ሳስበው ሳስበው ኢሳት የአርትኦት መመሪያ (editorial policy) መኖሩን መጣም እጠራጠራለሁ ካለውም በወጉ ታስቦበት የተቀረጸ እንዳልሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ ይሄንን እንድንል የሚያደርጉን በተደጋጋሚ የቀረቡ ዝግጅቶች አሉ፡፡ የብዙኃን መገናኛዎች በተለይም ኢሳትን የመሰለ ከባድ ሕዝባዊ ኃላፊነትንና አደራን የተሸከመ ፈርጣማ ፈርጣማ ዕኩያን ጠላቶች ያሉት የሕዝብ የብዙኃን መገናኛ በወጉ ታስቦበት ተጠንቶ የበሰለ የአርትኦት መመሪያ (editorial policy) ከሌላውና በውስጡ ያሉ ሠራተኞቹ የመሰላቸውን የፈለጉትን ዝግጅት የሚያቀርቡ ከሆነ ካባባድና ዋጋ ይሚያስከፍሉ የቆመለትን የተመሠረተለትን ዓላማና አቅጣጫ የሚያስቱ ስሕተቶች መፈጸማቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ ኢሳት ያለትርፍ የሚሠራ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማገልገል የተመሠረተ የኢትዮጵያ ሕዝብ የብዙኃን መገናኛ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ኢሳት በታሰበን ቁጥር ቀድሞ ድቅን ትውስ የሚል እንደ መሪ ቃል (slogan) የሚቆጠር ቃል ነው፡፡ የኢሳት ትልቁ ዋነኛው ሀብቱና ትርፉም ይህ ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ሕዝብ ለጣቢያው የሚለግሰው የገንዘብ የዓይነትና የሞያ እገዛ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያለ ባይሆንም በሕዝብ ዘንድ ይሄንን መታመን ማግኘቱ ብቻ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ለሀገርና ለሕዝቧ የሚሠራ የብዙኃን መገናኛ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሀገርንና የሕዝቧን ጥቅም ለአደጋ የሚዳርግ ሥራ ይሠራል ተብሎ አይታሰብም አይጠበቅምም፡፡ በእርግጥ ኢሳት እየተንቀሳቀሰ ያለው በሚፈለገው ደረጃ ባልዳበረና ባልጠነከረ በጣም ደካማ በሆነ የሕዝብ ድጋፍና በበጎ ፈቃደኞች ወይም በቂ ክፍያ ሳይከፈላቸው ለሀገር አንዳች ነገር ለማበርከት በፈለጉ ሠራተኞች እየተንቀሳቀሰ ያለ ከመሆኑ የተነሣ አንድ የብዙኃን መገናኛ እንዲኖረው የሚጠበቀውን ደረጃውን የጠበቀና የበሰለ የአርትኦት መመሪያ ይዞ አቅምና ብቃት ኖሮት አይገኝ ይሆናል፡፡ ይሁን ዝንጅ የቱንም ያህል የአቅም ውስንነት ቢኖረውም ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ የአርትኦት መመሪያውን አስቀድሞ በመቅረጽ በዚህ በተቀረጸው መመሪያ ብቻ ሥራዎች እንዲሠሩ የማድረጉ ነገር ለነገ የሚባልና ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ይህ ክፍተት መኖሩ ኢሳት ከተነሣለት ዓላማ በተቃራኒ አቅጣጫ ያሉ ተቃራኒ ቡድኖች ሰርጎ ለመግባትና በኢሳት ውስጥ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል አድርጓቸዋልም፡፡ ኢሳት በዚህ ደረጃ ተዘናግቶ እንደተጋለጠ የሚያሳዩ ነገሮችን በግልጽ ስናይ ቆይተናል፡፡ ኢሳት ይህ ስሕተት ሊታረም ከማይችልበት ደረጃ ከመድረሱና ከመምከኑ በፊት ትኩረት ሰጥቶ እንዲያየውና መፍትሔ ይፈልግለት ዘንድ ይህ ጽሑፍ ተጽፏል፡፡

ያለመታደል ጉዳይ ሆኖ ነው እንጅ የሀገርንና የሕዝቧን ጥቅም ለአደጋ ያለመዳረግ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት ኢሳት ብቻ አልነበረም፡፡ የምንሠራው ለሀገርና ለሕዝቧ ነው እስካሉ ጊዜ ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ ያሉ የብዙኃን መገናኛዎች ሁሉም ይህ ኃላፊነትና ግዴታ ነበረባቸው፡፡ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የብዙኃን መገናኛዎቻችን ይሄንን ኃላፊነትና ግዴታ ለድርድር ያለማቅረብ ኃላፊነትና ግዴታ ቢኖርባቸውም በመርሕ ደረጃ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በተግባር ግን ሊጠብቁት ሊያደርጉት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ መብትና ሥልጣን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ ሀገሪቱን ጨምድዶ ይዞ በኃይል እየገዛ ያለው አገዛዝ ጥቅም ከሀገርና ከሕዝቧ ጥቅም ተፃራሪ ከመሆኑ የተነሣ የብዙኃን መገናኛዎቻችን በወያኔ በመጠምዘዛቸው የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የሀገርንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ጥቅምና ክብር ለአደጋ የሚዳርጉ ለመሆን ተገደው ወያኔ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ እንደ የብዙኃን መገናኛነታቸው ሁሉ አንድ የብዙኃን መገናኛ ሊመራበት ሊሠራበት ሊተዳደርበት የሚገባውን ሞያዊና ሥነምግባርን ያከበረ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ መርሕን ተከትሎ ከመሥራት ጋር ተራርቀውና ተቆራርጠው የሀገርንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ጥቅምና ክብር ለጋደጋ በሚዳርግ አቅጣጫ መንጎድን ከተያያዙት 25ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡

