ሐራ ዘተዋሕዶ

የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎቻችን በልማት ሰበብ እየተሸራረፉና እየተጣበቡ ነው፤ በበዓሉ ትውፊት፣ ማኅበራዊ ሚና እና በቱሪዝሙ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይታሰብበት!

January 20, 2019 Leave a comment

janmeda since 2005 ec

***

janmeda since 2005 ec5

***

ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ

(የጠቅላይ ጽ/ቤት ዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ሓላፊ)

janmeda baptismal pool3

… የጥምቀት በዓል ለዘመናት ሲከበርባቸው የኖሩ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የተቀደሱ ቦታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚጨምረው የሕዝበ ክርስቲያን ቁጥር ልክ እየሰፉና እየተዋቡ መሔድ ሲገባቸው በተቃራኒው፣ ይዞታዎቹ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ሰበብ እየተሸራረፉና መጠናቸው እየቀነሰ በመምጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት ይዞታቸው ተከብረው የኖሩ አብሕርተ ምጥማቃት፣ ጃንሜዳን ጨምሮ በቁጥር ከ75 በላይ ቢኾኑም፣ ሁሉም ማክበርያ ስፍራዎች ሊባል በሚችል ደረጃ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ሰበብ እየተቆረሱ በመወሰዳቸው ለወደፊቱ የመስቀል ደመራ እና የበዓለ ጥምቀት የታቦት ማደሪያዎች ጨርሰው የሚጠፉበት ኹኔታ እንዳይፈጠር ያሰጋል፤ ይዞታቸው ለአደጋ መጋለጡ፣ ትውፊታዊ ሥርዓቱንና ማኅበራዊ ሚናውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሚፈጥረው ዕንቅፋት አኳያ፣ ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝበ ክርስቲያኑን እያሳሰባቸው ይገኛል፡፡ እንደ መስቀል ደመራ ኹሉ የጥምቀትን በዓል በመንፈሳዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት፣ በቦታዎቹ መጣበብ ሳቢያ እክል እንዳይገጥመው፣ ይህም በቱሪዝሙና ሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያስከትል የሚመለከታቸው የሥራ ሓላፊዎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡

ከንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እያገለገለ ያለውና በተለይም ከ1935 ዓ.ም. ጀምሮ በዘመናዊ መልኩ ተደራጅቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የማጥመቂያ ቦታ በጃንሜዳ እንዲሠራ መደረጉ፣ የቦታውን ሕጋዊ ይዞታ በማሳየት በኩል አብነት ሊኾን እንደሚችል ይታመናል፤ በስፍራው የተቀመጠው የመሠረት ድንጋይም በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ይኹንና፣ በታወቀ መነሻ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በጃንሜዳ እንደማያገባት ኹሉ፣ ታቦታቱ ወደ ቅጽሩ የሚዘልቁበት ግራና ቀኙ ተቈርሶ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ግብዓት ማስቀመጫነት በመዋሉና ቦታው በከፍተኛ ኹኔታ በመጣበቡ፣ በየዓመቱ ከተራና ጥምቀት፣ መግቢያ በሩን በሕገ ወጥ መንገድ የዘጋው ድርጅት እንዲከፍት፣ ቤተ ክርስቲያን በገዛ ይዞታዋ በደብዳቤ ፈቃድ ለመጠየቅና ለመለመን ተገዳለች፡፡

janmeda since 2005 ec4

ጃንሜዳ በሁሉም አቅጣጫዎች ሊባል በሚችል መልኩ ለተለያዩ አገልግሎቶች የተለያዩ ግንባታዎች በስፋት እየተካሔዱበት ከመኾን አልፎ፣ የመሮጫ ሜዳ ለመሥራት በሚደረገው ቁፋሮ የተደላደለ ሜዳማ ገጽታውን እንዲያጣና ወጣ ገባ ይዘት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ሜዳው በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በመወረሩ ምክንያት፣ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ በሜዳው መብት እንደሌላትና የጥምቀት ሥነ ሥርዐትን ከማክበር ባለፈ በባሕረ ጥምቀቱ አካባቢ የራስዋን እንቅስቃሴ እንዳታደርግ ማዕቀብ የተጣለባት ይመስላል፡፡

በተመሳሳይ፣ የእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ሥላሴ እና የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ታቦታት በሚወጡበት ስፍራም፣ ከሽሮ ሜዳ ወደ እንጦጦ ኪዳነ ምሕረት በሚወስደው የመንገድ ሥራ ምክንያት ቦታው ተቈርሶ የተወሰደ ከመኾኑም በላይ፣ቀሪውም የጥምቀት ማክበርያ ቦታ ለመንገድ ሥራው የግንባታ ቁሳቁስ ማስቀመጫ እንዲኾን በመደረጉ፣ በስፍራው የሚከበረው የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት በተመቻቸ ቦታ ላይ የመከበሩ ጉዳይ በእጅጉ አጠራጣሪ ኾኖ ይገኛል፡፡

