April 25, 2019

“አገርኛ ቋንቋን ከኮምፒዩተር ያዋሃዱ ሳይንቲስት!” በሚል ርእስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለ ዶ/ር አበራ ሞላ የሕወሃት ታሪክና ትልቅ አስተዋጾች ሰፋ ያለ ዘገባ አስፍሯል። ዶ/ር አበራ በእንስሳ ሕክምና ዙሪያ ከሰሯቸው በርካታ አኩሪ ግባራት በተጨማሪ፣ የአፍሪካ ጥንታዊ ብቸኛ ፊደል የሆነው ግዕዝ በኮምፒተር እንዲጻፍ ያደረጉ ምሁር ናቸው። ሰንዳፋ የተወለዱት ዶ/ር አበራ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ቤንች፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ምኢን፣ ጋሙ ጎፋ፣ ዳውሮ፣ ባስኬቶ ኦሮምኛ በትክክልና በብቃት በግዕዝ ፊደል መጻፍ እንደሚቻል ይናገራሉ።

አዲስ ዘመን የሚከተለውን አስፍሯል፡
—————————
ጽጌረዳ ጫንያለው
 የአማርኛ ቀለማትን በኮምፒዩተር

ዶክተር አበራ ሞላ የተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ሠራዊትን ወደ ኮምፒዩተር ያዘመቱ የፊደል ጀኔራል ናቸው። በዚህ የግዕዝ ፊደል ከተራ ጽሑፍ እስከ ተንቀሳቃሽ ፊደልና ሌሎች እንግዳ ጉዳዮችን ወደ ኮምፒዩተር ያለምንም መሸራረፍ እንድናሰፍር አድርገዋል። በብዙ ሀብት የሚገዙትን የኮምፒዩተር የእንግሊዝኛ ፕሮግራሞች የግዕዝ ፊደልም እንዲጠቀምባቸው ያደረጉም ናቸው። አማርኛን ያካተተውን እያንዳንዱን የግዕዝ ቀለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፒዩተር እንዲጻፍ አሜሪካ ውስጥ የፈጠሩት ዘዴ ኢትዮጵያ እንዲመዘገብ ሲሉም ከ30 ዓመታት በላይ የታገሉ ስለመሆናቸው ይመሰክርላቸዋል። የተመዘገበ የአሜሪካ ኮፒ መብትም አላቸው።

ዶክተር አበራ በሕክምናው ዓለም ፈውስ ሲሰጡ፤ በፊደል የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂያቸው ደግሞ ለታላቅ እውቅና ከመሰጠታቸው ጋር ተያይዞ “የግዕዝ አባት” የሚል የቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል። ዶክተሩ ኮምፒዩተርና ፊደላቱን ለማዋሃድ ብዙ ለፍተዋል። ብዙ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበትም አፍሰዋል። ኢትዮጵያ የፓተንት ሕግ የላትም ቢባሉም አላማቸውን ሳይለቁ ከልጃቸው ጋር የመጀመሪያውን የግዕዝ የእስክሪንና የማተሚያ ቀለሞች ሠርተው ለተጠቃሚ አቅርበዋል። ከዓመት በኋላ ደግሞ የፊደሉን ችሎታ በማሳደግ መጀመሪያ በ1981 ዓ.ም. ፖስት እስክሪፕት ከዚያም ትሩታይፕ በኋላም ተንቀሳቃሽ እያሉ ዛሬ ላይ አድርሰውታል። አማርኛና ግዕዝን ወደ ኮምፒዩተር ሲያስገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የስምንት እንግሊዝኛ ስፍራዎችን አስለቀቁ። ቦታውን በየተራ በማጋራትም ይጠቀሙ ነበር። ከዚያ በዩኒኮድ (Unicode) መፈጠር የተነሳ እያንዳንዱ የግዕዝ (Ethiopic) ቀለም የእራሱን ስፍራ እንዲያገኝ አስቻሉት።

