April 29, 2020

እዚህ ሃገር ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው መርህ አልቦነት ነው፡፡ፖለቲከኞች እንደ መሪ መርህ አልቦ የመሆናቸው ነገር ህዝቡንም ማወዛገቡ አይቀርም፡፡ የሃገራችን ፖለቲከኞች በአመዛኙ መርህ የሚመስላቸው የራሳቸው ፖለቲካዊ ፍላጎት ነው፡፡ የእነሱ ቀዳሚ ፖለቲካዊ ፍላጎት ደግሞ ስልጣን ላይ መቆናጠጥ ነው፡፡ መርህ አልቦ ሰው ስልጣን የሚፈልገው ደግሞ የሚጠላውን ለማጥፋት፣ ወይ እንደ ህወሃት በመንደር ተቧድኖ ለመዝረፍ አለያም የስነ-ልቦና ቀውስን በንግስና ለማስተንፈስ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ የሃገር ጉዳይ፣ የህዝብ እጣ ፋንታ ዋነኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ በበኩሌ መርህ አልቦ ሰው ሃገርን እና ህዝብን የሚያስቀድምበት የአእምሮ ክፍል ያለው አይመስለኝም፡፡ የመርህ አልቦነት ዋናው መነሻው ራስ ወዳድነት ነው፡፡ መርህ አልቦ ሰው መርህ የሚመስለው የራሱን ፍላጎት የሚያረካበት ማንኛውም መንገድ ነው- የትም ፍጭው ዱቄቴን አምጭው ነገር!

…………..

አሁን ሃገራችን ያለችበት አጣብቂኝ የሚታወቅ ነው፡፡ የፖለቲካ ትኩሳታችን ሳይበርድ ኮሮና መጥቶ ሌላ ፈተና ደቅኖብናል፡፡ በዚህ መሃል ሁሉ እንዴትም ተፈጭቶ ስልጣኑ እንዲመጣለት የሚፈልገው ብዙ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ “ምርጫ በሰዓቱ አደርጋለሁ” ከሚል ጀምሮ የስልጣን ጥሙ በመራው መንገድ ሁሉ የሚነጉደው ብዙ ነው፡፡ በሃገራችን በምርጫ ሰሌዳው ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ግልፅ በመሆኑ መንግስት አራት ህጋዊ አማራጮችን አቅርቦ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡ በአንፃሩ አቶ ጃዋር መሃመድ ይህ ህጋዊ አካሄድ እንደማያዋጣ፣ አራቱም በመንግስት የቀረቡ አማራጮች የማይሆኑበትን ነገር ነቅሶ በማስቀመጥ አስታውቋል፡፡ አማራጮቹ እንደማይሆኑ ሲያስረዳም የሚሆነው ፖለቲካዊ አማራጭ እንደሆነና ይህ አማራጭ ደግሞ ምን መሆን እንዳለበት ቀጥሎ አንደሚያስነብብ ተናግሯል፡፡

……………………

ጊዜውን ወስዶ ሃሳቡን ስላጋራን አመስግኜ ፅሁፉን ሳነብ የታዘብኩትን መርህ አልቦነት ላስቀምጥ፡፡ መሰረታዊው መርህ አልቦነት የክርክሩ መንደርደሪያ ህጋዊ ማዕቀፍ ሆኖ ሳለ ብቸኛው መፍትሄ ግን ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው ብሎ ማስቀመጡ ነው፡፡ ጃዋር በክርክሩ አሁን ያለው አስፈፃሚም ሆነ ህግ አውጭ የመንግስት አካል ከመስከረም 30 በኋላ ህጋዊ የማይሆንበትን ምክንያት የሚያጣቅሰው ከህጋዊ መርሆዎች አንፃር ነው፡፡ ለምሳሌ በሃገሪቱ ምርጫ የሚካሄደው በአምስት አመት መሆኑ፣ የፓርላማው የስራጊዜ የሚያበቃው መስከረም 30 መሆኑ፣ ጠ/ሚው ፓርላማውን በትነው በስድስት ወር ውስጥ ሌላ ምርጫ መጥራት አለመቻላቸውን (የፓርላማው ጊዜ እያበቃ ስለሆነ) ሁሉ ሲያስረዳን ህጋዊ መስመሮችን እያጣቀሰ ነው፡፡ ሃገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስተዳደር የማይቻለው ኮሮና ከመስከረም 30 በኋላ ችግር መሆኑ ሊቀር ስለሚችል መሆኑን ጠቅሶ ይህ የማይበቃ ሲመስለው ደግሞ ፓርላማው ራሱ በትክክለኛ ምርጫ ያልተሰየመ፣ የአንድ ፓርቲ ሰዎች ክምችት መሆኑንም ያክላል፡፡ (እዚህ ላይ ከአንድ ወር በፊት ፓርላማው የዲ/ዳንኤል ክብረትን ሹመት በብዙ ድምፅ መቃወሙን ተከትሎ ጃዋር ራሱ ፓርላማውን ህጋዊ አካል አድርጎ እንዴት ያሉ ነገሮችን ሲሰነዝር አንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ነገር !)

…………………..

