ከሳምንታት በፊት በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ አንድ ፎቶግራፍ ተለቅቆ ነበር፡፡ በፎቶግራፉ ላይ ከ10 የሚበልጡ የሊጥ በርሜሎችና ሊጡ የሚቦካባቸው 3 ሳፋዎች ተደርድረው፣ በአንድ ጥግ በማዳበሪያ ተሞልቶ የተቀመጠ ዱቄትም ይታያል፡፡ ምግብን የመሰለ ነገር በከባድ ጥንቃቄ መዘጋጀት ያለበት ቢሆንም ሊጡ የሚዘጋጅበት ሁኔታ ፈጽሞ ፅዳት የጐደለው መሆኑን ከፎቶግራፉ መታዘብ ይቻላል፡፡ ሊጡ የሚቦካበት ሳፋና በርሜሎች ቆሽሸው ይታያሉ፡፡ ከፎቶው ግርጌ ደግሞ ሊጡ የተዘጋጀው ከሰጋቱራና ከጄሶ ዱቄት ተቀይጦ መሆኑን የሚያሳይ አስደንጋጭ ጽሑፍ ሠፍሯል፡፡

እንደዚህ ያሉ የአንድ ሰሞን ተመሳሳይ ነገሮች በአቃቂ ቃሊቲ፣ በላፍቶ፣ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በሰበታና በልደታ አካባቢዎች ታይተዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት አካባቢ እንጀራ ጋግሮ በማከፋፈል ሥራ የተሰማሩ አምስት ሰዎች 30 በመቶ ጤፍ 70 በመቶውን ደግሞ እንደ ጄሶና ሰጋቱራ ያሉ ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል እንጀራ ጋግረው ሲያከፋፍሉ ተይዘው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በተያዙበት ወቅት በዚሁ መንገድ የተዘጋጀ አራት በርሜል ሊጥና ሦስት ኩንታል ዱቄት ተገኝቶባቸዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማም ጤፍ ላይ ሰጋቱራና ሌሎች ባዕድ ነገሮችን ደባልቀው ለአካባቢው ነዋሪዎችና የንግድ ተቋማት ሲያከፋፍሉ የነበሩ 15 ሰዎች እንዲሁ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ታቦት ማዳበሪያ በመባል በሚታወቀው አካባቢም በተመሳሳይ ተግባር የተሰማሩ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለፖሊስ በደረሰ ጥቆማ ፍተሻ በተካሄደባቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በእንጀራ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ማድቤት ውስጥ ለመጋገር የተዘጋጀ 17 በርሜል ሊጥ፣ ከ20 ኩንታል በላይ ሰጋቱራ፣ ከጀሶ የተዘጋጀ ዱቄት ተገኝቷል፡፡ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ለዚሁ ተግባር የሚውል ጄሶና ሰጋቱራ አዘጋጅተው የሚያከፋፍሉ መኖራቸውን እንደገለጹ በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ተዘግቦም ነበር፡፡

ሁኔታው ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ በተለይም እንጀራ ከውጭ ገዝተው የሚመገቡን ሥጋት ውስጥ ጥሏል፡፡ ጥቂት የማይባሉት እንጀራን ከማዕዳቸው እንዲቀር አድርገዋል፡፡ ‹‹ብንታመምስ›› እያሉም ቢሆን የውጭ እንጀራ የሚገዙ፣ ውጭ የሚመገቡም አሉ፡፡

ዜናው ከተሰማ በኋላ እንደ ቀድሞው ሬስቶራንት ገብቶ ያዘዘውን ምግብ በፍላጎት የሚመገብ ጠፍቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ማዕድ ሲቀርብ ከመመገብ ይልቅ እንጀራው ከምን የተዘጋጀ ይሆን በሚል ንፁህ ስለመሆኑ በመጠራጠር እንጀራውን በደንብ ለማጣጣም መሞከር ውጭ የሚመገቡ ሰዎች ተግባር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

