Wednesday, 31 December 2014 12:13

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ሪፖርት (2014)

 

ከሳዑዲ ተመላሾች ህዳር (2006)

ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ኤምባሲ በኦፊሻል ድረገጹ በነገው ዕለት በሚጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት (2014)፤ በኢትዮጵያ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ችግሮችን የዳሰሰና መፍትሔውን የጠቆመ ዓለም አቀፍ ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል። ይህ ሪፖርት የችግሩን ስፋት ለማሳየት ይረዳል በሚል ሙሉውን አቅርበነዋል። መልካም ንባብ።

………………………………….

ኢትዮጵያ ለግዳጅ ሥራ እና ለወሲብ ንግድ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የተዳረጉ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት መነሻ፤ በተወሰነ ደረጃም መዳረሻ አገር ናት። ከኢትዮጵያ የገጠር አካባቢዎች የሚወጡ ወጣት ሴቶች፤ በአገሪቱ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት እና፣ አልፎ አልፎም፣ በሴተኛ አዳሪነት ይበዘበዛሉ፤ ወጣት ወንዶች ደግሞ በባህላዊ ሽመና፣ በእረኝነት፣ እና በጎዳና ላይ ንግድ በግዳጅ እንዲሰሩ ይደረጋሉ። አዲስ አበባ የሚገኘው ዋና የገበያ ማዕከል ከአፍሪካ ቀዳሚው የወሲብ ንግድ ቤቶች መገኛ ሲሆን ዕድሜያቸው እስከ 8 ዓመት የሚሆኑ ልጃገረዶች በነዚህ ቤቶች በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ከኢትዮጵያ ውጪም በተለይ ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን እና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት እና በሴተኛ አዳሪነት እንዲሰሩ ይገደዳሉ፤ ኢትዮጵያውያን ወጣት ወንዶች ደግሞ ጂቡቲ ውስጥ በሱቅ ሰራተኝነት፣ በተላላኪነት፣ በቤት ሰራተኝነት፣ በስርቆት እና በጎዳና ላይ ልመና ለግዳጅ ሥራ ይዳረጋሉ።

በርካታ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲሰደዱ ጂቡቲ፣ ግብጽ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ወይም የመንን እንደመሸጋገሪያ ይጠቀማሉ። ከነዚህ አንዳንዶቹ ሊሄዱ ካሰቡበት አገር ሳይደርሱ እንደመሸጋገሪያነት ባረፉበት አገር ተይዘው ለብዝበዛ፣ ለእስራት፣ ለግዳጅ ስራ እና ለመታገት ይዳረጋሉ። ወጣት ሴቶች በመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች፣ በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ለቤት ሠራተኝነት ይዳረጋሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች አካላዊ እና ወሲባዊ ጥቃት፣ ደሞዝ ክልከላ፣ እንቅልፍ መነፈግ፣ የፓስፖርት መያዝ፣ በቤት ውስጥ መታገት እና ግድያን ጨምሮ አስከፊ ጥቃቶች ይደርሱባቸዋል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስራ ፍለጋ ከአገር ከወጡ በኋላ፣ በወሲብ ንግድ ቤቶች፣ በማዕድን ማውጫ ቦታዎች፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ነዳጅ ዘይት ማውጫ አካባቢዎች ለወሲብ ንግድ ብዝበዛ ይዳረጋሉ፤ ይኸው ሁኔታ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጥቃት ከሚያደርሱባቸው አሠሪዎቻቸው ጠፍተው ካመለጡ በኋላም ያጋጥማቸዋል። የዳበረ የሙያ ክህሎት ሳይኖራቸው ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የባህረ-ሰላጤው አገሮች እና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወንዶች አንዳንዶቹ በእነዚህ አገራት ለግዳጅ የጉልበት ሥራ ይዳረጋሉ። የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ. ከጥቅምት 2013 ጀምሮ በውጭ አገር የስራ ቅጥር ላይ ክልከላ አድርጓል። ከክልከላው አስቀድሞ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀን እስከ 1500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውን በሕጋዊ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ገልጾ ሪፖርት አድርጎ ነበር። ይህ ቁጥር ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ30 እስከ 40 በመቶ ብቻ የሚወክል ሊሆን እንደሚችል ሲገመት፤ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች በሕገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወይንም ስደት ይዳረጋሉ። በገጠራማ አከባቢዎች ዋነኞቹ ቀጣሪዎች ደላሎች ናቸው። ከ400 የሚበልጡ ኤጀንሲዎች ሰራተኞችን ወደ ውጭ አገራት የመላክ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነበር፤ ሆኖም መንግስት ከነዚህ ኤጀንሲዎች አብዛኞቹ ሕጋዊ እና ሕገወጥ የቅጥር ሂደቶችን እንደሚከተሉ በመገንዘቡ ለውጭ አገር በሚደረግ የስራ ቅጥር ላይ ክልከላ ጥሏል። ክልከላውን ተከትሎ በሱዳን በኩል የሚደረግ ሕገወጥ የሰራተኞች ፍልሰት እንደጨመረ ይታመናል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋሙ የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ከሚኖሩ ኤርትራውያን መካከል አንዳንዶቹ በፈቃደኝነት ከካምፕ ሲወጡ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከካምፕ ተጠልፈው ከተወሰዱ በኋላ በግብጽ የሲናይ በረሃ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተዳርገዋል።

