September 8, 2019

Source: https://ethiothinkthank.com/2019/09/08/the-dream-of-oppressed-ethnio-nationalists-is-to-become-another-oppressor

መስከረም 8, 2019

በሰላማዊ መንገድ ሆነ በትጥቅ ትግል፣ አዲስ ሀገር ለመመስረት ሆነ ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚካሄድ ፖለቲካዊ ንቅናቄ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል። እኩልነት እያንዳንዱ የማህብረሰቡ አባል “ለራሱ የሚገባው መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለሁሉም ይገባል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም በመልከዓ ምድር፥ ታሪክ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሥነ-ልቦና፥…ወዘተ ትስስር ባላቸውና በሌላቸው ማህብረሰቦች፥ ቡድኖችና ግለሰቦች መካከል ልዩነት አይፈጥርም። ስለዚህ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ከራስ ፍላጎትና ምርጫ ባለፈ ስለ ሌሎች ፍላጎትና ምርጫ፣ ስለ ወደፊት አብሮነትና አንድነት ማሰብ ይጠይቃል።

ነገር ግን የእኩልነት ጥያቄን በኃይል ለማዳፈን የሚሞክር መንግስታዊ ስርዓት ባለበት ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ይቀሰቀሳል። አምባገነናዊ መንግስት የህዝብን ጥያቄ በኃይል ለማፈንና በጉልበት ለማዳፈን ጥረት ሲያደርግ በራስ የመወሰን መብትን (right of self-determination) ዓላማ ያደረገ የዘውግ ብሔርተኝነት (ethno-nationalism) ንቅናቄ ይፈጥራል። በእርግጥ በራስ የመወሰን መብት ለእኩልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል። ምክንያቱም በራስ የመወሰን መብት ከተረጋገጠ ማህብረሰቡ የወደፊት ዕድሉን በራሱ የመወሰን፥ በራሱ ሕግና ደንብ የመተዳደር እና አስተዳደሪዎቹን በራሱ የመምረጥ መብትና ስልጣን ይኖረዋል። በመሆኑም የእኩልት ጥያቄ ያነሳው የህብረተሰብ ክፍል ራሱን በራሱ ማስተዳደርና መምራት ከቻለ በጨቋኙ ስርዓት የተነፈገውን መብት፥ ነፃነት፣ ፍትህና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይችላል።

ይሁን እንጂ የፖለቲካ ልሂቃኑ በትግሉ ዓላማና ግብ ዙሪያ አንድነትና ቁርጠኝነት ለመፍጠር በማህብረሰቡ ዘንድ የሚያሰርፁት የዘውግ ብሔርተኝነት የትግሉን አካሄድና ውጤት ይቀይረዋል። ምክንያቱም ብሔርተኝነት፤ ከቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ታሪክና ሥነ-ልቦና አንፃር ያለውን ልዩነት ይበልጥ በማስፋት፣ ከቀድሞ ታሪክ በጎውን በማደብዘዝ መጥፎውን በማጉላት፣ ከወደፊት አብሮነት ይልቅ መለያየትን በመስበክ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከት ነው። በመሆኑም የብሔር ፖለቲካ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለመተማመንና ጥርጣሬ፣ ወገንተኝነትና ጥላቻ፣ ቁጣና ምሬት፣ ፅንፈኝነትና የተጠቂነት እንዲሰርፅና እንዲስፋፋ ያደርጋል።

የብሔር ፖለቲካ መሰረታዊ ዓላማ በማህብረሰቡ ዘንድ ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን “ልዩነቶች” አጉልቶ በማውጣት ዜጎችን በቋንቋ፥ ብሔር፥ ባህል፥ ልማድ፥… ወዘተ በመለያየት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን የኃይል ሽኩቻ በማሸነፍ የፖለቲካ ስልጣን (power) መቆጣጠር ነው። “Pierre Bourdieu” የተባለው የፈረንሳይ ምሁር እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም ባወጣው ጥናታዊ ፅሁፍ፣ በብሔር ፖለቲካ አማካኝነት የሚገኘው “የመለያየት ኃይል” (separative power) እንደሆነ ይገልፃል። ተመሳሳይ በሆኑ ነገሮች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ የማይለያዩ ነገሮችን በመለያየት የሚገኝ ኃይል የህዝብን ጥቅም ከማስከበር ይልቅ ህዝብን መጠቀሚያ የሚያደርግ ነው።