እነዚህ የብዙኃን መገናኛዎቻችን ወያኔ ካለበት ጠንቀኛና ዕኩይ አስተሳሰቡ የተነሣ እየተመራበት ያለው የአሥተዳደር ስልት ከፋፍለህ ግዛው (divide and rule) በመሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም በብሔረሰቦች መሀከል አንድነት ስምምነት ፍቅር እንዳይኖር መለያየት ጥላቻና በቀል እንዲዳብር ከመስበክ ከመገፋፋት ከማነሣሣት ጀምሮ እስከ በእውነተኛ የታሪክ ኩነቶቻችን ላይ ፈጠራና መረጃ የሌላቸውን ድርሰቶቻቸውን ቀላቅለው በመንዛት የብሔረሰብ ግጭቶችና የእርስ በእርስ ጥላቻዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ በመጣር በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት እልቂት ላይ ዋነኛውን ሚና ተጫውቶ የነበረውን የሚል ኮሊንስ ነጋሪተ ወግና ምርዓየ ኩነትን (Mille Collince Radio and Tellevision) ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡ ግጭትንና አለመግባባትን ለማንገሥ ይሄንን ዕኩይ ዓላማ ለማሳካት ሲባል ታስቦባቸው የተዘጋጁ ድራማዎችን (ትውንተ ኩነቶችን) ጭውውቶችን ተረኮችን ሳይቀር ለሕዝብ በማቅረብ በርትተው ሲሠሩ እንደቆዩና አሁንም ቢሆን ባለፍ ገደም ይሄንኑ እያደረጉ እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ለሀገርና ለሕዝቧ እንሠራለን የሚሉ የብዙኃን መገናኛዎች የሀገርንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ጥቅም ክብርና ሉዓላዊነት ለጋደጋ ላለመዳረግ ሽፋን ሊሰጡባቸው ሊያስተናግዷቸው የማይገቡ ጉዳዮች ወይም ዝግጅቶች የትኞቹ ናቸው?፡-

ይሄንን ጥያቄ ያነሣሁት ከላይ የሀገር ውስጥ የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎቻችን የወያኔን ርካሽና ነውረኛ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ብሔረሰብን ከብሔረሰብ ለማባላት፣ የአማራ ተወላጆችን ከየሚኖሩበት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማስፈናቀል ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ለማስድረግ በቀጥናም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሠሩትን ፍጹም ኃላፊነት የጎደለውንና የጠላት ሥራ እዚህ ላይ ደግሜ ለማንሣት አይደለም፡፡ ሲጀመር ይህ ሚል ኮሊንሳዊ ድርጊታቸው የብዙኃን መገናኛን ሥነምግባር (media ethics) በአስከፊ ደረጃ የጣሰ የተላለፈ ድርጊት በመሆኑና ወንጀል መሆኑን ማንም የሚገነዘበው በመሆኑ እዚህ ላይ ምንም ማለት አይጠበቅብኝም፡፡ ይልቁንስ ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝንና ሰፊ ግንዛቤ የተወሰደበት ካለመሆኑ የተነሣ ኢሳትም በተደጋጋሚ በመፈጸም የተሳሳተውን የሀገርናንና የሕዝቧን ሉዓላዊነት ደኅንነት ህልውና ጥቅምና ክብር ለአደጋ የሚዳርጉ ዝግጅቶችን በተመለከተ ጥቂት ለማለት ነው፡፡

ነገሩ እንዲህ ነው፡- ወያኔና መሰሎቹ በሀገራችን ላይ ካመጡት ከፈጠሩት ችግር አንዱና ዋናው የሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ደርሶበት ከነበረበት ከፍ ያለ ደረጃ ማለትም የኢትዮጵያንና የሕዝቧን አንድነትና ህልውናና አንድነት ጥያቄ ውስጥ ባላስገባ መልኩ “የዜጎች መብት ነጻነት እኩልነትና የሀገራችን ችግር እንዴትና በምን መልኩ ይፈታ” በሚለው ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ይደረግ ከነበረው የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ትግል ወደ የብሔረሰቦችን ልዩነት መሠረት አድርጎ ወደሚዘወርው እጅግ ጥሬና ያልበሰለ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ደረጃ ላይ እንዲያሽቆለቁል ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሀገራችን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ጠቅለል ባለ መልኩ ስናየው አሁን ያለበት ደረጃ በጣም ጥሬና እጅጉንም ያልበሰለ እንጭጭ የሆነ ደረጃ ላይ ለመሆን ተገዷል፡፡ ይህ የብሔረሰቦችንና የቋንቋን ልዩነቶች መሠረት ያደረገ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ሁካታና ፉክክር አደገኛና አጥፊም አስተሳሰብ መሆኑ ነው ችግሩ፡፡ ለዚህም ነው በሠለጠነው ዓለም ይህ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቅኝት ፊት የተነሣውና የተገለለው፡፡ አሜሪካ እንዲሁም አውሮፓ ብትሔዱ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) እና የርዕዮተ ዓለም (Ideology) ቁርቁሳቸው በሰው ልጅ መብት ተኮር እንጅ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲና (የእምነተ አሥተዳደር ቡድንና) ትግል አታገኙም፡፡ በምዕራቡ ዓለም ብሔር ተኮር ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) እጅግ የተናቀ የተጠላና የተወገዘ ይሄንን የፖለቲካ ቅኝት ለማራመድ የሚሞክር ሰውም ያለው ዕውቀት ብስለትና መረዳት ደካማና አነስተኛ ደረጃ መሆኑን ለመታዘብ ለመረዳት የሚረዳ የሚያሳብቅ ኋላ ቀር የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ትግል ስልት እንደሆነ ነው የሚታሰበው፡፡ ኋላ ቀር እንደመሆኑም ጎጂ ነው፡፡ አቶ ኦባማ በኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት ለኬንያዊያን ዘመዶቻቸው ምን ብለው እንደመከሩ አልሰማቹህም? “የብሔር ተኮር ፖለቲካ ሀገርንና ሕዝብን ያፈርሳልና ከዚህ ዓይነት ፖለቲካ ራቁ!” አቶ ኦባማ የአሜሪካ መሪ ከመሆናቸው በፊት የሕገ መንግሥት ምሁር እንደመሆናቸው በመምሕርነት ማስተማራቸውን ታውቃላቹህ አይደል?