እ.ኤ.አ. ከሕዳር 2013 ጀምሮ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከ163ሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ያስወጣ ሲሆን ከነዚህም መካከል ከ94ሺ የሚበልጡት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ወንዶች፤ ከ8ሺ የሚልቁት ደግሞ በእረኝነት እና በቤት ሰራተኝነት የተቀጠሩ ሕጻናት ናቸው። ዓለምአቀፍ ተቋማት እና የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች እንደሆኑ ያምናሉ። በርካታ ስደተኞች ወደሳዑዲ ዓረቢያ ላደረሷቸው አዘዋዋሪዎች ክፍያ ያልፈጸሙ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በአንዳንዶቹ ላይ በድጋሚ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የመሆን አደጋን አስከትሎባቸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስወገድ የተቀመጡትን ዝቅተኛ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ባያሟላም፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 106 ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የፈጸሙ ወንጀለኞች ሕግ ፊት ቀርበው እንዲቀጡ ያደረገ ሲሆን፤ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበርም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች መጠለያ እና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አድርጓል። በ2013 የሕገወጥ የሰዎች ዘውውር ሰለባ ዎችን ወደሀገር መመለስ ተከትሎ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የውጭ አገር ስራ ቅጥር ኤጀንሲዎች ላይ ሲያከናውን የቆየው የቁጥጥር ስራ ችግር እንዳለበት፤ እነዚህ ኤጀንሲዎችም ወደ ውጭ አገራት የላኳቸውን ሰራተኞች ደህንነት ማስጠበቅ እንዳልቻሉ ተረድቷል። በምላሹም መንግስት በጊዜያዊነት ለውጭ አገራት የሚደረግ የቅጥር ስራን አስቁሞ ለዚሁ አግባብነት ያለውን የስራ ቅጥር አዋጅ የቅጥር ኤጀንሲዎችን ይበልጥ መቆጣጠር እና በውጭ አገራት የተቀጠሩ ሰራተኞችን ደህንነት በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ መከለስ ጀምሮ ነበር። በዓመቱ ውስጥ መንግስት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑትን ጨምሮ ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ከሌሎችም አገራት የተባረሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማመቻቸት ስራ ሰርቷል። በዚህ ሂደትም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ከስደት ተመላሾች የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አድርጓል። መንግስት ለነዚህ ድርጅቶች የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ያላደረገ ሲሆን፤ ለአገር ውስጥ እና ለድንበር ተሻጋሪ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች ቀጥተኛ ድጋፍ ማድረግ ለነዚሁ ድርጅቶች የተተወ ነበር። መንግስት ውጭ አገር በሚገኙ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች የሰራተኛ ጉዳዮችን የሚመለከቱ አታሼዎችን አልመደበም፤በኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽ/ቤቶች በሚሰጡ የዜጎች ደህንነት አገልግሎቶች ላይም ማሻሻያ አላደረገም። በ2013 በመንግስት የተዘጋጁ ስልጠናዎች አለመኖራቸው ዋነኛ ችግር ነበር። በተጨማሪም መንግስት የሕጻናት የወሲብ ንግድን እና ሌሎች በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን በሕግ ማስከበር፣ ከለላ በመስጠት እና በመከላከል በኩል በቂ ሥራ አልተሰራም።