አዲሱ ገበያ አካባቢ፣ የእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በርካታ ታቦታት ያርፉበት የነበረው ቦታም፣ ቀስ በቀስ ተቈራርሶ በማለቁና በቦታውም ላይ ግዙፍ ሕንፃዎች በመገንባታቸው፣ የታቦታቱ ማደርያ ተገፍቶ ተገፍቶ ከሕንፃዎቹ ፊት ለፊት ከነዳጅ ማደያው አካባቢ ምቹነት በሌለው የከተማ አውቶቡስና ታክሲ ማቆሚያ ቦታ ላይ ታቦታቱ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ጠባብና ምቾት የሌለው ቦታ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ቁጥር መጨመር ጋራ ተያይዞ ሥነ በዓሉን ያደበዝዘዋል፤ አላስፈላጊ የትራፊክ መጨናነቅና የመንገድ መዘጋጋትም ያስከትላል፤ ለጸጥታ ማስከበር ሥራም ምቹ እንዳልኾነ፣ ቀደም ሲል የተከበሩ በዓላትና ያጋጠሙ አሠቃቂ አደጋዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በአገራችንና በተለይ በከተሞቻችን፣ የባሕረ ጥምቀት ይዞታዎቻችን መጠናቸው ሊሰፋና ሊያንስ ይችላል እንጂ ችግር የሌለባቸው፣ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በይዞታ መገፋት ያላነሱና ያልተቆራረሱ ይገኛሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ ለዚህም ከሚጠቀሱት በርካታ ምክንያቶች ውስጥ፣ ከበዓል ማክበርያነት ባለፈ ተጨማሪ የልማት ሥራ ስላልተሠራባቸውና እንዲሠራባቸው ቢፈለግም የመንግሥት አካላት ፈቃደኛ ባለመኾናቸው እንደኾነ ርግጥ ነው፡፡ ቦታዎቹን በአግባቡ ለማስተዳደር፣ ለማስዋብና ለማልማት፣ የከተማዋ የአስተዳደር አካላት ሲጠየቁ ፈቃደኛ ባለመኾን፣ በተለያዩ ሰበቦች ሲቈራረሱና ሲወሰዱ ባለመከላከልና አንዳንዴም በልማት ስም እንዲሸራረፉ በመፍቀድ ጭምር ለጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ንቀትና ሥር የሰደደ ጥላቻ አሳይተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም፣ በዓሉን እንደምንም ካሳለፈች በኋላ ይዞታዋን ለማስከበር እስከ መጨረሻው አካል ድረስ ለፍትሕ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ቀጣዩ በዓል እስኪደርስ ዝምታን በመምረጥ መብቷን አሳልፋ ሰጥታለች፡፡

ይህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ጥላቻና ትንኰሳ በሌሎች የእምነት ተቋማት ላይ ቢፈጸም የሚያስከፍለውን ዋጋ ጠንቅቆ የሚገነዘብ መንግሥታዊ አመራር፣ የትዕግሥተኛና ሆደ ሰፊዋን ቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች፣ እዚህ ግባ በማይባል ተልካሻ ምክንያት በመንጠቅ ቈራርሶ ለሌላ አገልግሎት በማዋልና ቀስ በቀስ ገፋፍቶ ከይዞታዋ ለማስለቀቅ ይሠራ እንደነበር ከፍ ሲል ከተገለጹት አብነቶች በላይ ማረጋገጫ አይገኝም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አመራርም፣ ጥንታዊና ታሪካዊ ዕሴቶቿን ከማስጠበቅ ይልቅ በጥቃቅን ሥራዎች በመጠመድ መብቷንና ጥቅሟን ሊያስከብሩ የሚችሉ ሥራዎች አልሠራም ማለት ይቻላል፡፡

በመኾኑም፣ በምእመናንና ኦርቶዶክሳዊው ወጣት መንፈሳዊ ተነሣሽነትና ተጋድሎ ከዓመት ዓመት እጅግ እየደመቀና እየተዋበ መከበር የቀጠለው የጥምቀት ሥነ በዓል፣ የቤተ ክርስቲያንን አብሕርተ ምጥማቃት በማስጠበቅ ረገድም የራሱ አስተዋፅኦ ሊኖረው ያስፈልጋል፤ ቤተ ክርስቲያንም በቋሚ ይዞታነት ልትረከባቸው፣ ልትጠብቃቸውና ልትከባከባቸው ይገባል፡፡ በዓሉ በአማረና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ወጣቱ የሚከፍለውን መሥዋዕት ከማድነቅ ባሻገር፣ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋራ በአካል ቀርቦ ፊት ለፊት በመነጋገር አልያም ይህን ተግባር የሚያስፈጽም ጠንካራ ኮሚቴ በማዋቀር አብሕርተ ምጥማቃት በቋሚነት ለበዓለ ጥምቀት ማክበርያነት እንዲውሉ፣ እንዲጠበቁና እንዲለሙ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ሀገራዊ ለውጡን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመያዝ የታቀደና የሚተገበር ሥራ መሥራት ይኖርባታል፡፡