ምዕራባዊያን ብሔር ተኮር የፖለቲካ እንቅስቃሴን የማይከተሉት የተለያዩ ብሔረሰቦች በየ ሀገሮቻቸው ስለሌሉ አይደለም፡፡ በርካታ ዓይነት የብሔረሰብ ዓይነቶች ቢኖሯቸውም ያሉ እስከማይመስሉ ድረስ ሆን ተብሎ የተዘነጉ ናቸው፡፡ ልብ በሉ የብሐየረሰቦችን እሴቶች ፋይዳ ቢስ ያደርጋሉ መደረግም አለበት አይደለም እያልኩ ያለሁት፡፡ ምዕራባዊያኑ ከመሠልጠናቸው ጋር በተያያዘ የደረሱበት ብስለት የብሔረሰብና የቋንቋ ልዩነትን ለፖለቲካ (ለእምነተ አሥተዳደር) ፍጆታ ላለማዋል ሳይነጋገሩ መግባባት ላይ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል፡፡ ለነገሩ በየ ሕገ መንግሥቶቻቸው ላይ ቀርጸውታልና “ሳይነጋገሩ መግባባት ላይ የደረሱበት” ማለት እንኳን አይቻልም፡፡ ለምዕራባዊያኑ ብሔር ተኮር ፉክክር ማድረግ ኋላ ቀር የሆነና ያልሠለጠነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ፖለቲካቸው መሠረት ያደረገው ከላይ እንደጠቀስኩት የሰው ልጅ መብት ላይና ይሄንን የሰው ልጅ መብት ለማስጠበቅ በተሻለ ደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችሉ መንገዶችና ርዕዮተ ዓለሞች ልዩነት ላይ ነው የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ልዩነቱ ፍጭት ግጭትና ቁርቁሱ ያለው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ መብት ከተጠበቀና ከተከበረ የማይከበርና የማይፈታ የብሔረሰብም ይሁን የጎሳ መብቶችና ችግሮች አይኖርምና፡፡ ብሔረሰብ ብሔረሰብ ባለማለታቸው የቀረባቸው ጠባብነትና ድንቁርና ብቻ ነው፡፡ ምዕራባዊያን ብሔረሰብ ተኮር እምነተ አሥተዳደርን  የሚጠሉበትና የሚንቁበት ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሏቸው

1ኛው. የሰው ልጅን ሰፊና ጥልቅ የማሰብ የማገናዘብ አቅም እንዲሁም የሰው ልጅ እንደ ሉዓላዊ ወይም የላቀ ፍጡርነቱ አይደለም የሱ አምሳያ ለሆኑ የሰው ልጆች ለፍጥረት በሙሉ የማሰብን ግዴታና ኃላፊነት እጅግ ሲበዛ አጥብቦ ሁለ ነገሩን ብሔረሰቤ ወይም ጎሳየ በሚለው ጥቅም ብቻ ጠቦ እንዲወሰን እንዲታጠር እንዲቀየድ በማድረግ ብሔረሰቤ ወይም ጎሳየ ከሚለው ውጭ ላሉት ዴንታ ቢስና ግድ የለሽ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ እታገልለታለሁ መሥዋዕትነት እከፍልለታለሁ ለሚለውና በሁሉም ረገድ ተጠቃሚ ሊያደርገው ለሚጥርለት ብሔረሰቡ ጥቅም ሲል ወያኔ እንደሚያደርገው ሁሉ ሌሎቹን እንዲበድል እንዲያጠቃ እንዲቃረን ስለሚያደርግ ከዚህም የተነሣ ወንጀልንና ጥሰትን ለመፈጸም ስለሚዳርግ የሰው ልጅ ከደረሰበት የሥልጣኔና የብስለት ደረጃ እንደገና ወደ ኋላ የሚያስሽቆለቁል የሚስወርድ የሚያስጎትት በመሆኑ ሲሆን፡፡