በኢትዮጵያ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የሚረዱ

የመፍትሄ ሐሳቦች

ሕገወጥ ቅጥር ፈጻሚዎችን መቅጣት በሚቻልበት መልኩ የስራ ቅጥር አዋጁን ማሻሻል እንዲሁም በውጭ አገር ስራ የሚያስቀጥሩ ኤጀንሲዎች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ማጥበቅ፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ለተዘረዘሩ ለወሲብ ንግድና ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች የተቀመጡትን ቅጣቶች ማክበድ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 597 እና 635ን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ግልፅ ትርጉም ባካተተና ወንድ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ራሱን በቻለ አንቀጽ በሕጉ እንዲሸፈኑ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻል፣ እንዲሁም ቅጣቶችን በሌሎች ከባድ ወንጀሎች ላይ ከሚጣሉ ቅጣቶች ጋር እንዲጣጣሙ በሚያደርግ መልኩ ማሻሻል፤ በመላ አገሪቱ ያሉ የዳኝነት አካላት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ፣የፖሊስን የወንጀል ምርመራ አቅም ማጎልበት በአገር ውስጥ የሚፈፀመውን ህገወጥ የሕጻናት ዝውውር ወንጀል ፈጻሚዎችን ሕግ ፊት ለማቅረብ እንዲቻል ይረዳል። በጉልበት ብዝበዛ እና በወሲብ ንግድ ዓላማ የሚካሄዱ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን ለመቅጣት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን አንቀጾች 596፣ 597 እና 635 ይበልጥ በተግባር ላይ ማዋል፣ ብሔራዊ መታወቂያዎች እና ፓስፖርቶች በሚሰጡበት ወቅት የሚከናወነውን የማጣራት ስራን በማሻሻል ሕጻናት አጭበርብረው እነዚህን ሰነዶች አንዳላገኙ ማረጋገጥ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የሠራተኞች ጉዳይ አታሼዎችን መመደብ እንዲቻል አስፈላጊውን በጀት መያዝ፤ በውጭ አገራት ለሚሾሙ ዲፕሎማቶች እና የሥራ ቅጥር ውሎችን ሕጋዊነት ለሚያረጋግጡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ የሥራ ኃላፊዎች ስለ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤ የሚያስጨብጡ መደበኛ ሥልጠናዎች በመስጠት በውጭ አገራት ተቀጥረው ለመስራት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ከለላ መስጠት፤ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሌሎች አገራት ለሚጓዙ ስደተኛ ሠራተኞች በሚሰጠው የቅድመ ጉዞ ስልጠና ውስጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና የሰራተኛ መብትን የሚመለከት መረጃ ማካተት፤ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት መንግስታት ለኢትዮጵያውያን ሰራተኞች የሚያደርጉትን ጥበቃ እንዲያሻሽሉ ጥረት ማድረግ፤ በመንግሥትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚተዳደሩ የሰለባዎች መጠለያዎች ያልተቋረጠ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በጀት መመደብን ጨምሮ ከስደት ለሚመለሱ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ደረጃ ለማሳደግ ከአገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ መሥራት፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የተቋቋመውን ብሔራዊ ግብረ ኃይል ውጤታማነት ማሻሻል፣ እንዲሁም በክልል ደረጃ በአገር ውስጥ ስለሚፈፀሙ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎች ግንዛቤ ማሳደግን ዓላማ ያደረገ ዘመቻ ማካሄድ።

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር

ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች

ሪፖርቱ በሚሸፍነው ወቅት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠር ያወጣውን ሕግ በስራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረጉን እንደቀጠለ ነበር። ሆኖም ይህ ጥረት ሙሉ በሙሉ ያተኮረው በድንበር ተሻጋሪ የሰዎች ዝውውር ላይ ሲሆን፤ ለወሲብ ንግድ ዓላማ ወይም በአገር ውስጥ የሚደረጉ ለግዳጅ ስራ የታለሙ ሕገወጥ ዝውውሮች ላይ መንግስት ምርመራ ማድረጉን ወይም ክስ መመስረቱን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ጥቂት ናቸው። የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 596 (ለባርነት መዳረግ)፣ አንቀፅ 597 (ሕገወጥ የሴቶች እና የሕጻናት ዝውውር)፣ አንቀጽ 635 (የሴቶች እና የሕፃናት ዝውውር) እንዲሁም አንቀጽ 636 (የወንጀል ማክበጃ ሁኔታዎች) ለወሲብ ንግድ ዓላማ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መፈጸም የተከለከለ ተግባር እንደሆነ ይደነግጋል። ለወሲብ ንግድ የሰዎች ዝውውር መፈጸምን የሚከለክለው አንቀጽ 635 ከአምስት ዓመት ያልበለጠ የእሥር ቅጣት ይጥላል፤ ይህ በራሱ ከባድ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ አስገድዶ መድፈርን ለመሳሰሉ ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ከተቀመጡ ቅጣቶች ጋር ሲነፃፀር ግን አነስተኛ ነው። አንቀጽ 596 እና 597 ባርያ አሳዳሪነት እና የጉልበት ብዝበዛ ዓላማ ያለው የሰዎች ዝውውር ሕገወጥ ተግባራት እንደሆኑ የሚደነግጉ ሲሆን፤ ለነዚህም ከአምስት እስከ ሃያ ዓመታት የሚደርስ እና ከባድ የእስር ቅጣት ይጥላሉ። ነገር ግን አንቀጽ 597 እና 635 ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የጠራ ትርጉም ካለመስጠታቸውም ሌላ፤ በአዋቂ ወንዶች ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች ቅጣትን አያካትትም። በመሆኑም ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር የሚያያዙ ጥፋቶችን ተከትሎ ክስ ለመመስረት እምብዛም ጥቅም ላይ አይውሉም። ከዚህ ይልቅ፣ በጉልበት ብዝበዛ ዓላማ የሚፈፀሙ ድንበር ተሻጋሪ የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለመዳኘት አዘውትረው ጥቅም ላይ የሚውሉት አንቀጽ 598 (ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ አገር ስለ መላክ) እና አንቀፅ 571 (የሌላ ሰውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል) ናቸው። ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ግልጽ ሕጋዊ ትርጓሜ ባለመኖሩ ምክንያት ፌደራል ፖሊስ እና ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የመመርመር እና ለፍርድ የማቅረብ አቅማቸው ተገድቧል። ባለስልጣናት የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 632/2009 ላይ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችሉ ረቂቆችን ማዘጋጀት ጀምረዋል። አዋጁ ወደ 400 የሚጠጉ ፈቃድ የተሰጣቸው የስራ ቀጣሪ ኤጀንሲዎች አሰራር የሚመራበት ነው። የታቀዱት ማሻሻያዎች ሕገወጥ ቅጥርን ከመከልከል በተጨማሪ በኤጀንሲዎች ላይ የሚደረግ ቁጥጥርን ለማሻሻል ይረዳሉ።