ሕይወት ግርማም ከእነዚህ መካከል ነች፡፡ የ23 ዓመቷ ሕይወት በላጤነት ቤት ተከራይታ የምትኖረው የረር አካባቢ ነው፡፡ ለራሷ የሚሆን ምግብ ማዘጋጀት አይከብዳትም፡፡ አልፎ አልፎ ግን ምሳ ውጭ የምትመገብባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እንደ ፓስታና ማካሮኒ፣ ሩዝ ያሉ ምግቦች አስቤዛ ታደርግለች፡፡ ይሁንና በየቀኑ መመገብ አይሆንላትም፡፡ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ እንጀራ ማግኘት አለባት፡፡ ለእንጀራ ያላትን ፍቅር ስትገልጽም ‹‹በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እንጀራ ማግኘት ካልቻልኩ የበላሁ አይመስለኝም፡፡ ሌላ ምግብ ለመብላትም ፍላጐቱ አይኖረኝም፤›› ትላለች፡፡

ነገር ግን ጤፍ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ የመሸጡን ዜና ከሰማች በኋላ የምትወደውን እንጀራ በጥርጣሬ እንድትመለከት ሆናለች፡፡ እንጀራ ትገዛ የነበረው ከመደብር በመሆኑ፣ ዘወትር የምትመገበው እንጀራ ማን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚያዘጋጀው አለማወቋ ሥጋቷን አባብሶታል፡፡ በእንጀራው ላይ አንዳንድ እንግዳ ነገሮች እንደተመለከተች ይሰማትም ጀምሯል፡፡ ‹‹ያልተለመደ ጠረን አለው፡፡ ብዙ ሳይቆይ በአንድ ቀንም ይሻግታል፡፡ ስበላውም ጨጓራዬን ያመኛል፤›› ትላለች፡፡ ይህ የሕይወት ስሜት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ጎረቤቶቿም ተመሳሳይ ነገር በማየታቸው ሌላ ደንበኛ ቀይረዋል፡፡ እንደ ሕይወት እንጀራ ላለመብላት የወሰኑም አሉ፡፡

በተፈጠረባቸው ሥጋት ሬስቶራንት ገብተው ያዘዙትን ምግብ ለመመገብ የሚቸገሩም አሉ፡፡ ከጓደኞቿ ጋር ምሳ ለመብላት ቦሌ አካባቢ ወደሚገኝ አንዱ ሬስቶራንት ጎራ ያለችው ከቀናት በፊት ነበር፡፡ ምሳ ላይ የሚያዘወትሩትን ምግብ በየዓይነቱ፣ ሽሮና ፓስታ አዘዙ፡፡ ምግቡ እስኪመጣላቸው ድረስ ሲጨዋወቱ ቆዩ፡፡ ተርበው የነበረ ቢሆንም ማዕዱ ሲቀርብ እንዳሰቡት በደንብ መብላት አልቻሉም፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ጓደኛቸው እንጀራው ጄሶ ይኖርበት ይሆን? አለ፡፡ የቀረበላቸውን ምግብ እያዩ እርስ በርስ መተያየት ጀመሩ፡፡ እንደምንም ብለው አንድ ሁለት ለመጉረስ ሞከሩ፡፡ ስሜታቸው በመረበሹ መብላት አልቻሉም የተሰማቸው የተለየ ጣዕም ባይኖርም እየተመገቡ ያሉት እንጀራ ችግር ያለው መሰላቸው፡፡ ይህ በከተማዋ እየተሰማ ያለው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ የማዘጋጀቱ ዜና ከጆሯቸው በመግባቱ የተነሳ የሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል አጋጣሚው ከተጠቃሚዎች ባሻገር በእንጀራ ንግድ ላይ በተሰማሩ ሰዎች ዘንድም ጭንቀት ፈጥሯል፡፡ በነጋዴዎችና በሸማቾች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠርም አድርጓል፡፡ በእንጀራ ንግድ ከተሰማሩ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠሩት አቶ ቸርነት አብይ ወደ ገበያው ሲገቡ የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ነበር፡፡ በቀን 4,200 እንጀራ በመጋገር አንዱን በሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሒሳብ ለሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሥጋ ቤቶችና ሱቆች ያስረክባሉ፡፡