የግዕዝ ቀለሞችም የዓለም ፊደላት በዩኒኮድ መደብ ዕውቅና ከአገኙበት እ.ኤ.አ. ከ1989 በኋላም ሠርተው ጨምረዋቸዋል። ትክክለኛዎቹና ሁሉም የግዕዝ ቀለሞች የዩኒኮድ መደብ ውስጥ እንዲገቡም አስችለዋል። የዶክተር አበራ የሁለተኛው ፊደላቸው መነሻ ተወዳጁና ለረዥም ዘመናት ጥቅም ላይ የዋለው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አንደኛው የሞኖታይፕ የፊደል መልቀሚያ መኪና ፊደል ነው። ሌላው ደግሞ የተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት 1917 ዓ.ም. ቁምፊ (Typeface) ነው። የቀለማቱም መልኮች ከዩኒኮዱ ጋር አንድ ዓይነትና መደበኛ የኢትዮጵያ ፊደላትን ያካተተ ሲሆን፤ ቁምፊያቸው ግዕዝኤዲት ዩኒኮድ (GeezEdit Unicode) በመባል ይታወቃል። ውብ ቀለሞቻችንን በወጉና በማዕረጉ መጠቀም የተቻለውም በእዚህ የተነሳ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አበራ፤ የዕውቀት ክምችት እንዲስፋፋ በሶፍትዌር እንዲጠቀሙ ሕዝቡን ያስተማሩም ናቸው። በታይፕራይተር እየጻፉ ሰዓታትን የሚፈጁ፣ በሰልፍ የሚጨናነቁና መጽሐፍ ለመጻፍና ለማጻፍ ብዙ ወጪ የሚያወጡትንም ያሳረፉት ለመሆናቸው ምስክር አያሻቸውም። ዶክተሩ የግዕዝ ፊደላት ከሌሎች የዓለም ፊደላት እኩል እንዲራመዱ አድርገዋል።

ለምሳሌ ያህል እነ “ሀ”፣ “ሐ”፣ “ኀ”፣ “አ”፣ እና “ዐ” አይነት ቀለሞች ምን ይሠራሉ፤ አንዱ በቂ ነው ተብሎ በምሁራኑ ዘንድ ክርክር ተፈጥሮ ነበር። ለእንግዳችን ግን ፊደላት ከዚህ ይልቃሉ። ድምጾቻቸው፣ ስሞቻቸውና ጥቅሞቻቸው ይለያያሉ ብለውም ያምናሉ። ይህ ደግሞ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ አገው፣ ቤንች፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ምኢን፣ ጋሙ ጎፋ፣ ዳውሮ፣ ባስኬቶና እንዲሁም የኦሮምኛ ቋንቋዎችንም ይመለከታል። ሁሉም ቋንቋዎችና ፊደላት የእራሳቸው ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለው ስለሚያምኑ ሁሉም በኮምፒዩተር እንዲከተቡና ዩኒኮድ ውስጥ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው ጋር ተባብረው ሠርተዋል። የግዕዝ ምልክቶችን በተመለከተም መብት፣ ንግድ፣ ብር፣ ሣንቲም፣ ማጥበቂያ፣ ማላልያና አልቦ አኃዝ ፈጥረው በፓተንታቸውም ውስጥ ታትመው አገልግሎት እንዲሰጡ አስችለዋል። አልቦ ዜሮን መፍጠራቸው ለምን አስፈለገ ለሚሉም ከአልቦ (ዜሮ) በታች በአሉ (ኔጋቲቭ) ቁጥሮች እንድንጠቀምባቸው የዜሮ አኃዝ ቀለም መፍጠራቸው አስፈላጊ ነው ይላሉ። ሞዴት (ModEth) በመባል የታወቀውን የቃላት ማተሚያ የማይክሮሶፍትን ዶስ በመጠቀም እ.ኤ.አ. በ1987 አሜሪካ ውስጥ ለገበያ ያቀረቡት ዶክተር አበራ፤ ጊዜው ኮምፒውተሮችና ማተሚያዎች በቂ ኃይል ማግኘት የጀመሩበት በመሆኑ በብዙ ጥረትና ወጪ ተግባራዊ እንዲሆን አስችለዋል። ኢትዮጵያ የፓተንት ሕግ ስላልነበራት የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ሕጉ ሲወጣ ጉዳዩ ይታያል በማለት መጋቢት ፲፪ ቀን ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. ቢወስንም ከሚፈለገው በላይ ጊዜ በመውሰዱ ፈጠራዎቻቸውን በአሜሪካ ፓተንቶች ያስጠበቁት ባለታሪኩ፤ ይህ የሆነው የዓለም ኮምፒውተሮች ፊደላችንን እንዲያውቁ ስለተቻለ፤ ማንኛውም ሰው አከታተቡን አሻሽሎ ፓተንት ሊያወጣ ስለሚችል ኢትዮጵያ እንዳትጎዳና መብቷ እንዲጠበቅ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶክተር ኣበራ ሞላ በግዕዝ ፊደላት የተለያዩ ቋንቋዎችን በኮምፒዩተርና ተንቅሳቃሽ ስልኮች እንድንከትብ የፈጠሩ ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ በፊደልዋ የመጠቀም መብትዋ እንዳይቀማባት ፓተንቶች በማውጣት ዜግነታዊ ግዴታቸውን የተወጡ ታላቅ ባለውለታ ናቸው። ብዙ ሰዎች ይኸን ረዥምና እልህ አስጨራሽ ሥራቸውን ሳይረዱ የግዕዝ ፊደል ያልሆነውን የአማርኛ ታይፕራይተር አማርኛ ነው በሚሉ ጭምር ተወናብደዋል። የአማርኛ ታይፕራይተር ፊደል የአማርኛ ፊደልን የማይጽፍ ከመቶ ያነሱ ቁርጥራጭ የፈጠራ ነገሮችን የሚቀጣጥል ጊዜው ያለፈበት መሣሪያና አጠቃቀም እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተሩ፤ ፊደል ሳይከትቡ ከተብን በሚሉና አንዳንዱን ፊደል በሦስትና አራት መርገጫዎች የሚጽፉ የግዕዝን ፊደል በማዳከም ትልቅ ችግር ፈጥረዋል፤ እየፈጠሩም ነው ይላሉ።

