Wednesday, 14 September 2016 14:41
 –    ኢትዮጵያንም ያሰጋታል፣

 ሀገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ በጫት ምርት ላይ እገዳ እየጣሉ ሲሆን ሶማሊያም ከሰሞኑ ከኬኒያ በሚገባውን የጫት ምርት ላይ እገዳ በመጣል እንግሊዝን ኡጋንዳንና ሌሎች  ሀገራትን ተቀላቅላለች። ክልከላውን ይፋ ያደረጉት የሶማሊያ አቬሽን ሚኒስትር አሊ አህመድ ጃንጊ ናቸው። በርካታ ኬኒያዊያን ነጋዴዎች ወደ ሶማሊያ በሚላከው የጫት ኤክስፖርት ገቢ ህይወታቸውን የሚመሩ ሲሆን ይህ ድንገተኛ እገዳ ግን በተለይ በጫት አምራች ገበሬዎቹና ነጋዴዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስን አስከትሏል።

የሶማሊያ መንግስት የጫት እገዳውን ለምን እንዳደረገ ግልፅ የሆነ መረጃ ሳይሰጥ ቢቆይም ቢቢሲ ዘግየት ብሎ በለቀቀው መረጃ እንዳመለከተው ከሆነ መንግሥት በጫት ላይ እገዳ እንዲጣል የወሰነው ወንጀልን ያበረታታል በሚል ነው።

በዚህ እገዳ የኬኒያ ነጋዴዎችና ገበሬዎች በአንድ ቀን ብቻ እስከ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ የኬኒያ ሽልግ ያጡ መሆኑ ታውቋል። በመካከለኛው የኬኒያ ክፍል የሚገኙት የሀገሪቱ ገበሬዎች ኑሯቸውን የሚገፉት በጫት ምርት ግብይት ሲሆን በተለይ የሶማሊያዊያን የጫት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ በርካቶች የሰብል እርሻዎቻቸውን ወደ ጫት ማሳነት እንዲቀይሩ አድርጓቸዋል። የጫት ምርቱና ግብይቱ በየቀኑ ያለማቋረጥ የሚካሄድ ሲሆን የሶማሊያ መንግስት በአንድ ጊዜ እገዳውን ማስታወቁን ተከትሎ በርካታ የጫት ምርት ብክነት የደረሰ መሆኑ ታውቋል።

ሀገራት ቀስ በቀስ ጫትን ወደ መከልከሉ እያመሩ ሲሆን እንግሊዝ እ.ኤ.አ በ2014 እገዳ መጣሏን ማስታወቋ ይታወሷል። ኡጋንዳም ተመሳሳይ እርመጃ ውስዳለች። ሶማሊያ በምስራቅ አፍሪካ ጫትን አስገብቶ በመጠቀሙ ረገድ ከፍተኛውን ቦታ ይዛ የቆየች ሲሆን አሁን የተጣለው እገዳ ግን ለበርካታ ኬኒያዊያን ያልተጠበቀ ዱብ እዳ ሆኗል። ከኬኒያ በተጨማሪ ወደ ሶማሊያ ጫት የምትልከው ሀገር ኢትዮጵያ ናት።  እገዳው በሶማሊያ ባለስልጣናት በኩል እንደተገለፀው ከሆነ የጫት ምርት በዜጎች ማህበራዊ ህይወት ተፅዕኖ በማድረሱ የኢምፖርት እገዳው የተጣለ ከሆነ ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ የምትልከውን የጫት ምርት ጭምር የሚመለከት ይሆናል።

 ኢትዮጵያ በ2008 በጀት ዓመት 49 ሺህ 708 ቶን ጫት ኤክስፖርት በማድረግ 292 ሚሊዮን 997 ሺህ ዶላር ያገኘች መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቶች መዳረሻ ከሆኑት ሀገራት መካከል ከቻይና በመቀጠል ሶማሊያ በሁለተኛ ደረጃ ትገኛለች።

እንደ ንግድ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ በ2008 በጀት ዓመት 346 ነጥብ 14 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርት መዳረሻ በመሆን ቻይና የመጀመሪያውን ድርሻ ስትይዝ ሶማሊያ በአንፃሩ 306 ነጥብ 91 ሚሊዮን ዶላር ምርትን በመቀበል የሁለተኝነት ደረጃን ይዛለች።

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የምትቀበለው የጫት ምርት ከፍተኛ በመሆኑ አጠቃላይ በጫት ምርት ላይ እገዳን የምትጥል ከሆነ በኬኒያ የሚደረሰው ጉዳት ኢትዮጵያንም ጭምር የሚነካ ይሆናል።

በግብርና ምርት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ገቢ የኤክስፖርት ስብጥሩን ወደ ኢንዱስትሪው እያሰፋ እንዲሄድ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል ስኬት ሊመዘገብበት አልቻለም። ሀገራት በጫት ምርት ላይ እገዳ እየጣሉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የምርቱ የውጭ ገበያ አስተማማኝነት አደጋ ላይ እየወደቀ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የአለም የቡና ዋጋም እየወረደ መሄዱ የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ገቢ እንዲወርድ አድርጎታል። እነዚህ ሁኔታዎች በቀጣይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚል ሥጋትን አስከትሏል።

ስንደቅ

Leave a Reply