2ኛው. ደግሞ አሁን በዚህ ዘመን ላይ የሌላ ብሔረሰብ ደም ሳይቀላቀልበት በአንድ ብሔረሰብ ደም ብቻ ተወስኖ ያለ ሰው የሌለ ከመሆኑ የተነሣና ሲጀመርም የሰው ልጅ ሁሉ በሃይማኖትም ይሁን በሳይንስ (በመጣቅ) ምንጩ አንድ በመሆኑና የተለያየ የሰው ልጅ የዘር ምንጭ የሌለ በመሆኑ ቢያንስ በአንድ ሀገር ደረጃ እንዲህ ብሎ መከፋፈሉ መገላለሉ ተገቢ ባለመሆኑ ነው፡፡

እናም እኛም ያልበሰለውና ኋላ ቀሩ ብሔረሰብ ተኮር ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ውዳቂ ያልበሰለ የተሳሳተ በመሆኑና ከሚፈጥረው  ከሚያስከትለው አደጋ ሁሉ ሀገርንና ሕዝብን እራሳችንንም መታደግ ካለብን ልናደርግ የሚገባን ነገር ከዚህ ደካማ ያልበሰለ ኃላ ቀር የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቅኝትና አስተሳሰብ መውጣት መራቅ መለየት ብቻና ብቻ ነው፡፡ እስከ አሁን ይሄንን ውዳቂ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቅኝት አስተሳሰብ እንድንከተል መገደዳችን ያደረሰብን ጉዳት የለም ባይባልም ገና የሚመጣው አስጊና ከባድም ነውና እሳት “ጨብጠን አንቃጠልም” የሚለውን የጅል ፈሊጥ ትተን የጨበጥነውን እሳት ብዙ ሳያቃጥለን መጣሉ የተሻለ እንደሆነ መምከር እወዳለሁ፡፡

ይሄንን የተሳሳተ ያልበሰለ የተናቀ የተጠላና የተወገዘ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) እያቀነቀንን ያለን ሰዎች ይህ ድርጊታችን ያለንን አነስተኛ የብስለትና የማገናዘብ አቅም የሚያሳብቅ የሚያሳይብን በመሆኑ “ካፈርኩ አይመልሰኝ” የሚለውን የድንቁርና ፈሊጥ ትተን እንደ ባለ አእምሮና ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ በሠለጠነው ዓለም ከተናቀው ከተጠላውና ከተወገዘው የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) አስተሳሰብ ተለይተን ጥለን ትተን እንደሠለጠነው ዓለም ሁሉ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ጨዋታ ፉክክራችንን የሰው ልጅ መብትና የሰው ልጅ እንደ የሰው ልጅነቱ ሊያገኛቸው በሚገቡ ጥቅሞች መብቶች ላይ አተኩረን የብሔረሰብ ልዩነትን ከፖለቲካው ጨዋታ ውጪ በማድረግ “ይሄንን ለማስፈጸም እኔ የተሻለ የበሰለ አማራጭ አስተሳሰብ መንገድ ብቃት ችሎታ አለኝ” በሚለው ላይ ብንፎካከር ብንወዳደር ብንሸናነፍ አዋጭና የሀገራችንን ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) የጥፋት መንጋው ወያኔና መሰሎቹ ከጣሉበት አረንቋ ውስጥ ማውጣት ሀገራችንንና ሕዝባችንንም ተጠቃሚ ማድረግ ያስችለናል፡፡ ይንን በማድረግ ታሪክ የጣለብንን ኃላፊነትና ግዴታ እንወጣ ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉ አበክሬ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

አሁን ኢሳትን የነቀፍኩበት የተቸሁበት የኮነንኩበት ስሕተቱ እንደተገለጸላቹህ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢሳት የሕዝብ እንጅ የወያኔና የሌሎች የትፋት ኃይሎች ባለመሆኑ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በራሳቸው ዕኩይ ዓላማና ፍላጎት በከለሉት የፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) መጫወቻ ሜዳ ውስጥ እራሱን አስገብቶ ሀገር ውስጥ እንዳሉትና በወያኔ ተጽዕኖ ስር እንዳሉት የብዙኃን መገናኛዎቹ በዚህ አጥር ውስጥ ግብቶ መንቀሳቀስ በፍጹም አይጠበቅበትም፡፡ ኢሳት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ወያኔና መሰሎቹ ካመጡብን የድንቁርና በሽታ ደረጃውን በጠበቀው ዘመኑን በዋጀው የሠለጠነ አስተሳሰብ እራሳችንን የመፈወስ የሞራል (የቅስም) ግዴታና ኃላፊነት አለብን፡፡ ዝም ብለን ሳንመረምር ሳናንሰላስል እንደ ውኃ ወያኔና ሌሎች ቅጥረኛ የጥፋት ኃይሎች በቀደዱልን የጥፋት ቦይ መፍሰስ ፈጽሞ አይጠበቅብንም አይኖርብንምም፡፡ እንግዲህ ኢሳት የወያኔና የሌሎች የትፋት ኃይሎችን መርዘኛ የጥፋት ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ስብከት ሰላባ ሆነው ብሔርና ኅብረ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎችን (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖችን) መሥርተው እየተንቀሳቀሱ ላሉ ዕድል እየሰጠ ይሄንን የተጠላና የተናቀ ፖለቲካ እንዲሰብኩ ዕድል መስጠቱ ነው እንድነቅፈው እንድተቸው ያስገደደኝ፡፡