Image © Nazret.com

በእርግጥ ብሔርተኞች ራሳቸውን የሕዝብ ተወካዮች እንደሆኑ፣ ከግል ጥቅም ይልቅ ለህዝብ ጥቅምና ተጠቃሚነት እንደቆሙ ሲገልጹ መስማት የተለመደ ነው። ነገር ግን በብሔር ፖለቲካ አማካኝነት የሚገኘው ኃይል የጥቂቶችን የስልጣን የበላይነት እና የቁሳዊ ሃብት ጥማት ማርኪያ እንደሆነ አሜሪካዊቷ ምሁር “Catherine Killer” ትገልፃለች። በአጠቃላይ ብሔርተኝነት የሕዝብን ጥቅም ከማረጋገጥ ይልቅ ሕዝብን መጠቀሚያ የሚያደርግ የፖለቲካ አካሄድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ብሔርተኝነት ለራስ ጎሳ፥ ብሔር ብቻ ማሰብና ማድላት፣ በሌላው ላይ ጥላቻ ማሳየት እንደመሆኑ በአድልዎና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነው። ለራስ ጎሳ/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ፣ የሌላን ጎሳ/ብሔር ደግሞ ማግለል፥ መለየትና መጥላት ያካትታል። ስለዚህ በብሔርተኝነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ።

እንደ “Jean Jacques Rousseau” አገላለፅ፣ የራስን ጎሳ፥ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ከሌሎች የተሻለ አድርጎ ማሰብ እና/ወይም ለሌሎች ተወላጆች ደግሞ ዝቅተኛ ግምትና ክብር የመስጠት መሰረታዊ ዓላማ ሰዎችን እርስ-በእርስ በጭካኔ እንዲገዳደሉ ያደርጋል። በዚህ መሰረት በራስ-ወዳድነት (Egoism) እና ጥላቻ ስሜት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፤ ከመግባባትና መተማመን ይልቅ የጠላትነትና ፍርሃት መንፈስ ያሰርፃል። ስለዚህ ብሔርተኝነት ፍርሃትን በመቆስቆስ፣ ጭፍን ወገንተኝነትና ጥላቻ በማስረፅ ሰብዓዊ ፍጡርን ወደ አውሬነት ይቀይራል። ይህ ከሰው ልጅ መልካምነት ይልቅ የጭካኔ ባህሪን፣ ከሰብዓዊነት ይልቅ አውሬነትን፣ ከመግባባትና መተማመን ይልቅ ጥርጣሬና ፍርሃትን በመፍጠርና በማስፋፋት ለእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት መንስዔ ይሆናል።

ብሔርተኝነት በማህብረሰቡ ዘንድ በስፋት ከሰረፀ በኋላ በቀላሉ ማስወገድ አይቻልም። “Diamond and Plattner” (1994) የተባሉት የዘርፉ ምሁራን እንደገልፁት፣ የብሔርተኝነት አመለካከት በማህብረሰቡ ውስጥ ከሰረፀ በኋላ፤ ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬን፣ ከትህትና ይልቅ ቁጣና ምሬትን፣ ከመስማማት ይልቅ ፅንፈኝነትን፣ ከመቻቻል ይልቅ የተጠቂነት ስሜት እንዲስፋፋ ያደርጋል። በራስ ወዳድነትና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ የብሔርተኝነት አመለካከት ከማህብረሰቡ ውስጥ ማስወገድ ካልተቻለ ደግሞ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መግንባት አይቻልም። ከዚያ ይልቅ ከቀድሞ የባሰ ጨቋኝና አምባገነን ስርዓት እንዲፈጠር ያስችላል። በዚህ መሰረት የጭቁን ብሔርተኞች ህልም ከቀድሞ የባሰ ጨቋኝና ጨካኝ የሆነ ስርዓትና ማህብረሰብ መፍጠር ነው።


Nationalism, Ethnic Conflicts, and Democracy. Baltimore – London: Johns Hopkins University Press, 1994.