ሥራቸውን እንደጀመሩ የቢለን፣ ጉራጌ እና ሳሆ ምሁራን የቋንቋ ፊደሎቻቸውን እንዲጨምሩላቸው ናሙና ጽሑፎችን የላኩ ሲሆን፤ ከእዚሁ ጋር በማያያዝ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች እንዲከተብ አዲስ የአከታተብ ዘዴ ፈጥረው አዳዲስ የፊደል ገበታዎች አቅርበዋል።

አበርክቶ ለአገር

ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ምስጢር “ሕዝቡ እየተግባባ መሆኑ አበረታቶኝና ኢትዮጵያም ፓተንቶቼን (የፈጠራ ዕውቅና) ስለሰጠችኝ ነው። ያስተማረኝን ሕዝብ ውለታውን በትንሹም ቢሆን እንድመልስ ለብዙ ዓመታት በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ሳቀርብ የነበረውን ስጦታዬንም በሥራ ላይ ለማዋል ነው። ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ሶፍትዌር ፕሮግራሞቼን በነፃ በመስጠት አገሬ የምትጠቅምበትን ለማዘጋጀትም ነው” ይላሉ። ዶክተሩ ሕዝቡ የሚያውቃቸውና የማያውቃቸው ስጦታዎችን ይዘው መጥተዋል። በዋጋ ግምቱም በዶላር በሚሊዮኖች ይቆጠራል ይላሉ። ኮምፒዩተራይዝ ያደረጉት የግዕዝ ፊደል ለብዙ ሺህ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በእጃቸው ሲጽፉ የነበረበትን ሁኔታ ያሻሻለ እንደሆነ ሁሉ በተለያየ መንገዶች ብዙዎችን ለመጥቀምም ነው ወደ አገራቸው የመጡት። ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንም በነፃ የሰጡትን ድረገጽ (http://freetyping.geezedit.com/) በመጠቀም በአማርኛ እንዲከትቡ ከተደረገ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። ዶክተር አበራ ኮምፒዩተር ለአማርኛ ጽሑፍ እንዲጠቅም ያሰቡት እ.ኤ.አ. በ1982 ሲሆን፤ ጊዜው ብዙ ሰዎች ኮምፒዩተርን መንካት የሚፈሩበት ነበር።

