ዘተዋሕዶ


March 11, 2019t

reporter amharic cartoon

***

(ሪፖርተር፤ ርእሰ አንቀጽ፤ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም.)

ለነፃነት፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት በአንድነት መቆም የተቻለ አይመስልም፡፡ ‹እኔ ብቻ ልክ፤ እኔ ያልኹት ካልኾነ ሞቼ እገኛለኹ፤ ኹሉም ነገር በእኔ በጎ ፈቃድ ብቻ መፈጸም አለበት፤› ወዘተ የሚሉ ፉከራዎች እና ቀረርቶዎች ተያይዞ ለመጥፋት ካልኾነ በስተቀር የሚፈይዱት እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ራስንና አገርን ሰላም እየነሱ የሕዝቡን ሕይወት ማመሰቃቀል ያተረፈው ነገር ቢኖር ጽንፈኝነትን ነው፡፡ በፌዴራል መንግሥት እና በክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥንቅጡ በመውጣቱ ምክንያት፣ እንኳን ለመናበብ እና ስሕተቶችን ለማረም በቅጡ የሚነጋገሩ አይመስልም፡፡ የአንድ ፓርቲ ሰዎች የተለያዩ ክልሎችን እየመሩ መናበብ ባለመቻላቸው፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋጩና ደም ሊያፋስሱ የሚችሉ መግለጫዎች እየተሰሙ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ላይ እየተሰሙ ያሉ አሳዛኝ ትርክቶች የነገውን ተስፋ ያጨልማሉ፡፡ አዲስ አበባ፣ ከኢትዮጵያውያን አልፋ የአፍሪካውያን ከተማ መኾኗ እየታወቀ በዕብሪት ‹የእኔ ብቻ› የሚሉ ወገኖች አየሩን መቆጣጠራቸው ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ ሕግ አለ ተብሎ በሚታሰብበት አገር ውስጥ ከሕግ የበላይ በመኾን አገርን ለማተራመስ የሚደረገውን ጥረት፣ መንግሥት በአስቸኳይ መላ ካልፈለገለት እንኳን የተጀመረው ለውጥ የአገሪቱም ህልውና ያሰጋል፡፡ አሁን እየታየ ያለው ማስፈራራት እና ድንፋታ በሕግ አደብ የማይገዛ ከኾነ መንግሥት አገር እየመራሁ ነው ባይል ይሻለዋል፤ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ ሕገ ወጥነት እየበዛ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በሕግ አምላክ፣ ሕግ ይከበር ማለት የተለመደ የሕዝባችን የሕግ አክባሪነት መገለጫ ነበር፡፡ ጉልበተኞች አገር ሲያምሱ እና ሲያተራምሱ፣ ሕግ ማክበር ቀርቶ ሥርዓት አልቦነት ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጥፋት አይዘነጋም፡፡ ዛሬ በሕግ አምላክ ሲባል ሰሚ ሲጠፋ በጉልበታችሁ አምላክ ይባል ወይ? በሠለጠነ መንገድ መነጋገር እና ልዩነትን ማጥበብ ሲቻል፣ የጉልበት መንገድ እየተመረጠ የንጹሐንን ሕይወት ማጥፋት እና ማፈናቀል አልበቃ ብሎ፣ አገር ለማፍረስ ዕንቅልፍ ማጣት ምን ይሉታል? አገር የምትመሩም ኾነ ሥልጣን ለመያዝ የምትፎካከሩ፣ ራሳችኹ ሰላም አጥታችኹ አገር አትበጥብጡ፡፡ የፖለቲካ አክቲቪስትነት ካባ የደረባችኹ ግለሰቦችም ኾናችኁ ስብስቦች፣ ድርጊታችሁ ምን እያስከተለ እንደ ኾነ ራሳችኹን መርምሩ፡፡ የተሰጣችኹን ሥልጣን በአግባቡ መምራት ያቃታችሁ ሹማምንት ሓላፊነታችኹን ለሚችሉት አስረክቡ፡፡ መወሰን የማይችል ተሿሚ፣ በአክቲቪስቶች ቀጭን መመርያ እየተመራ አገርን ገደል ውስጥ ከሚከት ዞር ቢደረግ ይመረጣል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ አጋጭቶ ደም ለማፋሰስ ያሰፈሰፋችኹም አደብ ግዙ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመናትን አብሮ የተሻገረው ክፉ እና ደግ ጊዜያትን በአንድነት አሳልፎ ነው፡፡ ብሔር፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት እዚህ ዘመን የተደረሰው፣ ከመለያየት ይልቅ በአንድነት የሚያኖሩት የጋራ ዕሴቶች ስለሚበዙ ነው፡፡ ይኼን የመሰለ ታላቅ እና ባለ ታሪክ ሕዝብ ይዞ የዘመናት ድህነትን ታሪክ ማድረግ ሲገባና ከሠለጠኑት አገሮች ተርታ መሰለፍ ሲቻል፣ ጥቃቅንና የማይጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተጥዶ አገር ማተራመስ እብደት ነው፡፡ ይህችን ታሪካዊት አገር በዕድገት እና በብልፅግና የአፍሪካ ፈርጥ ማድረግ እየተቻለ፣ ሕዝብን ደም ለማፋሰስ ‹ጉሮ ወሸባዬ› ማለት የለየለት ክሕደት ነው፡፡ በሕግ የበላይነት የምትመራ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት በጋራ መክሮ እና ዘክሮ መደላድሉን ማመቻቸት እየተቻለ፣ አገርን ወደ ፍራስራሽነት ለመቀየር መማሰን ከሚታገሡት በላይ ነው፡፡ ትላንት ለነፃነት ሲጮኹ የነበሩ ልሳኖች አገር ለማፍረስ ሲያላዝኑ መስማት ያንገበግባል፡፡ ራስ ወዳድነት፣ ጥጋብ እና ማናለብኝነት አየሩን እየናኙት እንዴት ስለ ሕግ የበላይነት መነጋገር ይቻላል? እንዴትስ የነገዋን ዴሞክራሲያዊት አገር ማለም ይሞከራል? በሕግ አምላክ!

የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጪያ ይኾናል እንጂ ከሚል የጀብደኞች ኋላ ቀር አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይገባል፡፡ የጋራ የኾነች አገርን እንደ ቅርጫ ዕጣ መጣጣል በታሪክ እና በትውልድ ያስጠይቃል፡፡ ኹሉንም ነገር የእኔ ብቻ ነው ማለት አያዋጣም፡፡ በመንጋ ፖለቲካ በመመራት የሚገኘው ውጤት ምናልባት ከተሳካ ጊዜያዊ ድል እንጂ፣ ዘለቄታዊና አስተማማኝ የኾነ ድል አይኖርም፡፡ ስሕተትን በስሕተት ለማረም መሞከር ከሕዝብ ጋራ ያጣላል፡፡ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ በማሽመድመድ ለዓምባገነንነት ወይም ለሥርዓተ አልቦነት ያጋልጣል፡፡

አሁን በመሬት ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ኹኔታ ከተስፋ ይልቅ ስጋት ያጠላበት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሰሞኑን ዕጣ  በወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ መናበብ አለመቻላቸው ከባድ ስጋት ደቅኗል፡፡ ያገኛትን እየተጎራረሰ ዘመናትን የተሻገረ ሕዝብን በዚህ ጊዜ በኮንዶሚኒየም ምክንያት ማጋጨት ያሳዝናል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ላይ ከግራ እና ከቀኝ የሚሰሙ ተቃርኖዎች ራሳቸውን የቻሉ ስጋቶች ናቸው፡፡ ተሰሚነት አለን የሚሉ የግራ እና የቀኝ ወገኖች መነጋገር እና መደራደር ባለመፈለጋቸው፣ ነገ ከነገ ወዲያ ምን እንደሚከሠት አይታወቅም፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ዝምታም ከሚታገሡት በላይ ኾኗል፡፡ በመካከል ግን ሕዝብ ሰላም አጥቷል፡፡ በሕግ አምላክ!

ኢትዮጵያ ጭንቀት ውስጥ ኾና ሕዝብ መፃኢ ዕድሉ እያሳሰበው ባለበት በዚህ ወቅት፣ የተቃረኑ ወገኖችን በትዕግሥት እና በብልኃት ማስማማት ያስፈልጋል፡፡ ጽንፍ ተይዞ ሁሉም ነገር የቅራኔ ምንጭ ከኾነ፣ እንዴት ነው ለመጪው ምርጫ ዝግጅት የሚደረገው? ዜጎች ከቦታ ቦታ መዘዋወርስ እንዴት ይችላሉ? የሚፈለገው ማኅበራዊ ፍትሕ እንዴት ሊሰፍን ይችላል? ከእጅ ወደ አፍ በኾነ ኑሮ ሥቃይ ውስጥ በሚገኙ ሚሊዮኖች ላይ የዕለት ርዳታ ፈላጊዎች ተጨምረው እና የሥራ ዐጡ ቁጥር እያሻቀበ፣ አገርን ከገባችበት ማጥ ውስጥ እንዴት ማውጣት ይቻላል? የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት አስተካክለው በፍጥነት ሕግ መከበር ይኖርበታል፡፡ የተፈጠሩ ስሕተቶች ካሉም ሕዝብን ማዕከል አድርጎ ማስተካከል ይቻላል፡፡ ሕገ ወጥነትን በሕግ የበላይነት መስመር ማስያዝ ተገቢ ነው፡፡

ከላይ እስከ ታች ያሉ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ከሕገ ወጦች ማጽዳት ይገባል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የማስከበር ሓላፊነት አለበት፡፡ ይኼን ሓላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ የሕግ ማስከበርያ ተቋማቱንና ሕጋዊ ማዕቀፎችን በሚገባ መጠቀም አለበት፡፡ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልጽግና፣ አገራዊ አንድነት፣ ፍትሕ እና አገራዊ ክብር ተብለው በመንግሥት በምሶሶነት የተያዙት ፅንሰ ሐሳቦች ተግባራዊ መኾን የሚችሉት በሕግ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ ለነፃነት፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት በጽናት የሚቆሙ ወገኖች፣ ይህን ጥረት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አገር ወደ ቁልቁለት እየተንደረደረች ዝምታው ሊበቃ ይገባል፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ፣ “በሕግ አምላክ” እንጂ “በጉልበታችሁ አምላክ” እንዳይባል፣ ኹሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባቸውን ሓላፊነት መወጣት አለባቸው! Advertisements