janmeda baptismal pool

በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚታየው ቅንነት የተላበሰ ለውጥ፣ የቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥበት ኹኔታ ስለሚታይ፣ የጥምቀት ማክበርያ ይዞታዎቻችንን ለማስከበር በቁርጠኝነትና በሓላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅባታል፡፡ የበዓሉን ሰሞን እንደ መነሻ ወስዶ ከመሥራት ይልቅ እንደ ዐቢይ ሥራ ቈጥሮ በዘላቂነት መንቀሳቀስን እንደሚጠይቅ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ፣ በመዲናዋ ምን ያህል የጥምቀት ማክበርያ ስፍራዎች እንዳሉና የሚገኙበትን ክፍለ ከተማና ወረዳ፣ ምን ያህሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙና ምን ያህሉ እንደማይሰጡ፣ ምን ያህሉ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዳላቸውና እንደሌላቸው፣ ምን ያህሉ በምን ምክንያት እንደተሸራረፉ በዝርዝር ማጥናት ያስፈልጋል፤ የይዞታ ባለቤትነት ከተረጋገጠ በኋላ የከተማውን ተጨባጭ ኹኔታ ባገናዘበ መልኩ ለማስዋብና ለመጠበቅ ቤተ ክርስቲያን ዝግጁነቷን መግለጽና ማሳየት ይኖርባታል፡፡

janmeda baptismal pool2

በዓሉ በቀረበ ጊዜ ማጽዳት፣ ማስዋብና መጠቀም ብቻ በራሱ በቂ አይደለም፡፡ ዘወትር ተፈጥሯዊ ገጽታቸውን በዐጸዶችና አትክልት ለማስጌጥ፤ ለሠርግ ሥነ ሥርዓት መፈጸሚያ፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የሻሂ ቡና አገልግሎት የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጡ፣ መንፈሳዊነትን የተላበሱ መናፈሻዎችን በመገንባት የሚከባከብና የሚያስተዳደር በገቢ የሚያስችል አካል መመደብ ከቤተ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡

በማእከል ደረጃ፣ የጥምቀት በዓል በየዓመቱ በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበርበት የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት፣ ከምእመናን ቁጥር መጨመር፣ ከሥነ በዓሉ ድምቀት አንጻር ሊሻሻል፣ ሊጠናከርና ሊስፋፋ እንደሚገባው ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር ከፍ ሲል የተገለጸው የጃንሜዳ ቅርምት ችግር ከመሠረቱ ይፈታ ዘንድ ከሚመለከተው አካል ጋራ ፊት ለፊት መነጋገር፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ማስረዳትና ይዞታውን ማስጠበቅ ጊዜ ከማይሰጣቸው ተቀዳሚ ሥራዎቻችን አንዱ ሊኾን እንደሚገባ፣ ሜዳው የሚገኝበት ተጨባጭ ኹኔታ ያስገድዳል፤ ወደፊትም በገቢ ራሱን ችሎና ትርፋማ ኾኖ ዓመታዊ የበዓል አከባበር ሥነ ሥርዓቱን በራሱ አቅም ማስፈጸም የሚችልበትን ጥናት መሥራት ይኖርብናል፡፡

janmeda since 2005 ec3

ለበዓሉ ሰሞን ማጽዳት፣ ማስዋብና መጠቀም ከበዓሉ በኋላ ደግሞ ዘወር ብሎ አለማየት፣ አሁን ላለበት ኹኔታ የዳረገው ስለኾነ መንቃት ይጠበቅብናል፡፡ በአዘቦቱ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ መኾኑን ታሳቢ በማድረግ መንፈሳዊ ይዞታነቱን ጠብቆ ማስፋፋት፣ በርካታ ክፍሎች ያሏቸው መታጠቢያ ቤቶችን፣ የመዋኛ አገልግሎት፣ የቤት ውስጥ ስፖርት(ጂምናዝየም)፣ ደረጃውን የጠበቀ መናፈሻ፣ የጉባኤ(ስብሰባ) አዳራሽ በመገንባትና በአግባቡ አደራጅቶ በመምራት፣ ዓመታዊ የበዓል አከባበሩን በራሱ ወጪ እንዲሸፍንና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር በማስቻል፣ ማራኪና ተመራጭ ስፍራ ለማድረግ ዐቅደን ብንሠራ ታላቅ እገዛ እንደሚኖረው መገመት አያዳግትም፡፡

ይህን ታሪካዊና መንፈሳዊ ስፍራ የበለጠ ማሣመርና ይዞታውን በዘላቂነት ማስከበር፣ ሌሎች ይዞታዎችን ለማስጠበቅ እንዲሁም ጥምቀትን በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ከማሳካት አንጻር ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለው ተገንዝበን በጋራ ብንረባረብ መልካም ይኾናል፡፡

ምንጭ፡- የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ “ክርስቲያናዊ ሕይወት በጥምቀት” በሚል ርእስ ከአዘጋጀው የ2011 ዓ.ም. በዓለ ጥምቀት መጽሔት ልዩ እትም