ሐራ ዘተዋሕዶ

October 21, 2020 

/ብፁዕ አቡነ ኤልያስ/

***

የመሪዎች የቅስቀሳ ቃል፣ በክርስቲያኖች ላይ እየተባባሰ ለመጣው ጥቃት አንዱ መንሥኤ እንደኾነ የገለጹት የስዊድንና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፥ በሰላም እና በመተባበር ቃል፣ የሕዝቡን  ሰላም ጠብቀው አንድነቱንና ልማቱን እንዲያጠናክሩ፣ ቤተ ክርስቲያን ማረም እና መገሠጽ እንደሚገባት አሳሰቡ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን ለሚያካሒደው የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባው፣ የመክፈቻ ጸሎት፣ ዛሬ ሠርክ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም የተደረገ ሲኾን፤ ብፁዕነታቸው በመርሐ ግብሩ ላይ በሰጡት ትምህርት፣ መሪዎች ከአንደበታቸው በሚወጣ የቅስቀሳ ቃል፣ ክርስቲያኖችን ለግድያ እና መፈናቀል እየዳረጉ በመኾናቸው፣ በንግግራቸው ተቆጥበው እና ሰላምን ሰብከው፣ ከልመና ያወጡት ዘንድ ልናርማቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

“አንደበት እሳት ነው፤ ትንሽ እሳት ጫካ እንደምታቃጥልኹሉ፣ መሪዎች ከአንደበታቸው በሚወጣ ቃል፣ ሰላማችንንና አንድነታችንን እያጣንና እያበላሹት ነው፤ ክርስቲያኖች እንዲገደሉ እያደረጉ ነው፤ አንደበታችኹ እሳት ነው፤ እንበላቸው፡፡ አንደበታቸው ተቆጥቦ፣ ሰላምን ሰብከው፣ ሕዝቡ በሰላም፣ በመተባበር፣ በአንድነት እንዲኖር፣ ከልመና እንዲወጣ ያድርጉ፤” በማለት አሳስበዋል፡፡

እንደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ያሉት አካባቢዎች፣ ከዐሥርት ዓመታት በፊት የጥይት ድምፅ የማይሰማባቸው እንደነበሩ ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፣ ዛሬ ሰላማቸውን እያጡ የሚገኙት፣ የሕዝብን አንድነት እና ኅብረት በሚያበላሽ የአንደበት እሳት በመኾኑ፣ መሪዎች በሰላም ማሰሪያ ቃል አካባቢውን እንዲጎበኙት በትምህርታቸው መክረዋል፡፡

ይልቁንም ክርስቲያን ምእመናን፣ ሕግ በሚፈቅድላቸው ቦታ ተዘዋውረው ለመኖር እና ለመሥራት መሰቀል እና መገደል እንደሌለባቸው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡ ይኸው ዜግነታዊ መብታቸው፣ በሕገ መንግሥቱም የተረጋገጠ ቢኾንም፣ ክርስቲያኖች በሰላም እና በፍቅር ሊኖሩ ያልቻሉበት፣ “የሚገርም ጊዜ ላይ ነው ያለነው” በማለት እየተባባሰ የመጣው ጥቃት ያሳደረባቸውን ቁጭት ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትሻው፣ ኢትዮጵያውያን፥ በነፃነት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነት እንዲኖሩ እንጂ፣ የበላይነትን እንደማትፈቅድ፣ “የበላይነት” የሚልም አስተምህሮ እንደሌላት አስረድተዋል፡፡ “እኛ የበላይ እንኹን አንልም፤ ብለንም አናውቅም፤ ይኼ የእኔ ክልል ነው የሚል ከየት መጣ? የት ተፈጠረ?” በማለት ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል፡፡

“በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ያለውን ችግር እና ፈተና በዕድሜያችን አልሰማነውም፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ስደቱ እና መከራው የሚያበረታን እንጂ ፀራውያን እንደሚመስላቸው የሚያደክመን እንደማይኾን አስገንዝበዋል፡፡ ኾኖም ቤተ ክርስቲያን፣ “ይህ ለምን ይኼ ኾነ? ብላ ትጠይቃለች፤” ሲሉ ለምእመናንዋ ደኅንነት መጠበቅ እንደምትሟገት ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡ ወዲህም ደግሞ፣ “አይዟችኹ፤ እንደ ልዩ ነገር አትቁጠሩት፤” ብላ ሕዝቧን ማጽናናት እንዳለባት አሳስበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ “ይህ የነእገሌ ነው” ብላ ሳትለይ፣ የአገርን ታሪክ በራሷ ፊደል ጽፋ እና ደጉሳ በብዙ ድካም እንዳቆየች አውስተው፣ ባለታሪክ የኾነው ሕዝብዋም፣ ሊገደልና ሊሰቀል አይገባውም፤ በማለት የቀጠለውን የግፍ ድርጊት ኮንነዋል፡፡ ዓለም ሲያደንቃት የነበረች ኢትዮጵያ፥ ለኹሉም የምትበቃ የሰላም እና የፍቅር አገር ወደ መኾን እንድትመለስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባው አጥብቆ መጠየቅ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