በፌደራል ፖሊስ የተደራጀ ወንጀል ምርመራ ዩኒት ስር ያለው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መቆጣጠሪያ ክፍል ሪፖርቱ በሚሸፍነው የጊዜ ገደብ ውስጥ በ135 መዝገቦች ላይ ምርመራ አድርጓል። በቀደመው ዓመት ይህ አኃዝ 133 ነበር። የፌዴራሉ መንግስት ከድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ ብዛታቸው በውል ባልታወቀ ግለሰቦች ላይ በአንቀጽ 598 መሰረት በ137 መዝገቦች ክስ እንደመሰረተ ሪፖርት አድርጓል። ከነዚህም መካከል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ106 ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል። በቀደመው ዓመት ይህ አኃዝ 100 ነበር። የመንግስት ባለስልጣናት እነዚህ ክሶች የተመሰረቱት በግል የስራ ቅጥር አጀንሲዎች እና ደላላዎች ላይ መሆኑን ሲጠቁሙ በክሶቹ ላይ ዝርዝር መረጃም ሆነ በአጥፊዎቹ ላይ በአማካይ ምን ያህል ቅጣት እንደተጣለ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። እ.ኤ.አ. ከሰኔ እስከ ሐምሌ 2013 ባለው ጊዜ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሕገወጥ አዘዋዋሪዎችንና ደላሎችን ያካተቱ 267 ጉዳዮችን እንደተመለከቱ ሪፖርት ተደርጓል። በተጨማሪም በ2013 በደቡብ ክልል የጋሞ ጎፋ ዞን ፍርድ ቤት በአካባቢው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ6 ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ቅጣት አስተላልፏል። በአዲስ አበባ የሚገኙ የበርካታ ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች ሰራተኞች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ተባባሪ ነበሩ በሚል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምርመራ አድርጎ ከነዚህ ሰራተኞች በርካቶቹን በቁጥጥር ስር አውሏል።

በ2013 ሕጻናትን ለወሲብ ንግድ ማሰማራትን ጨምሮ ለወሲብ ንግድ ዓለማ የተደረጉ ሕገወጥ ዝውውሮችን በተመለከተ መንግሥት ምንም ዓይነት ክስ አልመሰረተም። በአገር ውስጥ የሚፈጸሙ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀሎችን በመመርመርና ለሕግ በማቅረብ ወይም ክልላዊ መንግስታት ይህን እንዲያደርጉ በማብቃት በኩል መንግሥት በቂ ጥረት አላደረገም። በመላ አገሪቱ የሚገኙ የክልል ሕግ ማስከበር አካላት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር በማሻገር መካከል ያለውን ልዩነት ያለመረዳት ችግር ማሳየታቸው እንደቀጠለ ሲሆን፤ ጉዳዮችን በአግባቡ የመመርመር ብሎም ተያያዥ መረጃዎችን የመሰብሰብ እና የማደራጀት አቅም ውሱንነትም ነበረባቸው። በተጨማሪም መንግሥት ምርመራዎችን በዓለምአቀፍ ደረጃ በማካሄድ በኩል ውሱንነት ነበረበት። በዓመቱ ውስጥ መንግሥት ለሕግ አስከባሪዎች በተለይ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወይም ለስልጠናው የሚውል ገንዘብ አልሰጠም፤ ሆኖም የፖሊስ አባላት እና ሌሎች ኃላፊዎች በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተሰጡ ስልጠናዎችን ተከታትለዋል። 77 ዳኞችም እንዲሁ ሕጻናትን ለስራ በማሰማራትና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ባተኮረ ስልጠና ተሳትፈዋል። መንግሥት ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ፈፃሚዎች ጋር ተባብረዋል በተባሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ምርመራ ማደረጉን፣ ክስ መመስረቱንም ሆነ ማስቀጣቱን በሚመለከት ምንም ሪፖርት አላቀረበም። ለምሳሌ በወረዳ እና ቀበሌ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች ጉቦ በመቀበል በመታወቂያ ካርዶች ላይ የዕድሜ ለውጥ እንደሚያደርጉ፤ ፓስፖርት የሚሰጡ መስሪያ ቤቶች ደግሞ የመታወቂያውን ትክክለኛነትም ሆነ የአመልካቾቹን ዕድሜ ስለማያጣሩ ሕጻናት ያለወላጆች ስምምነት ፓስፖርት እንደሚያወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ለህገወጥ ዝውውር ሰለባዎች የተሰጠ ከለላ