ኢሳት በተደጋጋሚ ለእነዚህ ወገኖች ዕድል እየሰጠ ይሄንን የተናቀ የተጠላና ውዳቂ የሀገርናንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ሉዓላዊነት ጥቅምና ክብር ለአደጋ የሚዳርገውን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) አስተሳሰባቸውን እንዲያስተዋውቁ ሕዝብን አሳስተውና አሰናክለውም ከጎናቸው እንዲያሰልፉ ከዚህም አልፈው የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካት ፈጠራ የተሞላበትንና መረጃ የሌላቸውን እርስ በእርስ የሚያፋጁ ወሬዎችን ወከልነው የሚሉት ብሔረሰብ ሐሳብ እንደሆነ አስመስለው እንዲያወሩና ይሄንን ዕኩይ አስተሳሰባቸውን የማይጋራው አብዛኛው የብሔረሰቡን ክፍል ዕኩይ አስተሳሰባቸውን እንዲጭኑበት ማሳሳት እንዲችሉ እንዲያሰናክሉ ዕድል ሰጥቷል፡፡

በእኔ እምነት ይህ ክፍተት ሊፈጠር የቻለው ኢሳት የሀገርንና የሕዝብን ሉዓላዊነት ህልውናና አንድነት መሠረቱ ያደረገ የሀገርንና የሕዝቧን ጥቅሞች ሊያስጠብቅ የሚችል በሳል የአርትኦት መመሪያ (editorial policy) ስለሌለው ጋዜጠኞቹ የመሰላቸውን ያስፈለጋቸውን ዝግጅቶች ማቅረብ የሚችሉበት ዕድል ስላለና ዕኩያኑ የጥፋት ኃይሎች አጀንዳቸውን በጋዜጠኞቹ በኩል ማቅረብ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል ስላለ ነው፡፡ ሲጀመር እነዚያ ዕኩያኑ የጥፋት ኃይሎች “እንዲህ እንዲህ ዓይነት አስከፊ ታሪክ ተፈጽሟል!” እያሉ የሚያወሩት ወሬ በመረጃ የተደገፈና የተረጋገጠ ካልሆነ እንደ እውነተኛና በትክክልም እንደተፈጸመ ተደርጎ እንዲወራ ከዚህም ባለፈ “ይቅርታ እንዲጠየቅበት እውቅና እንዲሰጠው!” እያሉ እንዲወሸክቱ ዕድሉ መሰጠቱ ትክክል አልነበረም፡፡ ከተደረገም የዚህን ሐሰተኛ ወሬ ሐሰተኛነት የሚያረጋግጡ የሚያጋልጡ መረጃዎችና አመክዮዎች ተነሥተው ውይይቱ ወደ አንድ ወገን ያደላ ሳይሆን ገንቢ በሆነ መልኩ መደረግ ነበረበት፡፡ ይህ አልተደረገም፡፡ ምናልባት ይሄንን የማድረግ አቅም ያልነበረ ሆኖ ከሆነ ርእሰ ጉዳዩ መነሣት አልነበረበትም የተዛባና የተሳሳተው መረጃ ትክክለኛ ተደርጎ እንዲቆጠር ዕድል ይሰጣልና፡፡ ስለሆነም በእነዚያ በቀረቡ ዝግጅቶች የሀገርንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ጥቅምና ክብር ሉዓላዊነት ለአደጋ እንዲጋለጥ ተደርጓል፡፡

እኔ በግሌ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ዝግጅቶች የቀረቡት በአጋጣሚ ነው ብየ አላስብም፡፡ ዝግጅቶቹን በሠራቸው ጋዜጠኛ አለመብሰል ምክንያት ሆን ተብሎ የተደረገ ሥራ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ እያልኩ ያለሁት ኢሳት ውስጥ የኦነግ ሕዋስ ሰርጎ ገብቷል ነው፡፡ የዚህ ሰው ጥፋት ከላይ በጠቀስነው ሥራው ብቻ አያበቃም፡፡ ወያኔ “የኦሮሚያ ክልል” ሲል በሚጠራው የሀገራችን ክፍልና በሌሎችም አካባቢዎች በወያኔና በሌሎቹ የጥፋት ኃይሎች ቀስቃሽነት ገፋፊነትና ሴራ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችንና ጥቃቶችን ሽፋን እንዳያገኙ ይከላከላል፡፡ እያልኩ ያለሁት ጋዜጠኛው “በዚህ በዚህ አካባቢ ባሉ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽሞባቸዋልና አማራም የበቀል እርምጃ ሊወስድባቸው ያስፈልጋል” ብሎ መዘገብ ነበረበት አይደለም እያልኩ ያለሁት፡፡ ነገር ግን በወያኔና በሌሎቹ የጥፋት ኃይሎች ቀስቃሽነት ገፋፊነትና ሴራ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችና ጥቃቶች በእነዚሁ የጥፋት ኃይሎች ሴራ እየተደረጉ እንደሆነ የደረሰውን ጥቃት በመጥቀስ አለመዘገቡ ያንን ወንጀል እየፈጸመ ያለው የኦሮሞ፣ የጉምዝ፣ የሀዲያ፣ የከንባታ፣ የሱማሌ ወዘተረፈ. ሕዝብ እንደሆነ እንዲታሰብና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዝ እንዲጨበጥ በማድረግ ብሔረሰብ ከብሔረሰብ ያለው ሰላማዊ ግንኙነትና አንድነት እንዲደፈርስ እንዲሻክር ዕድል እየሰጠ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ይሄንን የጥፋት ሴራ እየጠነሰሱ ያሉት የጥፋት ኃይሎች ሴራ እንዲጋለጥ ስላልፈለገ ካልሆነ በስተቀር በእነሱ ሴራ ምክንያት እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ሽፋን እንዳያገኙ የሚከላከልበት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡

