ኢሕአፓ የቅስቀሳ ሥራዬ በፖሊስ ተስተጓጎለብኝ አለ
- ከህዝቡ አበረታች ምላሽ ማግኘቱን አሳውቋል
ከ44 ዓመታት በኋላ፣ በአዲሰ አበባ ልዩ-ልዩ ሥፍራዎች ሕዝባዊ ቅስቀሳ ለማድረግ መርሃ-ግብር የነደፈው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ከህዝቡ አበረታች ምላሽ ቢያገኝም፤ የቅስቀሳ መርሃ-ግብሩ በፖለሲ መስተጓጎሉን ለኢትዮ-ኦንላይን ገለፀ፡፡ በመጪው ኅዳር ወር ነባር-አመራር ኃላፊነቱን ለወጣቶች የሚያስረክብበትና የሚተካካበት ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያዘጋጅ አሳውቋል፡፡
ኢሕአፓ፣ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ሕጋዊ ህዝባዊ ቅስቀሳ ለማድረግ ለአዲስ አበባ መስተዳደር አስቀድሞ እንዳሳወቀ ገልጿል፤ ነገር ግን የከተማ መሥተዳድሩ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ከጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ጋር ጉዳዩን በማያያዙ፣ ለሙሉ ቀን የተያዘው መርሃ-ግብር ተስተጓጉሏል ብሏል፡፡
በቅዳሜው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ላይ፣ ሃያ-ሁለት እና ዘነበወርቅ አካባቢዎች በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በኢሕአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ተሰማ፣ ሌሎች የፓርቲው ባልደረቦች ለእስር መዳረጋቸውን በእለቱ በህዝባዊ ቅስቀሳ መርሃ-ግብር ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ኩራባቸው ሸዋረጋ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አብዛኛው ዜጋ በለውጡ አካሄድና በለውጥ ኃይሉ ግራ ተጋብቷል ብሏል፡፡
ኢሕአፓ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድንና የአጋሮቻቸውን የለውጥ ጉዞ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ ያ ሁሉ ድጋፍ እንደ ጤዛ ረግፎ ወደ ተቃውሞ ተለውጧል ባይባልም፣ አብዛኛው ዜጋ በለውጡ አካሄድና በለውጥ ኃይሉ ግራ ተጋብቷል ሲል ገልጿል፡፡
የለውጥ ኃይሉ የጀመረውን አበረታች የዴሞክራሲ ምኅዳርን የማስፋት ሂደት አለመቀጠሉን፤ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሕግ የበላይነት ሲደፈር ዝምታን መምረጡን፤ የኢህአዴግ እርስ በእርስ አለመስማማትን፤ የኑሮ ውድነት ከቀን ወደ ቀን መጨመሩን እና ሌሎች ምክንያቶችን በዋቢነት ጠቅሷል፡፡
“ለውጡ የት ገባ?” ብለን ከመነሻው ላነሳነው ጥያቄ፣ ባመዛኙ መልሱ በአክራሪዎች ተጠለፈ፤ የለውጥ ኃይሉም እንደ ታዛቢ ቆሞ የሚያይበት ሁኔታ ደግሞ ጠለፋውን አፋጠነው በማለት ልንመልሰው እንችላለን ብሏል- ኢሕአፓ።
ይሁን እንጂ፣ የለውጡን ሂደት መም ፈልጎ ማግኘትና መልሶ መስመሩ ላይ መመለስ አሁንም ይቻላል ብሎ እንደሚያምን ኢሕአፓ ገለጿል፡፡
ለዚህም እንዲረዳ ፓርቲው የመፍትሄ ሃሳቦችን ያቀረበ ሲሆን፣ የለውጥ ኃይሎችና የለውጡ ተቃዋሚዎች በአንድነት ሊቀጥሉ አይችሉምና የለውጡ ተቃዋሚዎች ሕግ ሲጥሱ በማጋለጥ ሕጋዊ እርምጃ ሊወስደባቸው ይገባል ብሏል፡፡
አክራሪ ብሄርተኞችን እስከ አሁን እንደሚደረገው በመለማመጥ መቀጠል ሳይሆን፣ እንደ ስፈላጊነቱ ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል ሲል ገልጿል።
ኢሕአፓ የሀገራችን የችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን የህወሓትን ሕገ-መንግሥት ነው፤ ሕገ-መንግሥቱን በአስቸኳይ ለሕዝብና ለፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት አብቅቶ፣ በብሄራዊ እርቅ ማዕቀፍ ሕዝባዊ ብያኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ተቀዳሚ ሥራ መሆን ይገባል ሲል ጠቁሟል።
ሕገ-መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ ዞኖች፣ የሕገ-መንግሥቱ መጨረሻ እስኪወሰን ድረስ ጥያቄያቸው በይደር እንዲቆይ ማድረግም ያስፈልጋል ብሏል።
ይህ ካልሆነ፣ በተለይ በደቡብ ክልል እንደተጀመረው ጥያቄው መስተናገድ ከቀጠለ ማቆሚያ ስለማይኖረው፣ የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ፖለቲካዊ ሂደት እንደሚሆን ስጋት እንዳለው ኢሕአፓ ገልጿል፡፡
ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ለአማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በተለይ ደግሞ ለሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ እንደሆኑ የገለጸው ኢሕአፓ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ባልተረጋጋና በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ዕዝ ሥር ባለበት ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ሀገራዊ ኹነቶች ሕዝቡ ግራ በተጋባበት ወቅት፣ ምርጫን በጥድፊያ ማካሄድ ችግሮችን የበለጠ እንዳያባብስና ለአክራሪዎች ይበልጥ አቅም እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ሲል ሀገራዊ ምልከታውን ገልጿል፡፡
ሕገ-መንግሥቱ “በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ይደረግ” ይላል ከሚለው ቀኖና ባሻገር፣ በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ብቻ የተመሠረተ ትንተና አድርጎ ውሳኔ መስጠት ተገቢ ነው ሲል ኢሕአፓ አስታውቋል፡፡
ኢሕአፓ በመጪው ኅዳር ወር ነባር የፓርቲው የአመራር አባላት ኃላፊነታቸውን ለወጣቶች የሚያስረክቡበትና የሚተካኩበት ጉባዔ በአዲስ አበባ ከተማ ለማዘጋጀት በሂደት ላይ መሆኑን አሳውቋል፡፡