ይሁንና እርሳቸው “የተለያዩ ኮምፒዩተሮችንና ፕሮግራሞችን እየሞከርኩ ሁለተኛ ሥራ አደረግሁት” ይላሉ። ከአምስት ዓመት በኋላ ለአይቢኤም ፒ.ሲ. (IBM PC) ለሕዝብ ሽያጭ አቅርበው አማርኛን በኮምፒውተር ለመጻፍ አስችለዋል። ዛሬ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በግዕዝና አማርኛ ቋንቋዎች ማስተማር የመጀመሩም መንስኤ እርሳቸው እንደሆኑም ይነገራል። “አምስት መቶ የሚጠጉትን የግዕዝ ፊደሎቻችን ለሰማንያ ቋንቋዎቻችን ለመጥቀም ተዘጋጅተው ሳለ በሚገባ ስላልተጠቀምንባቸው ይህ ትውልድ ሊያስብበት ይገባል” ብለዋልም። ለስኬታቸው መንስኤ የሆኑት ቤተሰቦቻቸው፣ ወንድሞቻቸውና ሶፍትዌሩን የገዙት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ሄልወት ፓካርድ በየጊዜው በአዋሷቸው ማተሚያዎች በመጠቀምም ነበር። ፊደሉን እየከፈሉ ማሠራት ስለከበደ ዲጂ-ፎንትስ የሚባል ኩባንያ ራሳቸው እንዲቀርጹና እንዲሠሯቸው ፈቅዶላቸዋል።

ሽልማት

የግዕዝ ፈጠራ ግኝቶቻቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ በማቅረብ እስካሁን አራት የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝተዋል። ኢትዮጵያም ሶስት የግዕዝ ፓተንቶችን በ2011 ዓ.ም. ሰጥታቸዋለች። እነዚህም ግዕዝን በአንድና ሁለት መርገጫዎች በኮምፒዩተሮች፣ በስልኮችና በመሳሰሉት መጠቀም ያስቻሉ ዘዴዎች ናቸው። ኮምፒውተሩ ግዕዝ ፊደላትን እንዲከትብና እንዲመዘግብ ሲያደርጉ ግኝቶቹ በፕሮግራሚንግ ብቻ ሳይሆኑ ለእንግሊዝኛ ፊደላት የተሠራውን ቴክኖሎጂ ለ37 የግዕዝ ቤት ቀለሞች፤ እንዚራኖቹና ሌሎችም ጥቅም መሥራታቸውም ነበር የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ ያደረጋቸው።

በአሜሪካ የአርባ አራት ዓመታትን ኑሮ አሳልፈውበታል። በዚህ ቦታ እውቀትና ሙያ ካለ መኖር እንደሚቻልም አይተውበታል። ችግራችን የነበረው ዘመድ አዝማድ በአካባቢያችን አለመኖሩ ነበር ይላሉ። አንዳንዶች አሜሪካ ሲኬድ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ የሚሆን ይመስላቸዋል። ይሁንና ማንኛውም ሰው ወደ አሜሪካ ሲመጣ ዝቅ ብሎ መጀመር እንዳለበት ማሰብ ይኖርበታል። ይህ አስተሳሰብ ብዙዎችን መጸዳጃ ቤት ከማጽዳት አውጥቶ ትልቅ ደረጃ ያደረሰ እንደሆነም ያስረዳሉ። አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በዓላማ ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በመሆናቸው ስኬታማ ናቸው። ተስፋ መቁረጥም አይታይባቸውም። በዚህም የትም አገር ሄደው ስኬታቸውን ያሳያሉ ይላሉ። የኢትዮጵያውያን የመሥራት አቅማቸው ትልቅ እንደሆነም ይናገራሉ። “ትልቅ ነን እያልን መጓዛችን ለልቦናችን ጠቅሞናል። ይህ ችሎታችንንና ጥንካሬያችንን እንድናሳይም እድል ሰጥቶናል። በቅኝ ግዛት አለመገዛታችንና በአቅማችን መሥራትን የለመድን መሆኑ በአሜሪካ ችግር እንዳይገጥመን አድርጓል” ይላሉ። የእኔ ደስተኛ ሕይወት መምራት መሰረቱ ያለመገዛት ወኔ፤ በራስ መተማመንና ጥንካሬን የማሳየት ልምድ ነው ይላሉ።

