February 12, 2019

Source: http://amharic.borkena.com/2019/02/11/%E1%8B%A8%E1%8C%8E%E1%88%B3-%E1%89%85%E1%8A%9D%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%89%83%E1%8A%9C-%E1%88%98%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%8A%AB%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8B%AB%E1%88%98%E1%8C%A3%E1%8B%8D/

በዳዊት ሳሙኤል
የካቲት 4 2011 ዓ.ም.

ዛሬ ደግሞ ምኑን ከምኑ አገናኜህብን እደምትሉኝ እገምታለሁ። ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን አዲሱ የለውጥ አመራር በአዲስ አበባ እና በፌደራን ደረጃ በፊት ወያኔ ያደርገው ነበር ከሚባለው በከፋ ሁኔታ ቦታዎችን፣ ስልጣንንና ኃላፊነትን በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች እየተሞሉ ነው። የሚል ዜና በሰፊው እየተሰራጨ መሆኑን ስሰማ የዛሬ 20 አመት ሂልተን ሆቴል ለስልጠና ከቱሪዝም ኮሌጅ ተልኬ ያየሁትን የሰማሁት ሁኔታ ጋር ስለተመሳሰለብኝ ለአንባቢ ላጋራ ፈለኩኝ። አይደረግም ብዬ አልከራከርም። ነገር ግን ከላይ ያሉት አመራሮች ግን ሙሉ በሙሉ በእቅድ ይሰሩታል ለማለት ግን አልደፍርም። የሚሾመው በጎሳ ፖለቲካ የሰከረ፣ በመቦጥቦጥ ምኞት የጦዘ ብዙ ከንቱ ግን እንደሚኖር ከሀገሪቱ የፖለቲካል ሂስትሪ የሚጠበቅ ነው። ከአሁኑም ሁላችንም በአንድ ላይ ቁመን ካላወገዝነው መጨረሻው ጥፋት ነው።

እስኪ መጀመሪያ ስለ ሂልተን ትንሽ ልበል። ሂልተን አዲስ አበባ በመሀል አዲስ አበባ ሁለቱን ቤተመንግስቶች አማካኝ በሚያደርግ ስትራቴጅክ ቦታ ላይ በ1961 ዓ ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን ተመሰረተ። በውስጡ ከ400 በላይ አልጋዎች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የሳውናና ጃኩዊዚ አገልግሎት፣ የሀገር ምርቶች መሸጫ ሱቆች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች( ጎልፍ፣ የሜዳና የጠረንጴዛ ቴንስ፣ ጅም፣ )፣ የስብሰባ አዳራሾች፣ እጅግ የተዋቡ የተለያዩ ሬስቶራንቶችና መጠጥ ቤቶች ያሉት ሲሆን 11ኛ ፎቅ ላይ ሙሉውን አዲስ አበባን እያዩ የሚዝናኑበት ሬስትቶራንት ለከፍተኛ እንግዶች ያለበት፣ በዚሁ ፎቅ ላይ እጅግ የተዋበ ለሀገር መሪዎች ተብሎ ከፊት ለፊት መግቢያው ላይ የንጉሰ ነገስቱ ወርቃማ የአንበሳ ሀውልት ጉብ ያለበት የምኝታ ክፍል አለ። በአጠቃላይ ግቢው በብዙ በተለያዩ ዛፎችና አበቦች የተሞላ እጅግ የተዋበ ግቢ ነበር።
ከ400 የማያንስ ሰራተኛ የሚያስተዳድር፣ ሰራተኞቹ ለድርጅቱ በጣም ታማኞች ነገር ግን በጣም ትንሽ ደመወዝ የሚከፈላቸው ነበሩ። ነበሩ የምለው የዛሬውን ስለማላውቅ ነው። አሰሪዎቹ ትንሽ የውጭ አገር ሰዎች ቢኖሩበትም 90% አበሻ አሰሪዎች ናቸው።