በሪፖርት ዓመቱ መንግሥት በአገር ውስጥም ሆነ ባህር ማዶ ለተሻገሩ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባዎች በቂ እገዛ አላደረገም። በዚህ ረገድ መንግሥት ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ለህገወጥ ዝውውር ሰለባዎች የሚያስፈልገውን አገልግሎት ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የሰጠ ሲሆን፤ ለነዚህ ድርጅቶች ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ አላደረገም። ነገር ግን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሰራተኞችን ከአገሩ ማስወጣቱን ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከ163,000 የሚበልጡ ስደተኞችን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ከየመን ወደ አገራቸው የመመለስ ስራ ሰርተዋል። መንግሥት በዓመቱ ውስጥ ድጋፍ ያደረገላቸውን ሰለባዎች ብዛት ሪፖርት አላደረገም። ከስደት ተመላሾችን የሚቀበሉ ሰራተኞች የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎቸን በመለየት ወደ ክብካቤ ማዕከል ለመላክ የሚያስችል ወጥ የአሰራር መመሪያ አልነበራቸውም። ሪፖርቱ በሚሸፍነው ጊዜ በውጭ አገራት ብዝበዛ የተፈጸመባቸው ኢትዮጵያውያንን መመለስ ተከትሎ የቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፊያ እና የአዲስ አባባ የኢሚግሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ቁጥራቸው ያልታወቀ ሴት የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎችን ለእንዲህ ዓይነት ሰለባዎች የተለየ ክብካቤ ወደሚያደርጉ አስራ አንድ አገርበቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ልከዋል። ይህም የተከናወነው ራሳቸው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ እንደሆኑ በተናገሩ ግለሰቦች ጠያቂነት ነው። አንድ ድርጅት ያለምንም የመንግስት ድጋፍ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የመን እና ሊባኖስ ለተመለሱ 70 የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ፣ ሕክምና እና የስነልቦና ክትትል አድርጓል። መንግሥት ለአብዛኛዎቹ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች ድጋፍ ማድረግን በሚመለከት ኃላፊነቱን በከፍተኛ ደረጃ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ቢሰጥም፣ ለነዚህም ድርጅቶች ምንም ዓይነት የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ ባለማድረጉ የህገወጥ ዝውውር ሰለባዎች በቂ ክብካቤ ማግኘት አልቻሉም። አብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚመሩ የድጋፍ ተቋማት ደግሞ ፕሮጀክትን መሠረት ባደረገ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው በዘላቂነት አገልግሎት ሊሰጡ አይችሉም። ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ክብካቤ የማድረግን ጉዳይ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ትከሻ ላይ የጣለው መንግስት እ.ኤ.አ. በ2009 ባወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ አማካኘነት በነዚሁ ድርጅቶች ላይ ችግር ፈጥሯል። አዋጁ ከገቢያቸው ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ ምንጮች የሚያገኙ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በሰብዓዊ መብት፣ በሕጻናት መብቶች፣ በአካል ጉዳተኞች መብቶች እና በፍትህ ላይ እንዳይሰማሩ ይከለክላል። እነዚህ ክልከላዎች አንዳንድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች በአዘዋዋሪዎቻቸው ላይ ክስ እንዲመሰርቱ እና ቤተሰቦቻቸውን ፈልገው እንዲያገኙ ማገዝን የመሳሰሉ የተሟላ የከለላ አገልግሎት እንዳይሰጡ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥረውባቸዋል።

መንግሥት በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች እና በስድስት ታላላቅ ከተሞች (ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሶዶ፣ አርባ ምንጭ፣ ደብረዘይት እና ጅማ) ለሕጻናት ከለላ የሚሰጡ ማዕከላት አቋቁሟል። በነዚህ ማዕከላት የሚያገለግሉ ሰራተኞች ሕገወጥ የሕጻናት ዘውውርን ጨምሮ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሕጻናት ክብካቤ በማድረግ የሰለጠኑ ናቸው። እንደ ሌሎች ጥቃቶች ሰለባዎች ሁሉ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች በመንግሥት ከሚተዳደሩ ሆስፒታሎች የጤና ክብካቤ እና ሌሎች ማሕበራዊ አገልግሎቶችን በተመሳሳይ መልኩ አግኝተዋል።

