 1975-1991

ከላይ ከተጠቀሰው የዶ/ር አረጋዊ በርሄ ፅሁፍ ውስጥ “Exchequer” የምትለዋ ቃል ከደደቢት እስከ ቤተመንግስት ባለው የህወሓት ታሪክ ውስጥ የአቦይ ስብሃት ትክክለኛ ሚና ምን እንደነበር በግልፅ ትጠቁማለች። “Exchequer” የሚለው ቃል በአጭሩ የየዘውዳዊ መንግስትን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት የሚቆጣጠር ማለት ነው። በዚህ መሰረት በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ የአቦይ ስብሃት ድርሻና ሚና የድርጅቱን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት መቆጣጠር እንደነበር መገንዘባ ይቻላል። ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ የአቦይ ስብሃትና መለስ ዜናዊ ቡድን የህወሓት መስራቾችን በማስወገድ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በበላይነት ለመቆጣጠር ችሏል። ስለዚህ ከትማሌሊ ምስረታን በኋላ ባለው የህወሓት የትግል ታሪክ አቶ መለስ ዜናዊ የድርጅቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲመራ፣ አቦይ ስብሃት ነጋ ደግሞ የድርጅቱን ፋይናንስ በማስተዳደር ደርግን አስተዳድረዋል። ይህ ጥምረት ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን የደርግን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል። በቀጣይ ክፍል የስብሃት-መለስ ቡድን እንዴት ወደ ማፊያ ቡድንነት እንደተቀየረ በዝርዝር እንመለከታለን።