ወደ ተነሳሁበት ርእስ ልምጣና እኔ እዛ በነበርኩ ግዜ ሰራተኞቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመታገል እስከ ስራ ማቆም አድማ እርምጃዎችን ይወስዱ ነበር። እንዳለመታደል ሁኖ አሰሪዎቹ የብዙ አመት ልምድ ስላላቸው የማህበር መሪዎችን በጥቅማ ጥቅም እየያዙ ብዙ ቆራጥ ሰራተኞችን እስከ ስራ ማባረር እና አንዳንዶቹንም እስከ ህይወት መጥፋት ድረስ የደረሱ አሉ ይባላል። በወቅቱም ጸጋየ የሚባል የትግራይ ልጅ ብዙ ሰው ይወደው የነበረ በምግብ ተመርዞ ተገደለ ተብሎ ተጠርጣሪዎችም ታስረው ነበር። የተወሰኑ ሰራተኞችም ከስራ ተባረው በማይሰራው ፍርድ ቤት እየተንከራተቱ ነበር።

በሆቴል ቤት ከፍተኛ ቁልፍ ቦታዎች የሚባሉት የእንግዳ አቀባበል፣ የፋይናንስ ክፍል ፣ የሴኩሪቲ ኃላፊነቶች ፣ የምግብና መጠጥ ክፍል ናቸው። በደርግ ግዜ እና ወያኔ በገባባቸው የመጀመሪያ አመታት ኤርትራውያን በብዛት ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ነበር ይባላል። በሗላ ግን የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታን ተገን በማድረግና የኤርትራ ውያን መባረርን ተከትሉ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎች በትግራይ ተወላጆች መያዝ ጀመሩ። በወቅቱ የሴኩሪቲ ሀሌፊ የነበረ ሊላይ የሚባል የትግራይ ሰው ተስፈንጥሮ የእንግዳ አቀባበል ኃላፊ ሆኖ ሰራተኛውን ያም ሰው ነበር። እንደ ስራተኞቹ ትረካ በጠላትነት የታዩትን ሰራተኞች በልብስ ማስቀመጫ ሳጥናቸው ሳይቀር የድርጅቱን ንብረት በድብቅ በማስቀመጥ ድንገት ፍተሻ ተካሄደ በማለት ሰራተኞች ይባረሩ እንደነበር በምሬት ይናገሩ ነበር። ባጠቃላይ እድገት በዝምድና ፣ በታማኝነት ብቻ ነበር የሚሰጠው። አድርባዩ ለሆዱ እያንዳንዷን መረጃ ይዞ በመሮጥ የበቀል እርምጃ ስለሚወሰድበት ሰራተኛው በፍጹም አይተማመንም ነበር። አንድ ሰው በፊት እቃ አጣቢ የነበረ ሰው በዚሁ ስራው ተነስቶ የኮንስያዥ ሀላፊ እስከመሆን እንደደረሰ ሰራተኛው እርስ በእርሱ ይንሾካሾክ ነበር። የድርጅቱ መኪኖች የሚጠገኑት፣ ለሆቴሉ እቃ የሚቀርበው ሁሉ እንዲሁ በዘመድ አዝማድ የተተበተበ ነበር ይላሉ። እንግዲህ በዚህ ሆቴል ሁሉም አልጋ ዎች በሚያዙበት ወቅት በ10 ሽዎች የሚቆጠር ዶላር ገቢ በቀን ከአልጋ ብቻ ይገባል ማለት ነው።

መቼም የሁሉም ነገር መጨረሻ አለውና እነዚህ ማኔጀሮች ህወሀት ሲከፋፈል የነ እሰየ አብርሀ ወገን ነበሩና በተራቸው የዱላ ናዳ ሲወርድባቸው ተበታተኑ። ዋናውም ጠፍቶ ወደ አሜሪካ ኮበለለ። ከዚህ ታሪክ በኋላ ግን እኔም ለትንሽ ግዜ ስልጠናየን ጨርሼ በጊዜያዊ ሰራተኝነት ለአንድ አመት አካባቢ ተቀጥሬ ስለነበር የማቀውን ያየሁትን እጽፋለሁ።