መንግሥት ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር በአፋር ክልል ባቋቋመው የአስቸኳይ ዕርዳታ ማዕከል አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሎ ነበር። በማዕከሉ ፖሊስ እና የአካባቢው የጤና ባለሙያዎች ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎችን ጨምሮ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ስደተኞች ሕይወት አድን ሕክምና፣ አልሚ ምግብ፣ ጊዜያዊ መጠለያ፣ወደ መኖሪያ ቀዬአቸው የሚያደርስ መጓጓዣ እንዲሁም የምክር አገልግሎት ሰጥተዋል። ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች በአዘዋዋሪዎቻቸው ላይ በተከፈቱ የምርመራ ስራዎች እገዛ እንዲያደርጉ ባለስልጣናት ያበረታቷቸው ቢሆንም በዚህ ሂደት ላደረጉት እገዛ የሚደረግላቸው ከለላ አልነበረም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕግ የውጭ ዜጎች የሆኑ ሰለባዎች ወደመጡባቸው አገራት ማለትም አስቸጋሪ ሁኔታ እና የበቀል እርምጃ ወደሚጠብቃቸው ቦታዎች በግዳጅ እንዳይመለሱ አይከለክልም። በ2013 የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች ታስረው የቆዩበት፣ ለእስር የተዳረጉበት ወይንም መከሰሳቸውን የሚያመለክት ሪፖርት አልቀረበም። በውጭ አገር ተቀጥረው ለሚሠሩ ኢትዮጵያውያን የሚሰጠው የቆንስላ አገልግሎት ውሱን በመሆኑ፣ መንግሥት በዚህ መስክ የሚያደርገው ጥረት ደካማ እንደሆነ ቀጥሏል። የሠራተኞች ቅጥር ልውውጥ አገልግሎቶች አዋጅ ቁጥር 632/2009፤ ፈቃድ ያላቸው የአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሥራ ውል በሚፈርስበት ጊዜ ለሠራተኞች ድጋፍ መስጠት እንዲቻል የተወሰነ ገንዘብ በዝግ ሒሳብ እንዲያስቀምጡ ቢደነግግም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰለባዎችን ወደ ኢትዮጵያ ሲያጓጉዝ ለሚያወጣው የትራንስፖርት ወጪ ከዚህ በዝግ ሒሳብ ከተቀመጠ ገንዘብ አንድም ጊዜ አልተጠቀመም። በአንጻሩ ቤይሩት ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ትሰራ የነበረች አንዲት ኢትዮጵዊት ወጣት በአሰሪዋ ተገፍትራ ከአምስተኛ ፎቅ ከወደቀች በኋላ ሕክምናዋን ማጠናቀቋን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ አገሯ እንድትመለስ እገዛ አድርጓል። ኢትዮጵያ ስትደርስም ባለሰልጣናት ዕርዳታ ወደምታገኝበት አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ልከዋታል።

በአብዛኛው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች የሆኑና መሄጃ ያጡ ስደተኞችና እስረኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የመንግሥት ባለስልጣናት ሁኔታዎችን ያመቻቹ ቢሆንም፤ የተደረጉት ድጋፎች በአብዛኛው የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በማድረግ ላይ ያተኮሩና ለሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች አሰፈላጊ የሆነ ዘላቂነት ያለው የከላላ አገልግሎት ወይም ድጋፍ የማያካትቱ ነበሩ። በሚያዚያ 2013 ከየመን መንግሥት ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መግባት ያልቻሉ ወይም ከሳዑዲ ዓረቢያ የተባረሩ 618 ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። እነዚህ ተመላሾች አዲስ አበባ በደረሱበት ወቅት መንግሥት ምንም ዓይነት የሰብዓዊ ዕርዳታ አላደረገላቸውም ነበር። ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) አዲስ አበባ በሚገኘው ማዕከሉ አማካኘነት ለተመላሾቹ መጠለያ፣ ሕክምና እና የስነልቦና ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን የማፈላለግ ስራ ሰርቷል።መንግሥት አይ ኦ ኤም ላከናወናቸው ለነዚህ ተግባራት የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ አላደረገም።

