December 13, 2018 /

በያሬድ ሃይለማሪያም

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጥረት ወንጀል ፈጽመው የተደበቁትን ብቻ ሳይሆን ወንጀል ፈጽመው በአደባባይ የሚንጎማለሉትንም ሆነ ወንጀለኞችን የሸሸጉትን መጨመር አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አሥርት አመታት የሰብአዊ መብቶች የተፈጸመው እና ሰዎች በግፍና አስከፊ በሆነ ሁኔታ እንዲሰቃዩ የተደረጉት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ነው። አድራጊዎቹም በሁሉም ድረጃ የሚገኙ ሹማምንት እና የጸጥታ ሰራተኞች ናቸው። የተለየ ቀለም፣ ዘር፣ ኃይማኖት ወይም ሌላ የማንነት መገለጫ የላቸውም። እንደተበዳዩ ስብጥር ሁሉ በደል አድራሾቹም የተሰባጠሩ ናቸው።

በማዕከላዊ እስር ቤት ከተፈጸመው ባልተናነሰ መልኩ ከጋንቤላ እስከ ዑጋዴን፣ ከጎንደር እስከ ሞያሌ፣ ከአፋር እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከትግራይ እስከ ኮንሶ ባሉት የአገሪቱ ግዛቶች ሁሉ ግፍ በገፍ ተፈጽሟል።

ይህን ሰፊ እና ውስብስብ ችግር በይቅርታም ይታለፍ ወይም አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብ ጉዳዩ በጥንቃቄ ተይዞና በገለልተኛ አካል ተመርምሮ፣ ማስረጃ ተጠናክሮ እና የአጥፊዎቹ ማንነት በስም እና በኃላፊነት ደረጃ ተገልጾ ለሕዝብ እና ለአገሪቱ ፓርላማ መቅረብ አለበት።

አሁን በመገናኛ ብዙሃን በተዝረከረከና ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ እየቀረበ ያለው የግፈኞች ስንክ ሳር እና የተበዳዮች ሰቆቃ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ትላንት የወጣው ዛቻና ማሰራሪያ ያዘለ መግለጫ የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ በአግባቡ ከመመልስ ይልቅ ሌሎች ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፤

መንግስት ፍትህ ለማስፈን የጀመረው ጥረት እንዲሳካ እና ሂደቱም በፖለቲካ ሸር ተጠልፎ የታለመለትን ግብ ሳያሳካ ከመንገድ እንዳይቀር ከተፈለገ ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ ከወዲሁ ሊደረግ ይገባል።

አንቦ እና ባህርዳር ላይ የሰው ብልት ያኮላሸ እና ስቃይ የፈጸመ ገራፊን ወንጀለኛ ለውጡን እልል እያለ ስለተቀበለ እና ሰለተደመረ ባላየ እያለፍን ማዕከላዊ ላይ ካተኮርን አካሄዳችን ላይ ሽግር አለ። ማዕከላዊን ባልታሰርበትም ውስጡ ያለውን አደረጃጀት በደንብ አውቀዋለሁ። የመብት ጥሰት ለማጣራት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ኃላፊዎቹ ቢሮም በተደጋጋሚ ገብቼ ያለውን ሁኔታ ለማየት እድል አግኝቻለው። ቦታው አዲስ አበባ ላይ ቢሆንም ግቢው ውስጥ ያለው መንፈስ ግን መቀሌ ያለህ ነው የሚመስለው። ከፈታሽ ፖሊስ እስከ ከፍተኛ ኃላፊ ድረስ ያሉት ሰዎች ነባር ተጋዳላይ እና የህውሃት ደህንነት ኃይሎች ናቸው። ከሌላ ብሔር የመጡ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢኖሩም ቁጥራቸው ከግምት የሚገባ አይደለም። እዚህ እስር ቤት ውስጥ አሳሪውም፣ መርማሪውም ሆነ ደብዳቢው ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎች ናቸው። ይሁን እና መዘንጋት የሌለበት እዚህ እስር ቤት የሚመጡት ከፍ ያለ ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።

በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተገለጹትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስፈራሪያነት ወንጀለኞችን ከተደበቁበት እንይዛለን በሚል የለቀቁት የትላንቱ መግለጫ በግልጽ የሚያሳዩት አልደመር ብሎና አኩርፎ መቀሌ በመሸገው የወያኔ የወንጀል ግብረ ኃይል ላይ ነው። ይህ ኃይል ከፍተኛውን የወንጀል አድራጎት መፈጸሙ የሚጠራጠር የለም። በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርት እንዲቀርቡ ስንወተውት ቆይተናል። ወንጀል ከሰሩት ውስጥ የተደበቀው ይህ ቡድን ብቻ ነው። ሌላው በነጻነት እየተንጎማለለና ሹመት ያጽና ተብሎም ቀጥሏል። ይህ አይነቱ አካሄድ የመንግስትን ጥረት ለፍትህ ሳይሆን የፖለቲካ ፍትጊያውን ለማሸነፍ ብቻ እንደ ስልት የተወሰደ እርምጃ ተደርጎ እንዲታይ ያደርገዋል።

መቀሌ የመሸገው እና እፍረት በተፈጥሮው የማያውቀው የወያኔ ቡድንም ይህን ክፍተት ተጠቅሞ እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት በማስመሰል ዛሬም በሕዝቦች ቅራኔ ለመነገድ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ ነው። አሁን የተጀመረው የፖለቲካ መጓተት እና የተዘበራረቀ የፍትህ ሂደት ለእነዚህ የወንጀል ተጠርጣሪዎች መደበቂያ ዋሻ እንዲፈጥሩና ገሚሶቹም ከአገር እንዲሸሹ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው።

አሁንም የዶ/ር አብይ አስተዳደር ይህን ችግር በቅጡ ቢይዘው ይሻላል።Filed in:Uncategorized