ምንም ይፈጸም ምን የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎች ሊታፈኑ ሊደበቁ አይገባም፡፡ አንዳንድ ወገኖች “አለመነገሩ ጥሩ ነው” ሲሉ የሰማሁበት አጋጣሚ አለ ለምን? ሲባሉ “ሕዝቡ እርስ በእርሱ እንዲፋጅ ስለሚገፋፋው በተቻለን አቅም እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ብንደብቅ ነው የሚሻለው” ይላሉ፡፡ እኔ እነዚህ ወገኖች እንዲህ በማሰባቸው እጅግ መሳሳታቸውን ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች መጋለጣቸው ሕዝቡ እንዲያውቀው መደረጉ የጥፋት ኃይሎች ሴራ ምን ያህል እየጠነከረ እየተወሳሰበ መምጣቱንና የኢትዮጵያ ሕዝብም ምን ያህል የጥንቃቄ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትና እንዲነቃ እንዲገነዘብ ምን ቢያደርግ የጥፋ ኃይሎችን ሴራ ሊያከሽፍ እንደሚችል እንዲያስብ ያደርገዋል እንጅ በዕኩያኑ ሴራ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ተደረገ ብሎ እስከ አሁን ያላደረገውን ያደርገዋል ተብሎ ሊሠጋ ሊጠረጠር አይገባም፡፡ ይልቁንስ ይህ ሥጋት የሚያሠጋን በየትኛውም መንገድ ቢሆን ዜናውንና መረጃውን መስማቱ ማወቁ ላይቀር ነገር የዜናውና የመረጃው መቸትና የጥፋት ኃይሎች ሴራ እየተደበቀው እየተሠወረው የዚያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጻሚ በዚያ አካባቢ ያለ ሕዝብ እንደሆነ እንዲያስብ ሲደረግ ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ አጸፋውን እንዲወስድ ያደርገዋልና የብሔረሰብ ግጭት ውስጥ ገብተን ችግር ላይ እንወድቃለን ብሎ መፍራት የአማራን ሕዝብ ማንነት ጠንቅቆ ካለማወቅ ይመነጫል፡፡ የጥፋት ኃይሎች የግፍ ጥቃት ሰለባ የሆነው የአማራ ሕዝብ እስከዛሬ የተፈጸመበት የግፍ ዓይነቶች “ሞት ካልቀረለረን” ብሎ አጸፋውን ለመውሰድ እንዲነሣ የማያስገድዱና ቀላሎች ስለሆኑ አይደለም አጻፋ ለመውሰድ ክንዱን ያላነሣው፡፡ ነገር ግን የጥፋት ኃይሎች ይሄንን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃልና አጸፋ ለመመለስ ብሎ በሚወስደው የበቀል እርምጃ ስንትና ስንት መራር መሥዋዕትነት እየከፈለ ያቆያት ሀገር እንድትፈርስና የጠላቶቻችን ምኞትና አቅድ እንዲሠምር ስለማይፈልግ፣ የሽዎች ዓመታት ድካሙ ከንቱ እንዳይሆን ከዚህ ይልቅ ለዚህች ሀገር ህልውና ሲል እየተፈጸመበት ያለውን ግፍ እስከ ጊዜው ድረስና እስከሚችለው ድረስ መቀበልን ስለመረጠ እንጅ፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ለሁሉም ጊዜ አለውና የግፍና የመከራ መዓት ምንም ጫፉም እንዳልተነካ ሁሉ የመጨረሻ አቅሙን አሟጦ በመጠቀም ችሎና ታግሶ እያሳለፈ ያለው፡፡ ይሁንና ጋዜጠኛው እነዚህ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ሽፋን እንዳያገኙ የሚከላከለው ከጥፋት ኃይሎች ጋር ባለው የዓላማ አንድነት እንጅ እንደ አንዳንድ ወገኖች መረጃዎቹ መውጣታቸው ያልተፈለገ ውጤት ያመጣሉ ከሚል የተሳሳተ ሥጋት እንዳልሆነ ካረጋገጥኩ ቆይቻለሁ፡፡