ባደረጉት ጥናት ብዙዎቹ እንጀራ አቅራቢ ድርጅቶች ጤፍን ከማሽላና ከሩዝ ጋር በመቀላቀል እንደሚጋግሩ ይህም የተለመደና ጤናማ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ እሳቸው የሚያቀርቡት እንጀራ የተሻለ ሆኖ ገበያውን ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ለገበያ የሚያቀርቡት እንጀራ ደረጃውን የጠበቀ ከጤፍ ብቻ የተዘጋጀ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በምርታቸውም ይተማመናሉ፡፡ ነገር ግን የተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ውጥረት ፈጥሮባቸዋል፡፡ የገበያ እንጀራ ላይ ባለው ከፍተኛ ጥርጣሬ ምክንያት ገበያቸው እንዳይጎዳ ሠግተዋል፡፡ ምንም እንኳን እንጀራቸው ከንፁህ ጤፍ የሚጋገር ቢሆንም የጤፉ ዓይነት በተለዋወጠ ቁጥር የእንጀራው መልክ እንዳይቀያየር ገበያ እንዳያሸሽባቸው ሥጋት ያድርባቸዋል፡፡ በዝግጅት ሒደቱ ውስጥ ምንም ዓይነት እንከን እንዳይፈጠር ከወትሮው በተለየ ትኩረት እንዲሠሩ እንዳስገደዳቸውም ይናገራሉ፡፡

‹‹አጋጣሚው ኃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ ገበያችንም ከፍ እንዲል፣ ማኅበረሰቡም ገዝቶ ለሚመገበው ምግብ እንዲጨነቅ አድርጐታል፤›› የሚሉት በአስቱ እንጀራ ምክትል ሥራ አስኪያጅና ቴክኒካል ባለሙያው አቶ ታመነ አበራ ናቸው፡፡ ሁኔታው በፈጠረው ሥጋት ክፉና ደግ የተነጋገሩ ነጋዴዎችና ደንበኞችም ያጋጥማሉ፡፡ እንጀራውን ቀጥታ ለተጠቃሚው የሚያደርሱ ከደንበኞቻቸው የሱፐር ማርኬት ባለቤቶችና ባለሱቆች ጋር እየተጋጩ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ጄሶ የሌለው አንድ እንጀራ ስጠኝ›› ብሎ ከሻጩ ጋር የተጋጨም አለ፡፡

ሰሞንኛ ገጠመኝ ከሆነው እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር ከመቀላቀል ባለፈ በርበሬን፣ ዘይትን፣ ቅቤን ቡናን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ የመሸጥ ተግባር እንዳለ በተለያየ አጋጣሚ ታይቷል፡፡ ተመሳሳይ ነገሮችን ከገበያ ለመሸመት ለረጅም ጊዜ የሚያውቁት ደንበኛ ከሌለ በስተቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ ምን እንዳይሆን ብለው በእምነት ከአንዱ ነጋዴ የገዙት ቅቤ ከሞራ፣ ከሙዝና ከቫዝሊን ጋር የተቀየጠ ሆኖ ያገኙ ጥቂት አይደሉም፡፡ ዘይት በርበሬ ላይም የታየው ተመሳሳይ ነገር ነበር፡፡ ይህ ኢሰብዓዊ ድረጊት በእምነት የሚደረግን ግብይት ጥያቄ ውስጥ የሚከት የክህደት ተግባር በመሆኑ ብዙዎች አስቆጥቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በተገኘ መረጃ መሠረት በከተማዋ 2,721 በዳቦ፣ ኬክ ብስኩትና እንጀራ ምርት የተሰማሩ፣ 178 የምግብ ዘይት የሚያመርቱ፣ 125 በእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማምረት ላይ የተሰማሩ አሉ፡፡ ወደ 500 የሚሆኑ በባልትና ውጤቶችና በመሳሰሉት የተሰማሩ ነጋዴዎችና ድርጅቶችም ይገኛሉ፡፡ በሕገወጥ ንግድ የተሰማሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በአቋራጭ ለመክበር ሲሉ በሚያዘጋጁት ምግብ ላይ ባዕድ ነገር እየቀየጡ ለገበያ ሲያቀርቡ ይታያል፡፡