ከፋ ጠቅላይ ግዛት በሚሠሩበት ጊዜ ነበር በጓደኛቸው ፍቅረኛ አማካኝነት ዓይንና ልባቸውን ያሸነፈችውን ሠናይት ከተማን ያገኟት። ከ45 ዓመት ትዳር በኋላ ዛሬ ሦስት ልጆችና አምስት የልጅ ልጆችን አይተዋል። ይህ በፍቅር የበሰለ መስተጋብራቸው ደግሞ በሥራ መተጋገዛቸውንም አጠንክሮታል። ባለቤታቸው በሶሻል ወርክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጨረሻ ጊዜ አፄ ኃይለሥላሴ ዲግሪ ሲሰጡ የተቀበሉና በመስኩም ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው በመሆናቸው በሚያስፈልገው ሁሉ ያግዟቸዋል። ልጆቻቸውም በምህንድስና፣ በሕግና በኢኮኖሚክስ የተመረቁ በመሆናቸው ሁሉም በየዘርፉ ይደግፏቸዋል።

መልዕክተ ዶክተር አበራ

“ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ለማደግ ከተባበርን ብዙ ጊዜ አይፈጅብንም። ለዚህም ነው ሌሎች አገራት የእኛ የሆነውን ቶሎ ተቀብለው ወደ ሥራ የሚያስገቡት። አገር የሚለውጥ ነገር ላይ ሁላችንም መሥራት አለብን። ይህ መሆን ያለበት ግን በመሰራረቅ ሳይሆን በመተጋገዝ ነው። በትክክል አገራችንን ሊያሳድግ የሚችል ተግባር ላይ መሰማራት አለብን” ይላሉ። በተለያዩ ጊዜያት ጥቂት ሰዎች “በኮምፒዩተር አማርኛ ማጻፍ የጀመርነው እኛ ነን” እያሉ ብቅ ብለዋል። ከ30 ዓመት በፊት ይህንን ተግባራዊ ያደረገ የለም፤ የፓተንት መብትም ማንኛውም ሰው የለውም። “ግኝቶቼን መነፈግ የለብኝም። እኔ ባልኖርና መብታችንን ባላስጠብቅ ኖሮ በፊደላችን ለዘለቄታው መጠቀማችን አጠራጣሪ ሊሆን ይችል ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ እንዲያውቅ የምፈልገው ለአገሬ እድገት ምን ያህል እንደደክምኩና አሁንም ማድረግ ባለብኝ ሁሉ እንደማግዝ ነው” ብለዋል። በእያንዳንዱ ሥራችን ላይ የማስተማሩ ተግባር ከምሁራን ይጀምራል የሚሉት ዶ/ር አበራ ሞላ በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም የአማርኛ ፊደላት መልኮች በትክክል የማናውቅና አንድ የአማርኛ ዓረፍተ ነገር ውስጥ እንግሊዝኛ ሳንቀላቅል የማናወራ ጥቂት ዜጎች የመፈጠሩ መንስኤ ተገቢው ሥራ ባለመሠራቱ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል መልዕክታቸው ነው። ሰላም!

አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011 ዓ.ም. ገጽ 9 (ሕይወት እንዲህ ናት)

Interview of Dr. Aberra Molla by Tsigereda Chanyalew of Addis Zemen Ethiopian newspaper. (Part 2)