ከአምና በፊት በኢሳት መጽሐፈ ገጽ (ፌስ ቡክ) ግድግዳ ላይ በሚለጠፉ ጉዳዮች ላይ አስተያየቶችን እሰጥ ነበር፡፡ የአኖሌ የጥፋት ሐውልት እየተጠናቀቀ በነበረበት ወቅት የዚህን የጥፋት ሐውልት ባለቤቶች ወያኔንና ኦነግን ሥራዎች የሚያወግዝ ጽሑፎችን በመጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ በጻፍኩባቸው ወቅት ኢሳት ውስጥ ኦነግ ሰርጎ ያስገባው ምናልባትም ያስገባቸው ሕዋስ ወይም ሕዋሶች ኢሳት ላይ አስተያየት መስጠት እንዳልችል በማገድ (ብሎክ በማድረግ) ከለከለኝ ወይም ከለከሉኝ፡፡ ሌላ ሁለት የመጽሐፈ ገጽ መዝገብ (የፌስቡክ አካውንቶችን) ከፍቸ አስተያየት ስሰጥም እነዚህንም እየተከታተለ አገደብኝ (ብሎክ አደረገብኝ)፡፡ እስከ አሁንም እንደታገድኩ ነው፡፡ የፈየዱት ነገር የለም እንጅ ይህ ድርጊት ኢሳት እየታገለለት ካለው ዓላማ ጋር ፍጹም የሚቃረንና መወገድም ያለበት መሆኑን ገልጨ ለሦስት የኢሳት ጋዜጠኞች አሳውቄ ነበር፡፡ ይሄንን ጉዳይ በዚህ አጋጣሚ ያነሣሁት ኢሳት ምን ያህል ችግር ላይ እንዳለ እንዲረዳ ለማስገንዘብ ነው፡፡

ወደ ቀደመው ነገራች እንመለስና የነገሬ ዋና ጭብጥ ኢሳትም ሆነ ከጥፋት ኃይሎች ውጭ ያለ ማንኛውም አካል የወያኔን የጠባብነትና የድንቁርና ጥብቆ በፍጹም መልበስ የለበትም፡፡ በሠለጠነው ዓለም ከተጠላው ከተናቀውና ከተወገዘው የኋላ ቀርነት ያለመብሰል ያለመሠልጠን መለያ ከሆነው ብሔርና ኅብረብሔር ተኮር ፖለቲካ ርቆ በዚህ ድንቁርና ተጠልፈው የወደቁትን ወገኖች ለማንሣት በርትቶ መሥራት ይኖርበታል እንጅ የድንቁርና ዜማቸውን እንዲያላዝኑ ዕድል እየሰጠ ሕዝብ እንዲያደነቁሩ ዕድል መስጠት የለበትን ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይሄንን ሲያደርግ ብቻ ነው ኢሳት እንደሚመኘው ሁሉ ሀገራችንንና ሕዝቧን ተጠቃሚ የማድረግ ቁልፍ ሚና ሊጫወት የሚችለው፡፡ ይህ የአሁኑ ማስገንዘቢያየም የመጀመሪያየ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደምም ኢሳት ለትሕዴን (ደሚት) የአየር ሰዓት ሊሰጥ እንደሆነ ባስታወቀ ጊዜ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ቡድኖች ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ አደጋ እንደሆኑ የሚከተለውን አመክንዮ በማቅረብ የአየር ሰዓቱ እንዳይሰጥ ለማሳሰብ ሞክሬ ነበር፡-

“ከወያኔ እንደተማርነው የብሔርና ኅብረብሔር ተኮር ትግልን ጉዳይ የፖለቲካው ጅማሬና ፍጻሜ ያደረገ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የትግል ኃይል ሥልጣን ቢይዝ ጉዳዩ ዓላማው ተግባሩ ሁሉ የታገልኩለት መሥዋዕትነት የከፈልኩለት ብሔሬ ጎሳየ የሚለውን ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ለመጥቀም፤ ተጎድቷል ከሚለው ጉዳቱ ለመካስ እሱም በተራው በሌሎቹ ላይ እንዲፋንንና እንዲፈናጠጥ ለማድረግ ከመጣር የተለየ ሊያደርግ አይችልም፡፡ የብሔር ተኮር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ቡድኖች ከዚህ የላቀ የተለየ የተሻለ ለማሰብ ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ደረጃ እንጭጮች ጠባቦችና ያልበሰሉ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብና ለሀገር ትርጉም ያለው ሥራ ሊሠሩ የሚችሉትና ፋይዳ የሚኖራቸው ሥልጣን በያዙ ጊዜም ፍትሕንና እኩልነትን ለማስፈን የታመኑ የተጉ ሊሆኑ የሚችሉት ጠባብ ከሆነው የብሔርና ኅብረብሔር ተኮር አስተሳሰብ ወጥተው ከምንም ነገር በላይ እንደ ሰው አስፍተው በማሰብ ብሔሬ ምንትሴ ሳይሉ ለዜጎች ዕኩል ዋጋ መስጠት ሲችሉና እንደ ዜጋም ሀገር የምትባለዋን ሥዕል በጭንቅላታቸው ውስጥ ማስፈር ቦታም መስጠት የቻሉ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