የምግብነት ይዘት የሌለውን ባዕድ ነገር ከምግብ ጋር መቀላቀል በኩላሊት፣ በጉበት፣ በጨጓራ፣ በምግብ ቱቦ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ከማድረሱም ባለፈ በውስጡ የሚኖረው የኬሚካል ይዘት ለካንሰር በሽታ አስተዋጽኦ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት በፉድ ኤንድ ኒውትሪሽን ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ዶ/ር አብነት ተክሌ ናቸው፡፡ ምግብነት የሌለው ነገር ከምግብ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ሰውነት በሚገባበት ጊዜ በሦስት ዓይነት መንገዶች ጉዳቶችን ያደርሳል፡፡ የመጀመሪያው አላስፈላጊ ኬሚካል ወደ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ የሚፈጠረው የጤና ቀውስ ነው፡፡ ሁለተኛው በዓይን የማይታይ ተህዋሲያን በውስጡ ሲኖር አልያም ከተህዋሲያኑ በሚመነጭ መርዛማ ንጥረ ነገር የሚፈጠረው ነው፡፡ ሌላው ተደባልቀው ወደ ሰውነት በሚገቡበት ጊዜ የሚደርሰው አካላዊ አደጋ ነው፡፡

‹‹ማንኛውም ኬሚካል ወደ ሰውነታችን ሲገባ በጉበት መጣራት ይኖርበታል፡፡ ጉበት በሰውነታችን ያልተለመዱ ኬሚካሎችን ለማጣራት በሚያደርገው ሒደትም ይጐዳል፡፡ ጨጓራም እንደዚሁ፤›› የሚሉት ዶ/ር አብነት ባዕድ ነገር ወደ ሰውነት ውስጥ በሚገባበት ወቅት በማንኛውም ዓይነት መንገድ የጤና ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ከሚታዩት ችግሮች ባሻገር ከጊዜ በኋላ የሚከሰቱ መኖራቸውን፤ ባዕድ ነገርን ከምግብ ጋር ቀላቅሎ ለገበያ የማቅረቡን ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችም ይህንን ተገን በማድረግ በድፍረት እየሠሩበት እንደሚገኙ ይጠቁማሉ፡፡

የሸማቹን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር መፈጸም ወንጀል ነው፡፡ በዚህ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ በአንድ ዓመት ነግደው ካገኙት ገቢ ላይ 10 በመቶውን እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ እንደ ጥፋታቸው ክብደትና ቅለትም ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ይፈረድባቸዋል፡፡ ‹‹በቅቤ፣ በወተት፣ በማር፣ በእንጀራና በሌሎችም ለምግብነት በሚውሉ ነገሮች ላይ ባዕድ ነገር በመቀየጥ ተግባር ወደኛ የሚመጡ ኬዞች ብዙ ናቸው፤›› ያሉት በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ የተቋቋመ ቢሆንም የቁጥጥር ሥራ አይሠራም፡፡ ነገር ግን ከሸማቹ በኩል ጥቆማ ሲደርሰው በፍጥነት በመድረስ በምርቱ ላይ የላቦራቶሪ ምርመራ በማስደረግ ለጤና አደገኛ የሆኑ ነገሮች መኖራቸው ሲረጋገጥ ድርጊቱን በፈጸመው ድርጅት አልያም ነጋዴ ላይ ክስ በመመሥረት የሸማቹን መብት ያስከብራል፡፡

በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አዋጅና ደንብ መሠረት የምግብ መልክን ለማሳመርና ክብደትን ለመጨመር ሲባል ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ በሕግ የተከለከለ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአቃቂ ክፍለ ከተማ ጤፍን ከሰጋቱራ ጋር አቀላቅሎ ለገበያ የማቅረቡ ሁኔታ በስፋት ታይቶ ነበር፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማም እንደዚሁ ከሸክላ ጋር የተቀየጠ 20 ኩንታል በርበሬ እንዲወገድ፣ ድርጊቱን የፈጸሙም ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጉን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

በተግባሩ የተሰማሩት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው በቤታቸው ውስጥ ተደብቀው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከፈቃድ ጋር በተያያዘም ውስብስብ ነገሮች ታይተዋል፡፡ በተለይ በየካ ክፍለ ከተማ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸውና ጉዳዩ ከሚመለከተው የመንግሥታዊ አካል የብቃት ማረጋገጫ ሳያገኙ ለ12 ምጣዶች የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ኃይል ተገጥሞላቸው ሲሠሩ የቆዩ፣ በተመሳሳይ የወንጀል ተግባር የተሰማሩን በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል፡፡

ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ፈቃድ ሳያገኙ ለተጠቀሱት ምጣዶች የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ኃይል እንዴት ሊያገኙ ቻሉ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጌታቸው ወረቴ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲመልሱ ‹‹እኛም እንቆቅልሽ የሆነብንና ስንጠይቅም የነበረው ይህንኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