ከህዳር 2013 ጀምሮ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ቪዛ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸውን እጅግ ብዙ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ሰራተኞች ከአገር አስወጥቷል። የኢትዮጵያ መንግስት በአብዛኛው የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ 163,000 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሳዑዲ ዓረቢያ የመመለስ ስራን የመራ ሲሆን፤ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የመስጠት ስራ አካል በመሆን ከዓለምዓቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር በቅርብ ትብብር ሰርቷል። የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ሳዑዲ በሚገኙ 64 ማቆያ ካምፖች የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን የማፈላለግ ስራ ሰርተዋል። በሳዑዲ የማቆያ ማዕከላት ባለው ኢሰብዓዊ አያያዝ ምክንያት የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም ስደተኞቹን በአስቸኳይ ወደአገራቸው ለመመለስ እንዲቻል በሳምንት ሁለት ጊዜ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። በቀን እስከ 7,000 ተመላሾችን ሲቀበል የነበረው መንግስት ከአይ ኦ ኤም ጋር በመተባበር ምግብ፣ ጊዜያዊ መጠለያና የሕክምና እርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ ተመላሾቹን ወደትውልድ ቀያቸው ለማድረስ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። አንድ ሌሊት በአዲስ አበባ ማሳለፍ ያስፈለጋቸው ተመላሾች በአይ ኦ ኤም ጊዜያዊ የመቆያ ጣቢያ እና መንግሥት ባዘጋጃቸው ሌሎች ሶስት ጣቢያዎች እንዲያድሩ ተደርገዋል። ከነዚህ ጣቢያዎች ሁለቱ የመንግሥት የማሰልጠኛ ተቋማት ሲሆኑ አንዱ ደግሞ መንግሥት የተከራየው ማዕከል ነው። በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ መከላከል፣ ዝግጁነት እና የምግብ ዋስትና ክፍል በመቆያ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የማዘዣ ጣቢያዎች በማቋቋም ከሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተወከሉ ባለሙያዎች ተመላሾቹ ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የሴቶች፣ ሕጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ብርድልብስና ምግብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ከተመላሾቹ መካከል ከፍተኛ የአእምሮ ጉዳት ለደረሰባቸው 87 የሕገወጥ ዝውውር ሰለባዎች ዕርዳታ ላደረገ አገርበቀል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በገንዘብ ዋጋ 12,000 ዶላር የሚገመት አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል። ክልላዊ መንግሥታት ለተመላሾች መሰረታዊ ድጋፍ የሚሰጡ ኮሚቴዎችን በማቋቋም፤ በሕብረት ስራ ማሕበራት እና በአነስተኛ የንግድ ስራዎች አማካኝነት ተመላሾችን ከማህበረሰቡ ለመቀላቀል የሚያስችል ዕቅድ ነድፈዋል። ለምሻሌ በአዲ አበባ 3,000 ከስደት ተመላሾች የስነልቦና ሕክመና ድጋፍ ያገኙ ሲሆን፤ 1,743 ደግሞ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና ተከታትለው ተመርቀዋል። ስደተኞችን ለማስመለሱ ስራ መንግሥት ወደ 2.5 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ያደረገ ሲሆን ለምግብ ወጪ ያደረገው ወደ 27,000 ዶላር የሚገመት ገንዘብ በለጋሾች በኩል ከአይ ኦ ኤም እንዲመለስለት ጠይቋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተደረገ ጥረት

መንግሥት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ያደረገው ጥረት መጠነኛ ነበር። በክልሎችና በብሔራዊ ደረጃ የተከናወኑ የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘመቻዎችን አስተባብሯል። እ.ኤ.አ. በ2013 ብሔራዊ የመገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ መሆን የሚያስከትላቸውን አደጋዎች የሚያሳ ድራማ ለአየር አብቅተዋል። በመንግሥት የሚመራው የሴቶች የልማት ሰራዊት ሕጻናትን ብቻቸውን ወደ ከተሞች እንዲጓዙ ማድረግ እንዲሁም በሕገወጥ ደላሎች የሚመቻች ስደት ብዙ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል የሚያስረዳ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራ ሰርቷል። ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት በሰራተኛና ማሕበራዊ ጉዳ ሚኒስቴር መሪነት በተቋቋመው ቴክኒካዊ የምክክር ቡድን አባል የሆኑ ከፌደራል የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ኤጀንሲዎች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎች ሳምንታዊ ስብሰባዎችን አድርገዋል። በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚንቀሳቀሰው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ግብረ ኃይል በየሩብ ዓመቱ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን፤ ከሳዑዲ ዓረቢያ ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማድረግ በኩል በስፋት ተሳትፏል።

መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው የስራ ቅጥር ኤጀንሲዎች ሕጋዊና ሕገወጥ የሰራተኞች ስደት እንደሚያስፈጽሙ ስለተደረሰባቸው እ.ኤ.አ ከጥቅምት 2013 ጀምሮ በአነስተኛ ስራ ዘርፍ ለመሰማራት ወደውጭ በሚደረግ ሕጋዊ ጉዞ ላይ መንግሥት እገዳ ጥሏል። በስራ ቅጥር ልውውጥ አዋጁ ላይ የግል የቅጥር አጀንሲዎችን ይበልጥ ስለመቆጣጠር፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የሰራተኞች ጉዳይ አታሼ ስለመመደብ፤ እንዲሁም ስደተኛ ሰራተኞችን የመለየት እና የማሰልጠን ስራ የሚያከናውን ገለልተኛ ኤጀንሲ ስለማቋቋም በተመለከተ የሚደረጉት ማሻሻያዎች እስከሚጸድቁ ድረስ እገዳው ይቀጥላል። መንግሥት የስራ ቅጥር ኤጀንሲዎችን እንቅስቃሴ ተከታትሎ ስደተኞችን ወደአደገኛ ቦታዎች ልከዋቸዋል በሚል ቁጥራቸው ያልታወቀ አጀንሲዎች እንዲዘጉ አድርጓል። ባለስልጣናት የተጣለው የጉዞ እገዳ ሕገወጥ ስደትን ሊያበረታታ እንደሚችል በመገንዘባቸው፤ ከፌዴራል ፖሊስ ተጨማሪ በጀትና የሰው ኃይል መድበው በኢትዮጵያ ድንበሮች ላይ የሚደረገው ጥበቃ እንዲጠናከር አድርገዋል። እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 2014 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሕገወጥ ደላላ እየተመሩ በሱዳን ድንበር ከአገር ሊወጡ የነበሩ 101 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አውሎ ነበር። እ.ኤ.አ. በሕዳር 2013 መንግሥት አንድ የባለስልጣናት ልዑካን ቡድን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመላክ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ያሉባቸውን ካምፖች እንዲመለከት አድርጓል። በነዚህ ጣቢያዎች ባለው የከፋ አያያዝ እና የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከተ በቀረቡ በርካታ ሪፖርቶች የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን በአፋጣኝ ለመመለስ ተንቀሳቅሷል። በዓመቱ ውስጥ በመንግሥት በጀት ለስደተኛ ሰራተኞች ሊሰጥ ታቅዶ የነበረ የስድስት ሳምንታት የቅድመ-ጉዞ ስልጠና በበጀት እጥረት ምክንያት ሳይሰጥ ቀርቷል። በቀደሙ ዓመታት መንግሥት ከዮርዳኖስ፣ ኩዌት እና ኳታር መንግሥታት ጋር የተፈራረማቸው የሰራተኞች ስደት ስምምነቶች እንደተጠበቁ ነበሩ። በ2013 ደግሞ መንግሥት ከጅቡቲ፣ ሱዳን፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ኬንያ መንግሥታት ጋር አዲስ ስምምነቶችን ተፈራርሟል። ሆኖም እነዚህ ስምምነቶች የዕረፍት ጊዜያትን፣ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ሁኔታዎች እንዲሁም ለቅጥር የሚፈጸም ክፍያን መከልከልን የመሳሰሉ ለሰራተኞች ከለላ የሚሰጡ አንቀጾችን በግልጽ አላመላከቱም።

በ2013 መንግሥት የወሳኝ ሁነቶች ጽህፈት ቤት ያቋቋመ ሲሆን፤ ይህም በ2012 በመላ አገሪቱ የልደት ምዝገባ እንዲደረግ ለማስገደድ የወጣውን አዋጅ ለመተግበር የታለመ ነበር። ሆኖም ወጥነት ያለው ብሔራዊ የመታወቂያ ካርድ ባለመኖሩ ይህ አዋጅ ሊተገበር አልቻለም። የመታወቂያ ካርዶችን በወረዳ ደረጃ መስጠት መቀጠሉ የሐሰት መታወቂያዎች እንዲዘጋጁ መንገድ ፈጥሯል። በሪፖርት ዓመቱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቁጥጥር ክፍል ሰራተኞች ብዛት ከ380 ወደ 291 የቀነሰ ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያቶቹ ስራ የሚለቁ ሰራተኞች መብዛት እና የሚመደብ በጀት ውሱንነት ናቸው። በ2013 መንግሥት ያዘጋጀው ለወጣት ሰራተኞች የተከለከሉ የስራ ዘርፎች ዝርዝር ሕግ ሆኖ ጸድቋል። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪዎች የሰራተኞች መብት ጥሰት ሲያጋጥማቸው ቅጣት ወይም የእርምት ርምጃ እንዲወስዱ የሚያስችል ስልጠና አልተሰጣቸውም ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት ርምጃዎች የውጭ ኢንቨስትመንትን ያሸሻሉ የሚል ስጋት ስላለ ነው። መንግሥት የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ለዓለምአቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ውጭ አገራት ከመሰማራታቸው በፊት የፀረ-ሕገ ወጥ ዝውውር ስልጠና የሰጠ ሲሆን፤ ስልጠናው የተሠጠው ከውጭ አገር በተገኘ ዕርዳታ ነው።

Leave a Reply