አለዚያ ግን ሥልጣን በያዙ ጊዜ ወያኔ 24 ዓመታት ሲያደርገው እንዳየነው ሁሉ የሌሎቹን ብሔረሰቦች መብቶችና ጥቅሞች እየረገጡ ተጎዳ ተበደለ ተጨቆነ ተጋደልንለት ሞትንለት መሥዋዕትነት ከፈልንለት የሚሉትን ብሔረሰባቸውን ብቻ ለመካስ ለመጥቀም ለማስደሰት ነው ያለ የሌለ ኃይላቸውን በመጠቀም የሚጥሩት እንጂ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ተመልክተው የፍትሕንና የእኩልነትን ጥያቄ የሚመልሱ የሚፈቱ አይሆኑም ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውምና፡፡ ከዚህ ቁንጽል አስተሳሰብ መውጣት አስካልቻልን ጊዜ ድረስ የደም መፋሰስ በዚህች ሀገር ውስጥ ይቆማል ብላቹህ ተስፋ አታድርጉ፡፡ ትሕዴንና አረና ትግራይ ስማቸው እንደሚያመለክተው ሐሳባቸውና ዓላማቸው የትግሬን ሕዝብ ከወያኔ በተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እንጅ እንደ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያን አስበው ኢትዮጵያ አቀፍ ዓላማና ሐሳብ አንግበው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማዕከል በማድረግ ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ በእኩል አገልግሎ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ አይደለም፡፡ ያ ቢሆንማ ኖሮ “የትግራይ ሕዝብ ምንትስየ” እያሉ ለራሳቸው ሥያሜ ባለወጡ ነበር፡፡ ስማቸው የሚያመላክተውና የሚነግረን ነገር ይንን ነው፡፡ እነዚህ አካላት በተደጋጋሚ ሲገልጹት እንደተሰማው ለመመሥረታቸው ምክንያታቸው “የትግሬ ሕዝብ በወያኔ ተከድቷል የተገባለት ቃል አልተፈጸመለትም!” የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ዓላማቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከወያኔም የከፋ ወያኔ በመሆን የትግሬን ሕዝብ ለመጥቀም ነው ማለት ነው”

በማለት ነበር ለማስጠንቀቅ የሞከርኩት እነዚያ ቡድኖች ሕልምና ዓላማቸው ይሄ ካልሆነና ኢትዮጵያ አቀፍ ከሆነ “የትግራይ” የሚለው ስም ምንም ትርጉምና አገልግሎት የለውምና ይተውት ይጣሉት፡፡ ኢሳት ግን ይሄንን ማስጠንቀቂያየን ሊሰማ አልፈቀደም ነበርና እሰጣለሁ ያለውን የአየር ሰዓት ለትሕዴን (የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በመስጠት ትሕዴን በኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ነጋሪተ ወግና ምርዓየ ኩነት) ዝግጅቶቹን እያቀረበ ይገኛል፡፡ እያልኩ ያለሁት በትግርኛ ሌላም ከታሰበ በሌላ ቋንቋ ዝግጅቶች አይቅረቡ አይደለም፡፡ እያልኩ ያለሁት ይዘታቸው ብሔረሰብንና ወያኔ ክልል ሲል የሚጠራውን የሀገር ክፍል ሳይሆን ሀገርንና ሕዝብን ማዕከል በማድረግ ሀገርንና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ዝግጅቶቹ እስከቀረቡ ጊዜ ድረስ በተለያየ ቋንቋ መቅረቡ ይበልጥ ተጠቃሚ ያደርገናል እንጅ በምንም መልኩ የሚጎዳ አይሆንምና፡፡

መጀመሪያ እኔ ኦሮሞ ነኝ (first I’m Oromo)፣ መጀመሪያ እኔ ትግሬ ነኝ እኔ ምንትስ ነኝ በማለት ብሔረሰቤ የሚሉት ከምንም ነገር እንደሚበልጥባቸው በግላጭ በአደባባይ የሚናገሩ ሰዎች ሥልጣን ቢይዙ እንዴት ነው ሌላውን ብሔረሰብ ከራሳቸው ጋር እኩል ሊመለከቱና ሊያስተናግዱ ሊያደለግሉ የሚችሉት? እኔ ኦሮሞ ነኝ እኔ ትግሬ ነኝ እኔ ምንትስ ነኝ ከማለት በፊት “እኔ ሰው ነኝ” ማለት ይቀድማል፡፡ እኔ ሰው ነኝ ማለት ከቻልንና የሰው ልጆችን ወይም ዜጎችን በእኩል የማየት ግዴታ እንዳለብን አምነንና ተረድተን ይንንም ማድረግ እንዳለብን እስካወቅንና ማድረግ እስከቻልን ጊዜ ድረስና ለዚህም ታማኝነታችንን እስካረጋገጥን ጊዜ ድረስ “እኔ ምንትስ ነኝ” እያልን ብሔረሰብ እየጠራን ለየብሔረሰባችን ጥብቅና ቆመን ለብሔረሰባችን ነጻነትና ጥቅም ልንቆም ልንጋደል የሚያስፈልግበት አንድም ፍትሐዊ ምክንያት የለም፡፡ ጠበንና ደንቁረን ለማጥፋትና ለማውደም ካልሆነ በስተቀር፡፡ ኢሳት እንዲህ ብለው የሚያስቡ ሰዎችን ይሄንን ደካማ አስተሳሰብ በሚሞግትና እንዲማሩ እንዲለወጡ እንዲታረሙ በሚረዳ መልኩ ሳይሆን ሰንካላና ደካማ አስተሳሰባቸውን ወደ ሕዝብ በማድረስ ሕዝብ እንዲያሳስቱ በሚያስችላቸው መልኩ ዕድል ሰጥቶ ማስተናገዱና መበሣሪያነት ማገልገሉ ፍጹም ስሕተት ብቻ ሳይሆን የሀገርናንና የሕዝቧን ደኅንነት ህልውና ጥቅምና ክብር ሉዓላዊነት ለአደጋ መዳረግም እንደሆነ ነው ለማስረዳት ለማስገንዘብ እየሞከርኩ ያለሁት፡፡ እናም የኢሳት የቦርድ አባላት ሆይ! ይሄንን አንገብጋቢና ወሳኝ የቤት ሥራ ጊዜ ሳትሰጡ ትሠሩ ዘንድ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው amsalugkidan@gmail.com

Leave a Reply