ትግሬዎቹ ሲነቀሉ በፋይናንስ የስራ ክፍል ውስጥ ይሰራ የነበረ መልከ መልካም የአምቦ ሰው አቶ ከበደ ቦረና የሚባል የእውቀት ችግር የሌለበት ሰው የፋይናንስ ሀላፊ ሁኖ ተሾመ ። ወዲያውኑ ሊላይ የተከለው ሁሉ መነቀል ተጀመረ። የእንግዳ አቀባበል ኃላፊው ትንሽ ወንድሙ ሆነ፣ በሁሉም የስራ ክፍሎች የሂሳብ ተቆጣጣሪዎች የእህት ልጅ፣ የአጎት ልጅ ተደረጉ፣ የሾፌሮች አለቃ፣ ከአየር መንገድ እንግዶችን አምጭ ሀላፊ ደግሞ አጎቱ ነው የሚባል ሰው ተሾመ። ባጠቃላይ ያለምንም ሀፍረት ሁሉም ቦታ በሚባል መልኩ ተወረረ።

በወቅቱ ከአስር አመት በላይ በሴኩዩሪቲ የስራ ክፍል በጊዜአዊነት ያገለገሉ ሰራተኞች ቋሚ እንሁን ብለው ወደ ክስ በመሄዳቸው ድርጅቱ ድፖርትመንቱን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ለግል የጥበቃ ድርጅት ኮንትራት ሰጥቶ ከስራ አስወጣቸው። በዚህ ወቅት በሌሎች የስራ ክፍሎች እስከ 19 አመት በጊዜአዊነት የሰሩ ጎስቋላ ሴቶች በድርጅቱ ውስጥ ነበር። ክስ እንደሚመጣባቸው ሲያውቁ ጊዜያዊ ሰራተኞችን ተከታታይ ጊዜ አይሰሩም ለማስባል ሁላችንንም አንድ አንድ ወር እያሳረፉ በማሰራት ሰራተኛው ላይ የጭንቀት ጦርነት ከፈቱበት። በወቅቱም ከነበሩት ለምን? ብለው ከሚጠይቁ ደፋሮች ውስጥ ተፈርጄ አንድ ወር አሳረፉኝ። በዚህ ወቅት 24 ልጆችን አስተባብረን የክስ ወረቀት ይዘን መጥተን ክሱ እስከሚፈረድ ማባረር አትችሉም ተብለው ወደ ስራ መለሱን። የማይነካው የድርጅቱ የጭካኔ ጥግም ተደፈረና ከዚያ በኋላ ሁሉም ወደክስ መሮጥ ተጀመረ። እኔ ሌላ የተሻለ ብየ በወቅቱ ወዳመንኩበት ቦታ ሌላ ስራ በማግኜቴ ሄድኩ እንጅ ጓደኞች ቋሚ እንዲሆኑ የሚል ተፈርዶላቸው ገቡ።
በወቅቱ ቋሚው ሰራተኛ የስራ ማቆም አድማ ሲጠራ የሰራተኛ ማህበር መሪው 5 ደረጃና የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግለት የሰራተኛውን ትግል ከማኔጀሮቹ ጋር ተመሳጥሮ አመከነው። ባንድ ወቅትም የኢትዬጵያ ሰራተኞች ስብሰባ ተገናኝተን እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ ስለው። ” ወንድሜ እኔ ጡረታ ለመውጣት የቀረኝ ግዜ አምስት አመት አልቀረኝም፣ የሀገሩ ባለስልጣናት መብትህን ብትጠይቅ ጥይት ነው ምላሻቸው፣ 30 አመት ሰርቼ ያላገኜሁትን ገንዘብ ደመውዜ ላይ ሲጨምሩልኝ ለምን ብየ ነው ዝም እምለው?” ብሎ ያለምንም ሀፍረት አመነልኝ። በሗላም ደጋግሞ እንዲመረጥ ይደረግ የነበረውን ሸፍጥ ተረከልኝ።

