December 16, 2018e


Seyoum Teshome

ክፍል 5፡ መቀሌ ላይ የመሸገው ህወሓት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማስቀጠል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል። በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የብሔር ግጭትና ብጥብጥ በማስነሳት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል። በተለይ በትግራይ ክልል ደግሞ ምንም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይጀመር እንቅፋት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የስብሃት ማፊያ ቡድን ለኢኮኖሚ እድገት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ዋና ማነቆ ነው።

በመሰረቱ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ዘላቂነት የሚኖረው በኢኮኖሚው ዘርፍ ስር-ነቀል ለውጥና ማሻሻያ ሲደረግ ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋለውን ህገወጥ አሰራርና የጥቅም ትስስር ማስወገድ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችና ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ የጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ የመሬት፥ ብድርና የውጪ-ምንዛሬ አቅርቦት፣ የቢዝነስ ማበረታቻና ድጋፍ አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለውን አድሏዊ አሰራር መቀየር ይኖርበታል።

“የስብሃት ማፊያ ቡድን” ተከታታይ ፅሁፍ፦

በተለይ ደግሞ ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች እና ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግላቸው ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውና ድጋፍና ማበረታቻ እየተደረገላቸው ያሉት የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች ናቸው። በዚህ ረገድ በተባበሩት መንግስታት እና የዓለም ባንክ ድጋፍ የተሰሩ ጥናቶች፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ምሁራን የተሰሩ ጥናቶች ለአዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች (entrepreneurs) እና ድርጅቶች እድገትና መስፋፋት ዋና ማነቆ የሆነባቸው የመንግስት ድጋፍና ማበረታቻ ከሚደረግላቸው ትላልቅ ድርጅቶች ናቸው።

በጥናቱ መሰረት ከጀማሪ እና መካከለኛ ደረጃ ያሉ የቢዝነስ ድርጅቶች ከመሬት፣ ብድርና የውጪ ምንዛሬ አንፃር የተሻለ አቅርቦት እና ድጋፍ ከሚደረግላቸው የመንግስት ድርጅቶች (State-owned enterprises) እና የኢንዶውመንት ድርጅቶች (party-affiliated endowments)፣ እንዲሁም የውጪ ድርጅቶች ጋር ኢፍትሃዊ ውድድር ውስጥ መግባታቸው ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። በሌላ በኩል እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም በዓለም ባንክ የተሰራ ጥናት የግል ቢዝነስ ተቋማት በመንግስት አሰራር፥ ሙስና እና የተንዛዛ ቢሮክራሲ. ከጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ በመሬት፥ ብድርና የውጪ-ምንዛሬ አቅርቦት፣ እንዲሁም በመንግስት ማበረታቻና ድጋፍ አሰጣጥ ረገድ የሚገጥሟቸው ችግሮች ለመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች አሳሳቢ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።

በዚህ መሰረት በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በህወሓት/ኢህአዴግ የተዘረጋው የኢኮኖሚ ስርዓት ከፓርቲና የመንግስት ፖለቲካ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ “Tilman A. (2010)” የተባለ ጀርመናዊ የስነ-ምጣኔ ምሁር “Industrial policy in Ethiopia” በሚል ርዕስ የሰራውን ጥናት በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል የሚስተዋለው ልዩነት የፖለቲካዊ ስርዓቱ ውጤት እንደሆነ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ኢትዮጲያ ውስጥ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እርስ በእርስ የተጠላለፉ ናቸው፡-

“…business and politics are still strongly entwined in Ethiopia. State-owned enterprises (SOEs) still dominate many manufacturing industries and service sectors, and party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. To date Ethiopia is clearly anything but a predatory state whose government pillages the economy. …Power constellations may change, those who have vested interests in SOEs and endowment-owned enterprises may gain political influence, and political power shifts may force political leaders to compromise on their development agenda.” Tilman A. (2010): Industrial policy in Ethiopia / Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010. − (Discussion Paper / Deutsches Institut für Entwicklungspolitik ; 2/2010) ISBN 978-3-88985-477-3

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የመንግስት ድርጅቶች የማምረቻና አገልግሎት ኢንዱስትሪውን በበላይነት የተቆጣጠሩ ሲሆን የኢንዶውመንት ድርጅቶቹ ለግል ድርጅቶች የሚሆነውን ዘርፍ ተቀራምተውታል። እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኪራይ ሰብሳቢ እና ጥገኛ ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ለውጥ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶቹን የፖለቲካ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚጠቀምባቸው ይገልፃል። ለአዳዲስና ጀማሪ የሆኑ አነስተኛና መካከለኛ የግል ቢዝነስ ተቋማትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው የመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ መቀነስ እና/ወይም ማስወገድ ሲቻል ነው።

ከላይ በተገለጸው መሰረት በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት የልማት ድርጅቶችን በመንግስት ቁጥጥር ስር ያደረገው የሀገርና ህዝብ ሃብትን ያለ ከልካይ ለመዝረፍ እንዲያመቸው ነው። የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወር አለበት። ይህ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነት ለመቆጣጠር በሚከተሉት ስልት ምክንያት በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ መግታት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ የሚታየውን የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ያስቀራል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች ወደ ግል ሲዘዋወሩ በምርት ዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን የገበያ ስልት ይቀይሳሉ። በመሆኑም ምርቶቻቸውን ለአከባቢው ማህብረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ስለሚሆኑ ለአከባቢው ማህብረሰብ ሆነ ለሀገሪቱ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራሉ። እነዚህን ድርጅቶችን ወደ ግል በማዘዋወር መንግስት ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ትእምት (EFFORT) ያሉ የኢንዶውመንት ድርጅቶችን በመውረስና ወደ ግል ማዘዋወሩ የህወሓት ባለስልጣኖች እያገኙት ያለውን ያልተገባ ጥቅም ያስቀራል። ይሁን እንጂ እነዚህ ድርጅቶች የስብሃት ማፊያ ቡድን የግል ንብረት ናቸው።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚደረገው ጥረት የስብሃት ማፍያ ቡድንን ከማስወገድ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ህወሓት በፌደራል መንግስት ውስጥ የነበረውን የስልጣን የበላይነት ሲያጣ በፌደራል የመንግስት የልማት ድርጅቶች አማካኝነት በሀገርና ህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረው ቅጥ ያጣ ዘረፋና ሌብነት መጋለጡ ይታወሳል። በመሆኑም ይህ የማፊያ ቡድን ወደ መቀሌ ሲሄድ ከስልጣኑ በተጨማሪ ዘረፋና ሌብነቱ ቀንሷል። ሆኖም ግን የትእምት (EFFORT) ኢንዶውመንት ድርጅቶች እስካሉ ድረስ የፋይናንስ ምንጩ አይደርቅም። የስብሃት ማፊያ ቡድን ከእነዚህ ድርጅቶች የሚያገኘውን ገንዘብ ወንጀል ለመፈፀም እና ወንጀለኞችን ስፖንስር ለማድረግ ይጠቀምባታል፡፡ የትእምት (EFFORT) ድርጅቶችን በዚህ ማፊያ ቁጥጥር ስር ሆነው እንዲቀጥሉ መተው የተጀመረውን ለውጥ እንዲቀለበስ የመፍቀደ ያህል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ከህወሓት እጅ እስካልወጡ ድረስ ለውጡን፤ ማስቀጠል ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ የዶ/ር አብይ አመራር ትእምትን (EFFORT) ካልወረሰ ህወሓትን ሰዶ-ሲያሳድድ ይኖራል፡፡

ማጣቀሻዎች