ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ. ም
በእሥር ላይ በነበሩ የኢሕአፓ የከፍተኛ አመራር አባላት ላይ ህወሓት የፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) በጥብቅ ያወግዛል!

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሃል አገር ሥልጣን ከመቆጣጠሩ በፊት፤
በቅድሚያ ተቀናቃኜ ነው ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ሠራዊትን ለማጥፋት ከሻቢያና ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር በምዕራብ ጎጃም
በከፈተው የጦርነት ዘመቻ የኢሕአፓ የከፍተኛ አመራር አባላትን እነ ፀጋዬ ገብረመድህን
(አበበ ደብተራው)፤ ይስሃቅ ደብረጽዮን፣ በለጠ አምሃ፣ ስጦታው ሃሰንንና ሌሎችን ማርኮ
ወደ ትግራይ መውሰዱ የሚታወስ ነው። ኢሕአፓ በተለያየ መንገድ የእስረኞቹን ሁኔታ
ለማወቅ በተደጋጋሚ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ዘረኛውና አምባገነኑ የህወሓት ቡድን ሙልጭ
አድርጎ በመካድ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቷል።
አሁን ግን በወቅቱ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራት በቅርቡ
“ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥና ለአሜሪካ
ድምፅ ሬዲዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ፣ እነዚህ የጦር ምርኮኞች ለመደበኛ ፍርድ ቤት
ሳይበቁ፣ በህወሓት አመራር አባላት ውሳኔ መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል። አቶ ገብሩ
ይህን ለእስረኞች ቤተሰቦችና ለእኛ ለትግል ጓዶቻቸው አስጨናቂና አሳዛኝ ሆኖ የኖረውን
ሚስጥር ይፋ በማድረጋቸው ሳናመሰግናቸው አናልፍም።
ህወሓት ሀገራችንን በመሣሪያ ኃይል ከተቆጣጠረና የዓለምዓቀፍ ሕግጋትን ተቀብያለሁ
በማለት መመጻደቅ ከጀመረ በኋላ፣ የጦር ምርኮኛን አያያዝ የሚመለከተውን የጀኔቫ
ኮንቨንሺንን ሕግ በመጣስ፣ በጫካ ውስጥ እንደለመደው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእንበለ
ፍርድ ጓዶቻችን በግፍ በመረሸኑ ከፍተኛ ቁጣና ቁጭት ያደረሰብን መሆኑን እንገልጻለን።

ይህን ፋሽሽታዊ ድርጊት ኢሕአፓ (ዴሞክራሲያዊ) በጥብቅ እያወገዘ፣ በማናለብኝነት
በጓዶቻችን ላይ የግድያ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ የሰጡትን የህወሓት አመራር አባላት
እንደምንፋረዳቸው አበክረን እንገልጻለን።
ህወሓት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ከልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አፍኖ ደብዛቸውን ያጠፋውን
በርካታ የኢሕአፓ አባላት እጣ-ፈንታ አሁንም ምን እንደሆነ በይፋ እንዲያሳውቅ በጥብቅ
እየጠየቅን ህወሓት በድርጅታችን የአመራር አባላት ላይ የወሰደውን አረመኔያዊ ድርጊት
ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም፣ ለሟቾች ቤተሰቦችና ለመላው ጓዶቻቸው ጥናቱን እንዲሰጣቸው እንመኛለን።
የጓዶቻችንን ደም ያፈሰሱትን እንፋረዳለን!

 

P.O.Box 8141 P.O.Box 88675 Silver Spring, MD 20910 Los Angeles, CA 90009

Phone: 202- 241 2078 Email Address: eprp-democratic@eprp-ihapa.com

Leave a Reply