በወቅቱ የድርጅቱ ማኔጀር አንድ ጀርመናዊ ክላውስ ሻርክ የሚባል እጅግ አምባገነን ከሀበሾቹ ጋር ሁኖ ነበር ይህ ሁሉ ግፍ የሚሰራው። ለሁሉም ግዜ አለው እንደሚባለው እነዚህም በተራቸው ወያኔ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ በድብቅ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር የገንዘብና የውስጥ ድርጅት ስራ ይሰራሉ ብሎ በርካታ ባለ ሀብቶችን ባሰረ ግዜ ከሀዊ ሆቴል ማኔጀር ጋር ጠራርጎ ዘብጥያ ከተታቸው። በወቅቱ ወያኔ ወለጋ ውስጥ ለገሰ ወጊ የተባለን የኦነግ የሽምቅ መሪ ገደልኩ ብሎ ከበሮ የሚደልቅበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ግን የለገሰ ምክትል የነበረው ለገሰ ከመገደሉ በፊት እጁ ንና ሙሉ መረጃዎችን አምስተኛ ፖሊስ ጣብያ አምጥቶ ጓደኞቹን ከድቶ እንዳስጨረሳቸው ውስጥ አዋቂዎች ያወሩ ነበር። ከአስመራም በቀጥታ ከኦነግ አመራሮች ወያያኔ ሙሉ መረጃ ይመጣለት ነበር። እኒህ ሁሉ ሰዎች አሁን የት ሁኑው ይሆን? እያልኩ አሁንም አእምሮየ ይጠይቃል ። አብረውን ተደምረው ደግሞ እያወናበዱን እንደሆነ ባልጠራጠርም።

አሁን መከረኛው ሂልተንና ሰራተኛው ምን ላይ ይሆን? ከአራት አመት በፊት በተደረገ የሆቴሎች ደረጃ ግን ትናንሽ የግል ሆቴሎች በልጠውት እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ አግኝቶ አንዱ አወዳዳሪ የነበረ ሰው ” እዚህ ሀገር በስም ብቻ ትልቅ የሚባሉ ብዙ ድርጅቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ 3 ኮኮብ እንኳን ሳይገባው ዝም ብለን የሰጠነው ድርጅት ቢኖር ሂልተን ነው” አለኝ። ለመሆኑ በዚህ ድርጅት ላይ ላለፉት 20 አመታት የወረደበትን መከራ ታውቃለህ? ስለው አላቅም አለኝ። ይህ ምሳሌ ለአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲም የሚሰራ ነው። ወደፊት ግዜ ሲገኝ እመጣበታለሁ። ለአሁኑ ግን ያለውን ሀብት በጋራ እያሳደጉ እያሻሻሉ እንደመጠቀም ብልጣብልጥ ወስላቶች በጎሳ ስም ተደራጅተው ሲያወድሙ የጎሳው አባላት የሁላችንም የጋራ የሆነው ሀገር ና ድርጅት ከመውደሙ ውጭ ምን ጠብ ይልለታል? በዚህ አይነትስ አዙሪት ውስጥ መቀጠሉ አይሰለቼንም ወይ? አሁን በሀገሪቱ ውስጥ የተተፋን የከንቱ ሀሳብ እንደገና መድገም ነገ በሌላ አብዬት መውደቅ እንዳለ መገንዘብ አቃታቸው ወይ? አምስት መቶ የማይሞሉ የወያኔ ወንጀለኞች በዘረፉት የትግራይ ህዝብ ምን ጠብ አለለት? አሁንስ በኦሮሞ ስም የሚራኮቱ ስግብግቦች ለ30 ሚሊዬን ህዝብ ምን ያዘንቡሉታል ሀገርን ከማዳከም ውጭ? ይህ ሁሉ ሲሆን ደህንነቱ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮው፣ የኢትዬጵያ ሰራተኞች ማህበር መሪዎች ምን እየሰሩ ነበር? በሀጢያቱስ አብረው ተጠያቂ አልነበሩም ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚመጡባችሁ እገምታለሁ። እኔ ግን እምለው ገና ካሁኑ ይህ ነገር ስር ሳይሰድ ለሁላችንም እኩል የሆነች ሀገርን ለመገንባት ያገባኛል እስካላልን ሀገሩም፣ ለውጡም የትም አይደርስም።
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን። ድል ለኢትዬጵያ ህዝብ!!

The post የጎሳ ቅኝት የተቃኜ መተካካት የሚያመጣው ውድመት ። ሂልተን አዲስ አበባን እንደ ምሳሌ። (በዳዊት ሳሙኤል) appeared first on Borkena Amharic