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ ጃዋር መንግስት ያቀረባቸው አራት አማራጮች እንዴት ተገቢ እንዳልሆኑ ያስረዳን ህጋዊ መርሆዎችን እየጠቀሰ ነው፡፡ ሆኖም ወደ መፍትሄው ሲመጣ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ የእኔ ጥያቄ መንግስት ያቀረባቸውን አማራጮች ከህጋዊ ማዕቀፍ አንፃር ተንትኖ ከፖለቲካዊ ማዕቀፍ አንፃር መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በህጋዊ ማዕቀፍ አንፃር እየተተነተኑ ያሉ ጉዳዮችን በተጀመረበት የህጋዊ ትንታኔ ማዕቀፍ አኳያ ህጋዊ መፍትሄ ማፈላለጉን ጃዋር ያልወደደው ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡

……………………….

መልሱ ቀላል ነው! ህጋዊ ማዕቀፎች የጃዋር ጎራን(ህወሃት ጨምሮ)የስልጣን ተጋሪ ሊያደርገው አይችልም፡፡ የፖለቲካ ማዕቀፍ የተባለው መፍትሄ በዋናነት የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚል አይነት መፍትሄ ማካተቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ዳር እየተገፋ ያለውን አክራሪ የኦሮሞ/የትግሬ  ብሄርተኛ የፖለቲካ ጎራ ወደ ውሳኔ ሰጭነት የማምጣት እድል ያለው ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጃዋር ለውጡን ተከትሎ ወደ ሃገርቤት ሲመጣ የፖለቲካ ካልኩሌተሩን የሰራሁ እኔ ነኝ እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ንግግር ጃዋር ወደ ሃገርቤት ሲመጣ  የሃገሪቱን ፖለቲካ የመዘወር ምኞት ሰንቆ እንደመጣ ይጠቁማል፡፡ ይህ ነገር ቢሳካ ኖሮ የሃገራችን ቀጣይ ምርጫን ውጤት የእርሱ ፖለቲካዊ ጎራ በሚፈልገው መንገድ ለመቃኘት እድል ይሰጠው ነበር፡፡ ሆኖም አልሆነምና ጃዋር ተስፋ አድርጎት ከመጣው ከመሃል ፖለቲካ አድራጊ ፈጣሪነት ተገፍቶ ወደ ተከላካይነት ወርዷል፡፡ ይህንንም ለማ እና አብይ እንደከዱት በተደጋጋሚ በመናገር አስመስክሯል፡፡ ጃዋር ፖለቲካዊ ያለው መፍትሄ በከዳተኝነት የሚከሰውን የአብይ መንግስት ከነአካቴው ከስልጣን እጣ ፋንታ ከመሰረዝ እስከ  ስልጣን ለማጋራት እንዲገደድ በማድረግ ለጃዋራዊያኑ ጎራ ተመልሶ አድራጊ ፈጣሪ የመሆንን ዕድል ይከፍታል፡፡ በዚህ መንገድ ፅንፈኛ ብሄርተኝነት ዳግም የውሳኔ ሰጭነትን እድል  ያገኛል፡፡ በጃዋር በኩል ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚባለው ይህ ነው፡፡

………………………

ሌላው ጥያቄ ፖለቲካዊም ሆነ ማንኛውም መፍትሄ መሰረት የሚያደርገው አሁን ሃገሪቱ እየተገለገለችበት ያለውን ህገመንግስት ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ በርካታ እንከኖች ቢኖሩበትም እስካልተቀየረ ድረስ በእርሱው መመራት ግድ ነው፡፡ የጠ/ሚ አብይ አስተዳደር እንደመፍትሄ አማራጭ ብሎ ያቀረባቸው አራት መንገዶችም መነሻቸውን ያደረጉት የሃገሪቱን ህገመንግስት የሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ በነገራች ላይ የምርጫ ጊዜን ስለማራዘም የሃገራችን ህገመንግስት እንደሚወራው ምንም ያላለ አይደለም፡፡ በአንቀፅ 54 ላይ በተለይ የተሻለ መፍትሄ የሚጠቁም ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ይህችን ቦታ ጃዋር ያለፋት “የፌደራሉም ሆነ የክልልሎች ፓርላማ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያልተመረጠ ስለሆነ….” በምትል አስቂኝ የአራዳ ሽወዳ ነው፡፡ ፓርላማው ጃዋር  የሚፈልገውን አጀንዳ ሲያስፈፅም ደግሞ እንዴት ህጋዊ መስሎ እንደሚታየው የዲ/ዳንኤል ሹመት ውዝግብ ምስክር ነው፡፡

……………………..

የሆነ ሆኖ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚለው ነገር  በጃዋር በኩል እንደመፍትሄ የተነሳው የፖለቲካዊ ሃይሎችን ያስማማል ተብሎ አይደለም፡፡ ይልቅስ ጃዋር ከሚፈልገው የፖለቲካ ዘይቤ ውጭ እየሄደ ያለውን የአብይ አስተዳደር ለማወክና ሃገሪቱን ብጥብጥ ውስጥ ለመክተት ነው፡፡ የዚህ ጥቅሙ የጃዋራዊ አክራሪ ብሄርተኝነት ወይም ህወሃታዊ የዘረፋ ቡድኖችን ወደስልጣን ደጀሰላም የማቅረብ ጭላንጭል ይዞ ሊመጣ የመቻሉ ተስፋ ነው፡፡ ለዚህ ነው በክልላቸው፣ ለብቻቸውም ቢሆን ምርጫ እንደሚያደርጉ አስረግጠው ሲናገሩ የሰነበቱት ህወሃቶች ሳይቀሩ በምርጫ ጉዳይ ላይ ሊነጋገሩ ገስግሰው አዲስ አበባ የተገኙት፡፡

የጃዋር “የፖለቲካ መፍትሄ” ጥሪ ምን ፍለጋ ነው?